በኢትዮጵያ ግጭት ዋነኛ አጀንዳ እንዲሆን የሚፈልጉ ግለሰቦች “ተልዕኮ ያላቸው ናቸው” – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ 

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ግጭት ዋነኛ አጀንዳ እንዲሆን የሚፈልጉ ግለሰቦች “ተልዕኮ ያላቸው (infiltrator) ናቸው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። በሀገሪቱ ያለውን “ግጭት እና አላስፈላጊ መገዳደል”፤ የመከላከያ እና የፖሊስ ተቋማት “እየተቆጣጠሩት” መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

አብይ ይህን ያሉት ባለፈው መስከረም ወር መጀመሪያ በአዳማ ከተማ በተካሄደ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ላይ ባቀረቡት እና በትላንትናው ዕለት በቴሌቪዥን ጣቢያዎች በተላለፈ ገለጻቸው ላይ ነው። ከ“ዕዳ ወደ ምንዳ” በተሰኘ መሪ ቃል ለ11 ቀናት የተካሄደው የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ዓላማ፤ የብልጽግና ፓርቲ “ለህዝቡ የገባውን ቃል ማስፈጸም የሚያስችል የአመራር አቅም እንዲፈጠር ማድረግ” መሆኑ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።

የገዢው ፓርቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት አብይ በስልጠናው ላይ ያቀረቡት ገለጻ የተወሰነው ክፍል፤ “ተረክ እና ትርክትን” የሚመለከት ነበር። “ታሪክን ማዛባት ልማድ የሆነበትን፣ የቆሸሸ ፖለቲካ ማጽዳት ያስፈልጋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ለዚህም “ነገርን በእውነት እና በልክ ማስቀመጥ” እንደሚገባ አመልክተዋል።

ብልጽግና ፓርቲ የሚሰራቸውን ስራዎች “ሊያንኳስሱ” እና “ሊያዛቡ” የሚችሉ ወገኖች ቢኖሩም፤ ገዢው ፓርቲ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚያደርገው ጥረት “የሚያቆመው ኃይል የለም” ሲሉ ለከፍተኛ አመራሮቹ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ “ግጭት አለ፤ አላስፈላጊ መገዳደል አለ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከፍተኛ አመራሮቹ ይህንን “የፓርቲው እና የመንግስት ዋነኛ አጀንዳ” በማድረግ “የስራቸውን ድካም በእሱ መሸፈን” እንደሌለባቸው አሳስበዋል።

“ኢትዮጵያ ውስጥ እርስ በእርስ መባላት፣ መጠላላት፣ መገፋፋት፣ መፈናቀል፣ መቆም አለበት። አደገኛ ነገር ነው። ከዚያ በላይ እንዳንወነጨፍ እያደረገን ነው። ግን ሁሉ አጀንዳ እሱ ብቻ ነው? አይደለም። እሱ እንዲሆን የሚፈልጉሳ? ተልዕኮ አላቸው፤ infiltrator ናቸው። የተላኩ ሰዎች ናቸው” ብለዋል አብይ። ሆኖም ግለሰቦቹ ከየትኛው አካል ወይም ወገን ተልዕኮ እንደተሰጣቸው፤ በቴሌቪዥን በተላለፈው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ ላይ አልተብራራም።

የኢትዮጵያ ህዝብ የብልጽግና ፓርቲ ተወካዮችን ከመምረጥ ባሻገር፤ በተለያየ ወቅት ለሚቀርብለት ጥሪ በጎ ምላሽ እየሰጠ እንደሚገኝ አብይ ተናግረዋል። “‘ተዋጋ’ አልከው፤ ልጁን ሰጠ። ‘አረንጓዴ አሻራ’ አልከው፤ ወጥቶ ተከለ። ‘ድሃ አልብስ፣ አብላ’ አልከው – አበላ። ህዝብ respond እያደረገ ነው። ስራ እና አሳየው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አመራሮቹ ምን ሊያደርጉ እንደሚገባቸው ነግረዋቸዋል።

አብይ “የሰከሩ” እና “ያበዱ” ሲሉ የጠሯቸው ግለሰቦች “በትርክት የሚያሳብዷት ኢትዮጵያን ለመፍጠር” እንደሚያስቡ ጠቅሰው፤ የገዢው ፓርቲ አመራሮች እና አባላት ለዚህ “ተባባሪ መሆን እንደሌለባቸው” አሳስበዋል። ለዚህ ዓላማ ተባባሪ መሆን የሚፈልጉ አመራሮች ካሉ፤ በፓርቲው ውስጥ “ጊዜያቸውን ማባከን” እንደሌለባቸውም አክለዋል። “እዚህ ውስጥ ብዙ አለ፤ ጊዜ የሚያባክን ሰው። ጊዜህን አታባክን። ቦታህን ፈልግ” ሲሉም ለአመራሮቹ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት አስተላልፈዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)