በመብት ተሟጋቾች የተተቸው የሊባኖስ እና የኢትዮጵያ ስምምነት ለፓርላማ ቀረበ 

በተስፋለም ወልደየስ

የቤት ሰራተኞች መብት እንዲከበር የሚሟገቱ ግለሰቦች እና ተቋማት ትችት ሲያሰሙበት የቆየው፤ የኢትዮጵያ እና የሊባኖስ መንግስታት የስራ ስምሪት ስምምነት ለፓርላማ ቀረበ። በሁለቱ ሀገራት ስምምነት ላይ ለኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች የሚከፈለው ዝቅተኛ ደመወዝ አለመካተቱ በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ጥያቄ ተነስቶበታል።

ኢትዮጵያ ከ300 ሺህ እስከ 400 ሺህ የሚገመቱ ዜጎቿ በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው ከሚሰሩባት ከሊባኖስ ጋር የስራ ስምሪት ስምምነት የተፈራረመችው በሚያዝያ 2015 ዓ.ም. ነበር። ስምምነቱ በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ወደፊት ወደ ስራ ውል የሚገቡ ዜጎችን መብት እና ጥቅም የማስከበር ዓላማ ያለው መሆኑ ዛሬ ለፓርላማ በቀረበው ሰነድ ላይ ተጠቅሷል። 

ሃያ አምስት አንቀጾች ያሉት ይኸው የስራ ስምሪት ስምምነት፤ የኢትዮጵያውያን ሰራተኞችን ምልመላ፣ የቅጥር ሁኔታዎች፣ የስራ ውል፣ የመብት ጥበቃ እና ሌሎችንም ጉዳዮች የሚዘርዝር ነው። ስምምነቱ በሊባኖስ በሚገኙ አሰሪዎች እና በኢትዮጵያውያን ሰራተኞች መካከል ተግባራዊ የሚደረግ “ሞዴል የስራ ውልን” ጭምር ያካተተ ነው።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ሁለቱ ወገኖች የሚፈራረሙት የስራ ውል፤ የአሰሪ እና ሰራተኛን “መብት እና ግዴታ” ማስቀመጥ እንዳለበት በስምምነቱ ላይ ሰፍሯል። በስራ ውሉ ላይ “የደመወዝ መጠን፣ ሰራተኛው ያለውን ጥቅማ ጥቅም፣ የስራ ሰዓት፣ የምግብ እና መኖሪያ አቀራረብ፣ ኢንሹራንስ፣ ጤና፣ አሰሪው የሚሰጠው የእረፍት ጊዜ መጠን እና ውሉ ለስንት ጊዜ ያህል እንደሚቆይ” መካተት እንዳለባቸውም ስምምነቱ ይደነግጋል።

በስራ ውሉ መሰረት ከኢትዮጵያውን ሰራተኞች ጋር ውል የገቡ የሊባኖስ ቀጣሪዎች፤ ለሰራተኞቻችው “የደርሶ መልስ የአውሮፕላን ትኬት” ማዘጋጀት እንደሚጠበቅባቸው ስምምነቱ ያስገድዳል። ኢትዮጵያውያን ዜጎች የሚሰማሩባቸው የስራ ሁኔታዎች፤ “ዓለም አቀፍ ህጎች እና መስፈርቶችን መሰረት ያደረገ” መሆን እንደሚገባውም በስምምነቱ ላይ ተቀምጧል። 

የስራ ስምሪት ስምምነቱ፤ ሁለቱ ሀገራት አባል ከሆኑባቸው ዓለም አቀፍ ህጎች እና መስፈርቶች በተጨማሪ የሊባኖስ እና የኢትዮጵያ መንግስታት በየፊናቸው ሊወጡ የሚገባቸውን ኃላፊነቶች አስቀምጧል። “የሊባኖስ መንግስት ለኢትዮጵያ ስራ ተቀጣሪዎች የተዘጋጀው ማመልከቻ ላይ የስራውን ጸባይ፣ መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች፣ ተቀጣሪው ሊሰራ የሚችልበትን የስራ ዘርፍ ከእነ አተገባበሩ እና መመሪያው፣ ደመወዝ፣ ጥቅማ ጥቅም፣ መኖሪያ፣ ትራንስፖርት እና አበሎችን በሀገሪቷ የስራ ሚኒስቴር ደንብ መሰረት መሟላቱን ማረጋገጥ አለበት” ሲል ስምምነቱ ያትታል።

