በተስፋለም ወልደየስ
ጊዜው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡ ሰሞን ነው። አራት ኪሎ ከሚገኘው ጽህፈት ቤታቸው ከገቡ ገና አራተኛ ወራቸው። ወቅቱ መንግስትን እና ገዢውን ፓርቲ የሚመለከቱ፤ ከዚህ ቀደም በአደባባይ የማይደመጡ የተለያዩ የተቃውሞ እና ሞጋች ሀሳቦች እንደ ልብ የሚንሸራሸሩበት ነበር። በዚህ ጊዜ ነበር ባልተለመደ መልኩ በአንድ የመንግስት ቁልፍ ተቋም የሚሰሩ ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ያወጁት።
የስራ ማቆም አድማውን ያደረጉት በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እና በሌሎች ስምንት ከተሞች ባሉ አየር ማረፊያዎች ተመድበው የሚሰሩ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ነበሩ። ባለሙያዎቹ አድማውን የመቱት ለስምንት ዓመታት ያህል ሲያቀርቡት የቆዩት “የሙያ ዕውቅና፣ የደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም መከበር ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ባለማግኘቱ” መሆኑን በወቅቱ አስታውቀው ነበር።
የባለሙያዎቹ ቀጣሪ የሆነው ኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን፤ በአድማው ምክንያት መደበኛ በረራዎች እንዳይስተጓጎሉ በመስሪያ ቤቱ በኃላፊነት ደረጃ ያሉ ባለሙያዎችን፣ ጡረተኞችን እና ከስራው የተገለሉ ሰዎችን ለመጠቀም ተገድዷል። የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች ያቀረቡት የደመወዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች “የተጋነነ ነው” የሚል አቋም የነበረው ቢሆንም፤ ችግሩን ለመፍታት ኮሚቴ ተዋቅሮ ጥናት በመደረግ ላይ መሆኑን አስታውቆ ነበር።
ጥናቱ በአጭር ጊዜ ከተጠናቀቀ በኋላ ለጥያቄው ምላሽ እንደሚሰጥ በወቅቱ ቃል ቢገባም፤ ከአምስት ዓመት በኋላም ባለሙያዎቹ ተመሳሳይ ጥያቄያቸውን ይዘው ደጅ መጥናት ቀጥለዋል። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በዓመቱ “ኦክቶበር 20” ታስቦ የሚውለውን “የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ቀን” ትላንት አርብ ጥቅምት 9፤ 2016 በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በተከበረበት ዕለት ይኸው ጉዳይ በተደጋጋሚ ተስተጋብቷል።
በክብረ በዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ግሩም የኔነህ፤ የባለሙያዎቹ “ፍትሃዊ ጥያቄዎች” እስካሁን ባለመመለሳቸው በርካታ ሰራተኞች ስራቸውን ለመልቀቅ መገደዳቸውን በአጽንኦት አንስተዋል። “በአሁኑ ወቅት ተቋሙ በሚከፍለው አነስተኛ ደመወዝ የተነሳ፤ በየደረጃው ያሉ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ከሙያው በመሸሽ ላይ ይገኛሉ። ለአብነት ባሳለፍነው የ2015 በጀት ዓመት ከ12 በላይ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ተቋሙን ለቅቀዋል” ሲሉ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።
“ይህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የባለሙያዎች ፍልሰት በተቀሩት ባለሙያዎች ላይ ከፍተኛ የስራ ጫና እና ለተከታታይ የስራ ሰዓታት በስራ ላይ እንዲቆዩ ስለሚያስገድድ በበረራ ደህንነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል” ሲሉ አቶ ግሩም አሳስበዋል። ጀማሪ ተተኪ ባለሙያዎች ለማፍራት በተደረገው ጥረት ስልጠና ከተሰጣቸው ውስጥ፤ “አንድ ሶስተኛ ያህሉ ብቻ ወደ ስራ መሰማራታቸው” ሁኔታውን አስቸጋሪ እንዳደረገው የማህበሩ ፕሬዝዳንቱ ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 180 የሚሆኑ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በስራ ላይ እንደሚገኙ ከማህበሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። የባለሙያዎቹ ብዛት ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ማደግ የቻለው በ60 ገደማ ብቻ መሆኑ፤ ሙያው ተተኪ ባለሙያዎችን “ከገበያ ላይ ተወዳድሮ ለማግኘት ትልቅ ተግዳሮት እንደገጠመው” የሚያሳይ መሆኑን የማህበሩ አባላት ይገልጻሉ። አሁን በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎች በሚከፈላቸው ደመወዝ አነስተኛነት ምክንያት፤ በትርፍ ጊዜያቸው እንደ ራይድ ባሉ “የሜትር ታክሲ” አይነት ተጨማሪ ስራዎችን ለመስራት መገደዳቸውን ያስረዳሉ።
