በጃፓን የታተሙ የመማሪያ መጻሕፍት በሶስት ሳምንታት ውስጥ ለትምህርት ቤቶች እንደሚከፋፈሉ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

በተስፋለም ወልደየስ

በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያለውን የመማሪያ መጻሕፍት እጥረት ለመቅረፍ በውጭ ሀገር ከታተሙ መጻሕፍት ውስጥ 249 ኮንቴየነር የህትመት ወጤቶች ከትላንት በስቲያ ጅቡቲ ወደብ መድረሳቸውን የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ። እነዚህ መጻሕፍት በቀጣዮቹ ሶስት ሳምንታት ለየትምህርት ቤቶቹ በሚሰራጩበት ወቅት፤ አንድ መጽሐፍ ለአራት ተማሪዎች እንዲዳረስ ተደርጎ እንደሚከፋፈሉም አስታውቋል።

በዘንድሮው የትምህርት ዘመን ከቅድመ አንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ የተመዘገቡ ተማሪዎች ብዛት 20.6 ሚሊዮን ነው። ከእነዚህ ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ቁጥር 2.1 ሚሊዮን መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። ሆኖም የትምህርት ዘመኑ ከተጀመረ ከአንድ ወር በኋላም የመማሪያ መጻሕፍት ለተማሪዎች አልተሰራጨም። 

የመማሪያ እና ማስተማሪያ መጻሕፍት በጊዜው ተደራሽ ያለመሆን ጉዳይ፤ የተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ትላንት ረቡዕ ጥቅምት 6፤ 2016 በጠራው ስብሰባ ላይም ጥያቄ አስነስቶ ነበር። በቋሚ ኮሚቴው የተዘጋጁ ጥያቄዎችን በንባብ ያሰሙ አንድ የፓርላማ አባል፤ የመጻሕፍት ግብዓት ባልተሟላበት ሁኔታ “የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ እንዴት ማድረግ ይቻላል?” የሚል ጥያቄ ለትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች አቅርበዋል።

ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ “በፌደራል አሰራር መሰረት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን [መጻሕፍት] አሳትሞ የማከፋፈል ስራ የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊነት” መሆኑን አስታውሰዋል። የትምህርት ሚኒስቴር ለጉዳዩ በሰጠው ቅድሚያ ትኩረት፤ መስሪያ ቤቱ ከነበሩት ሌሎች ፕሮጀክቶች 45 ሚሊዮን ዶላር ያህል በማዘዋወር ለመጽሐፍ ህትመት እንዲውል ማድረጉን ገልጸዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ዝቅተኛ ዋጋ ያቀረበው “ቶፓን” የተባለ የጃፓን የህትመት ኩባንያ እንደነበር የጠቆሙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ በዚህም ምክንያት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መጽሐፍ በመታተም ላይ የሚገኘው በጃፓን መሆኑን አስረድተዋል።  በኩባንያው ከታተሙ መጻሕፍት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ 20 ኮንቴነሮች ጅቡቲ ወደብ የደረሱት ከ15 ቀናት በፊት መሆኑን ተናግረዋል።

የመጀመሪያው ዙር መጻሕፍት በትራንስፖርት ችግር ምክንያት ለትምህርት ቤቶች እስካሁንም አለመሰራጨታቸውን ፕሮፌሰር ብርሃኑ በትላንቱ ስብሰባ ላይ አስታውቀዋል። ሆኖም ከጭነት አጓጓዥ ድርጅቶች ጋር ከትላንት በስቲያ ከተደረገ ውይይት በኋላ መጻሕፍትን የማጓጓዝ ስራ ለመጀመር ከስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል። ከትላንት በስቲያ ጅቡቲ ወደብ የደረሱትን 249 ኮንቴነር የመማሪያ መጻሕፍትን፤ ከሁለት እስከ ሶስት ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ትምህርት ቤቶች እንደሚሰራጩም የትምህርት ሚኒስቴሩ አክለዋል።

“በሁሉም ትምህርት ቤቶች ያሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በሚቀጥሉት ሶስት ሳምንታት ውስጥ፤ ቢያንስ አንድ መጽሐፍ ለአራት ተማሪ ይደርሳቸዋል” ሲሉም ፕሮፌሰር ብርሃኑ ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። “የሚቀጥለው ሴሚስተር ከማለቁ በፊት ደግሞ አንድ [መጽሐፍ] ለሁለት ይደርሳል። በአጠቃላይ ያሳተምነው ለሁለት ተማሪ አንድ መጽሐፍ በሚደርስ መልኩ ነው። እርሱን እናደርሳለን” ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር በዘንድሮው ዓመት አሳትሞ ለማሰራጨት ያቀደው የመማሪያ እና ማስተማሪያ መጻሕፍት ብዛት 20.6 ሚሊዮን መሆኑን ከመስሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ሚኒስቴሩ በመጀመሪያው ዙር ለተማሪዎች ለማሰራጨት ያቀደው 8.3 ሚሊዮን መጻሕፍት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)