የሊባኖስ መንግስት ለስራ ውሉ “ህጋዊ ፍቃድ እና እውቅና” ከመስጠት ኃላፊነቱ ባሻገር፤ በዓለም አቀፍ ህጎች ላይ በተመለከተው መሰረት ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች “በግዳጅ ስራ ላይ እንዳይሰማሩ ማድረግ” እንደሚኖርበት በስምምነቱ ላይ ሰፍሯል። ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች “በሕገወጥ መንገድ ፖስፖርታቸውን እንዳይነፈጉ፤ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ እና ደመወዝ እንዳይከለከሉ፤ የአካል፣ ስነ ልቦናዊ ወይም ጾታዊ ጥቃትና ሌሎች ማስፈራሪያዎች እንዳይደርስባቸው” የማረጋገጥ ኃላፊነት የተጣለውም በሊባኖስ መንግስት ላይ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ወደ ሊባኖስ የሚጓዙ ሰራተኞች “አስፈላጊ የሆኑ መስፈርቶች እና አካላዊ ብቃት ማሟላታቸውን፤ ስለሚሄዱበት ሀገር ህግ፣ ባህል እና ልምድ ገለጻ እና ስልጠና ማግኘታቸውን” እንደዚሁም የስራ ቅጥሩ በሀገሩ “የህግ ማዕቀፍ መሰረት የተዘጋጀ መሆኑን ማረጋገጥ” ይጠበቅበታል። ኢትዮጵያውን ሰራተኞች የሚፈራረሟቸው የስራ ውሎች፤ ወደ ሀገሬው የስራ ቋንቋ ተተርጉሞ የማዘጋጀትን ኃላፊነት ስምምነቱ የሰጠው ለኢትዮጵያ መንግስት ነው።

የስራ እና ክህሎት ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል እና የሊባኖስ የስራ ሚኒስትር ሙስጠፋ ባይራም ከስድስት ወራት በፊት በቤይሩት ከተማ የተፈራረሙት ይህ ስምምነት፤ ዛሬ ማክሰኞ ጥቅምት 6፤ 2016 ለተወካዮች ምክር ቤት በቀረበበት ወቅት ከፓርላማ አባላት የድጋፍ አስተያየቶች ተችረውታል። በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ከሰጡ ስምንት የፓርላማ አባላት አንዱ የሆኑት ዶ/ር ከፈና ኢፋ፤ ስምምነቱ  ኢትዮጵያውያን ዜጎች “በመካከለኛው ምስራቅ የሚደርስባቸውን መንገላታት ለማስቀረት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው” ሲሉ አሞካሽተውታል።

ፎቶ፦ ከስራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል የፌስቡክ ገጽ የተወሰደ

መሰል ስምምነቶች በሊባኖስ ብቻ ሳይሆን በቀጣይነት “በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ተግባራዊ እንደሚደረጉ” ያላቸውን ተስፋ የገለጹት የፓርላማ አባሉ፤ በስምምነቱ “በደንብ መታየት አለበት” ያሉትን ጉዳይ ጠቁመዋል። የምስራቅ እስያ ሀገራት የስራ ስምሪትን በተመለከተ በመካከለኛው ምስራቅ ካሉ ሀገራት ጋር ባደረጓቸው ውሎች ላይ መነሻ ደመወዝ እንዳስቀመጡ መመልከታቸውን የተናገሩት ዶ/ር ከፈና፤ ተመሳሳይ አካሄድ ኢትዮጵያ ከሊባኖስ ጋር ባደረገችው ስምምነት ላይ መካተት እንደነበረበት ጠቁመዋል። 

“መነሻ ደመወዝ ካልተቀመጠ፤ ሰራተኞቹ ወደ ሀገራቸው በሚመለሱበት ጊዜ ራሳቸውን ለማቋቋም በጣም ይቸገራሉ። ይሄንን ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች በተግባር በኢትዮጵያ ውስጥ እያየን ነው” ሲሉ ስምምነቱ የሚመራለት የተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን “ከግምት ውስጥ እንዲያስገባ” የፓርላማ አባሉ አሳስበዋል። ኢትዮጵያ እና ሊባኖስ ባደረጉት ስምምነት ላይ፤ ደመወዝ የሚከፈለው ቀጣሪ እና ሰራተኛ “በተስማሙበት የስራ ውል መሰረት እንደሆነ” ከመግለጽ ውጪ ስለ ክፍያው መነሻ የተብራራ ነገር የለም።

የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል በስምምነቱ ላይ በግልጽ ያለመካተቱ ጉዳይ፤ የቤት ሰራተኞች መብት እንዲከበር በሚሟገቱ ግለሰቦች እና ተቋማትም የሚነሳ ትችት ነው። በሊባኖስ ለሚገኙ ኢትዮጵያውን የቤት ሰራተኞች ላለፉት ስድስት ዓመት የተለያዩ ድጋፎች ሲያቀርብ የቆየው “እኛ ለእኛ በስደት” የተሰኘው የግብረ ሰናይ ድርጅት መስራች የሆነችው ባንቺ ይመር፤ ይህንኑ ትችት ከሚያስተጋቡት አንዷ ናት።