በአሜሪካ የሰራተኞች ስታስቲክስ ቢሮ መረጃ መሰረት፤ በሀገሪቱ የሚገኙ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ዓመታዊ አማካይ የደመወዝ መጠን 132,250 ዶላር ነው። ይህ ማለት በዚህ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች በየወሩ 11 ሺህ ዶላር ገደማ አማካይ ደመወዝ ያገኛሉ። በኬንያ የሚገኙ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች እንደ የደረጃቸው ከስድስት ሺህ ዶላር እስከ 15 ሺህ ዶላር ገደማ እንደሚከፈላቸው “ቱኮ” የተሰኘው የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ዘግቧል።
በኢትዮጵያ በተመሳሳይ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ትልቁ ወርሃዊ የደመወዝ መጠን 300 ዶላር ገደማ ሲሆን አነስተኛው ደግሞ 90 ዶላር አካባቢ መሆኑን ሰራተኞቹ ይናገራሉ። ለኢትዮጵያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሚከፈለው ደመወዝ እና የሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ክፍያ ማነስ፤ በባለሙያዎቹ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑን የአውሮፕላን አብራሪዎችም ይስማሙበታል። የአቢሲኒያ በረራ አገልግሎት የተሰኘው የግል ድርጅት ባለቤት እና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ካፒቴን ሰለሞን ግዛው፤ “ስለ ኑሮ እየተጨነቀ አውሮፕላን የሚያስተናግድ የአየር በረራ ተቆጣጣሪ safe አድርጌ አላየውም” ሲሉ ጉዳዩ “በደንብ ሊታሰብበት” የሚገባ መሆኑን ያሳስባሉ።
“የማየው ችግር አለ። የእነርሱ ችግር የእኔም ችግር ነው፤ የሀገሬ ችግር ስለሆነ። ስለዚህ ይሄ ነገር የአንድ የመንግስት ድርጅት [ጉዳይ] ተደርጎ ባይታይ [እላለሁ]። ምክንያቱም ይሄ የመንግስት ድርጅት ሳይሆን የዓለም ድርጅት ነው። በsafety በአየር መንገዳችን አንድ ችግር ቢገጥመን፤ የእኛ ነገር ስለሚጋነን ብዙ ችግር ውስጥ እንገባለን። ስለዚህ መንግስት ይሄንን ነገር የራሱ ችግር አድርጎ ቢያይ ተገቢ ይመስለኛል” ብለዋል ካፔቴን ሰለሞን።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለ39 ዓመታት ያህል በአብራሪነት ያገለገሉት “የኢስት አፍሪካን አቪዬሽን” የግል የበረራ ድርጅት ባለቤት ካፒቴን ሙላት ለምለምአየሁም በትላንትናው ክብረ በዓል ላይ ተመሳሳይ ሃሳብ ሰንዝረዋል። የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን ችግር በየጊዜው ለሚያገኟቸው የመንግስት ባለስልጣናት ሲያስረዱ መቆየታቸውን ካፒቴን ሙላት ተናግረዋል። ከላይ እስከ ታች ያሉ ባለስልጣናት ጥያቄውን “በአሉታዊ መልክ አይተውት አያውቁም” የሚሉት አንጋፋው አብራሪ፤ “የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ይሄ ነገር ይሳካል ብዬ እገምታለሁ” ሲሉ ተስፋቸውን አጋርተዋል።
በትላንቱ ዝግጅት ላይ ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዶ/ር አለሙ ስሜ እና የሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴም ተመሳሳይ ተስፋ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል። ዶ/ር አለሙ “በዘርፉ የተሰማሩ የአየር ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች የሚገባቸውን ከስራቸው ጋር የሚመጥን ጥቅማ ጥቅም እና ደመወዝ እንዲያገኙ እንዲሁም የመገልገያ መሳሪያዎች እንዲዘምኑ ከማድረግ አንጻር፣ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም በፈቀደ መጠን እና መንግስት መክፈል በቻለው መጠን ጥያቄያችሁን በአዎንታዊ መልኩ ለመመለስ የሚኒስቴር መስሪያ ቤታችንም፤ መንግስትም በትኩረት እየሰራበት መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ” ሲሉ ለክብረ በዓሉ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
እርሳቸው ይህን ቢሉም፤ የዘርፉ ባለሙያዎች ግን በመንግስት የተገባው ቃል በዚህም ዓመት ወደ ተግባር መቀየሩ ላይ ጥርጣሬ አላቸው። ከአቶ ጁነዲን ሳዶ ጀምሮ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የመሩ ባለሥልጣናት መሰል ተስፋዎችን ሲሰጧቸው መቆየታቸውን መልስ ብለው የሚያስታውሱት ባለሙያዎቹ፤ ለጥያቄዎቻቸው ተግባራዊ ምላሽ እስካላዩ ድረስ በክብረ በዓሉ ላይ የተገባውን ቃል ለማመን እንደሚቸገሩ ይናገራሉ። ከአምስት አመት በፊት ባካሄዱት የስራ ማቆም አድማ ምክንያት ዘጠኝ የሚሆኑ ባልደረቦቻቸው ለእስር የተዳረጉባቸው ባለሙያዎቹ፤ መንግስት ጥያቄዎቻቸውን ሳይመልስ በዚሁ ከቀጠለ “ያለን አማራጭ ሙያችንን ትተን በሌላ ስራ ላይ መሰማራት ነው” ይላሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)