ሁለቱ ሀገራት በተስማሙበት ሰነድ ላይ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ሊከፈላቸው የሚገባ ዝቅተኛ ደመወዝ አለመቀመጡ፤ የክፍያው መጠን በሊባኖስ ወገን እንዲተመን የሚያደርገው መሆኑን የየግብረ ሰናይ ድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግራለች። “የሊባኖስ መንግስት 50 ዶላር እከፍላለሁ ካለ፣ በሀገሪቷ ህግ መሰረት ልጆቻችን መቀበል አለባቸው። 150 ዶላር ካለም [እንደዚያው]። በስምምነቱ መሰረት ‘ይሄ ቢሆን፤ ይሄ ይሆናል’ የሚል ምንም የተቀመጠ ነገር ስለሌለ፤ በሀገሪቷ መተዳደሪያ ህግ መሰረት ያለው የከፋላ ስርዓት ተግባራዊ ይሆናል ማለት ነው” ስትል ባንቺ ታስረዳለች። 

ሊባኖስን ጨምሮ ቢያንንስ በመካከለኛው ምስራቅ ስድስት ሀገራት ተግባራዊ የሚደረገውን ይህን አሰራር፤ ባንቺ የምትገልጸው “ዘመናዊ ባርነት” በሚሉ ቃላት ነው። በሊባኖስ በቤት ውስጥ ሰራተኝነት ሰባት ዓመት ያገለገለችው ባንቺ፤ በከፋላ ስርዓት “አንድ የቤት ውስጥ ሰራተኛ ሊባኖስ እግሯ ከረገጠ በኋላ ያለ አሰሪዋ ፍቃድ ደጅ አትወጣም” ትላለች። “ስራ መቀየር ሳይስማማት ቀርቶ ስራ መቀየር ብትፈልግ አሰሪዋ መፍቀድ እንዳለበት፤ ብትታመም፣ የተለያየ ችግር ቢደርስባት ከሀገር ለመውጣት ‘አሰሪዋ ፍቃደኛ መሆን አለበት’ የሚል ስርዓት ማለት ነው” ስትል ታብራራለች። 

ለፓርላማ የቀረበው የሊባኖስ ስራ ስምሪት ስምምነት “የኢትዮጵያውያን ሰራተኞች መብት እና ደህንነት፤ በሊባኖስ የሚገኙ የሌላ ሀገር ዜጎች በሚያገኙት ልክ” መሆኑን ያስቀምጣል። ይህንኑ የማረጋጥ ኃላፊነትም በሊባኖስ መንግስት ላይ ይጥላል። የቤት ውስጥ ሰራተኞችም ሆነ በጥቅሉ የሌላ ሀገር ዜጎች ሰራተኞች መብት በሊባኖስ የሰራተኛ ህግ ላይ አመለካተቱን የምትጠቅሰው ባንቺ፤ ይህን በተመለከተ በስምምነቱ የተካተተው አንቀጽ የኢትዮጵያውያንን መብት የሚያስከብር አለመሆኑን ትሟገታለች።

ፎቶ፦ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የፌስቡክ ገጽ የተወሰደ

የሰራተኞች መብት እና ክብር በሚጣስበት ወቅት፤ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ጥቅም ላይ የሚውሉት የሊባኖስ ህጎች መሆናቸው በስምምነቱ ላይ መጠቀሱንም አጥብቃ ትተቻለች። “በመሰረታዊነት የእኛ ዕጣ ፈንታ በእኛ ሀገር መንግስት እንጂ መያዝ እና መከራከር የነበረበት፤ ለሊባኖስ መንግስት መተው የለበትም” የምትለው ባንቺ፤ በሊባኖስ ህግ መሰረት መዳኘትን በተመለከተ በስምምነቱ የሰፈረው የደመወዝ ወለል ጉዳይ አለመካተት የ“እኛን መብት አሳልፎ የሰጠ ነው” ስትል ታክላለች።

በስምምነቱ ላይ የተጠቀሱ የኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞች “መብት እና ጥቅም” ጉዳይ፤ በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ወቅትም ተነስቷል። አቶ መለሰ መና የተባሉ የፓርላማ አባል፤ የስራ ስምሪት ስምምነቱ “የዜጎችን ነጻነት፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝ እና ጥቅሞችን” “በደንብ ገባ ተደርጎ ምላሽ የሚሰጥ መሆን” እንዳለበት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። “የዜጎቻችንን መብት እና ጥቅም የሚያስከብር ጥርስ ያለው አዋጅ ሆኖ እንዲወጣ ማድረግ ያስፈልጋል” ሲሉም ስምምነቱን የሚመለከተው የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን በሚገባ እንዲመለከተው አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ እና የሊባኖስ መንግስታት የተፈራረሙት የስራ ስምሪት ስምምነት ተግባራዊ የሚደረገው፤ “ሀገራቱ በህጎቻቸው መሰረት ስምምነቱን ለማጽደቅ የሚያስፈልጉትን ቅድመ ሁኔታዎች ሲያሟሉ እና ይህንንም ሌላኛው ወገን ሲያሳውቁ” እንደሆነ በስምምነቱ ላይ ተገልጿል። በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የተገኙ 246 የፓርላማ አባላት፤ ስምምነቱ በዝርዝር እንዲታይ ለሰው ሀብት ልማት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች የመሩት በሙሉ ድምጽ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)