አቶ ሳንዶካን ደበበ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ተሾሙ

በተስፋለም ወልደየስ

ላለፈው አንድ ዓመት በፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲሰሩ የቆዩት አቶ ሳንዶካን ደበበ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ (chief of staff) ሆነው ተሾሙ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የልዩ ጽህፈት ቤታቸውን እንዲመሩ አቶ ሳንዶካንን የሾሟቸው፤ ከሶስት ሳምንት በፊት መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

ልዩ ጽህፈት ቤቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስር ካሉ ስድስት መዋቅሮች አንዱ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስር ያሉ ሌሎች መዋቅሮች የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት፣ የቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት፣ የፕሬስ ሴክሪተሪያት፣ የፖሊሲ እና የአፈጻጸም ክትትል ክፍል እንዲሁም የሪፐብሊኩ ጠባቂ ናቸው። 

አቶ ሳንዶካን ልዩ ጽህፈት ቤቱን እንዲመሩ ከተሾሙ በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር የመጀመሪያ የውጭ ጉዟቸውን ወደ ቻይና ማድረጋቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ሹመቱንም ሆነ የቻይናውን ጉዞ አቶ ሳንዶካን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በቻይና በነበራቸው የአምስት ቀናት ቆይታ በሶስተኛው የቤልት ኤንድ ሮድ ፎረም መክፈቻ ላይ ንግግር አድርገዋል። አብይ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ባደረጉበት ወቅት እንዲሁም በሻንጋይ እና ሴቹዋን ግዛት በነበሯቸው ጉብኝቶች፤ ከእርሳቸው ጋር ወደ ስፍራው የተጓዙ የልዑካን ቡድን አባላት አብረዋቸው ነበሩ። 

አብይ አህመድ ወደ ስልጣን እንደመጡ የልዩ ጽህፈት ቤታቸው ኃላፊ አድርገው በመጀመሪያ የሾሟቸው አሁን በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑትን አቶ ፍጹም አረጋን ነው። እርሳቸውን በመተካት የልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት በአሁኑ ወቅት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የሆኑት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ናቸው። አቶ ሽመልስ በሚያዝያ 2011 ዓ.ም. አቶ ለማ መገርሳን በመተካት የኦሮሚያ ክልልን እንዲመሩ ከመሾማቸው በፊት፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽህፈት ቤት በኃላፊነት ለሰባት ወራት ሰርተዋል። 

ከግንቦት 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ልዩ ጽህፈት ቤቱን ለስምንት ወራት በኃላፊነት ሲመሩ የቆዩት፤ በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ናቸው። ዶ/ር ሹመቴ ከልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊነታቸው ተነስተው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳን) በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ በጥር 2012 ዓ.ም. ሲሾሙ በምትካቸው በቦታው የተመደቡት አቶ መስፍን መላኩ ናቸው።

አቶ መስፍን በየካቲት 2015 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ክላስተር አስተባባሪ ሆነው ከተሾሙ በኋላ የኃላፊነት ቦታውን ተረክበው የነበሩት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አማካሪነት ሲሰሩ የነበሩት አቶ መሐመድ ራፊ አባራያ መሆናቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። አዲሱ ተሿሚ አቶ ሳንዶካን ወደ ልዩ ጽህፈት ቤት ኃላፊነት ከመምጣታቸው በፊት፤ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ላለፉት 12 ዓመታት ሰርተዋል። 

በምግብ ሳይንስ እና በምርት አሰባሰብ ቴክኖሎጂ ከሐረማያ ዩኒቨርስቲ በ2001 ዓ.ም. የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት አቶ ሳንዶካን፤ ወደ ስራው ዓለም የገቡት የብዝሀ ህይወት ጥበቃ ኢንስቲትዩት ይባል በነበረው መስሪያ ቤት ነው። በኢንስቲትዩቱ በምርምር ሰራተኝነት ስራ በጀመሩበት በ2003 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በምግብ ሳይንስ እና ኒዩትሪሽን ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኘተዋል። አቶ ሳንዶካን ሶስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ያገለገሉበትን ይህን መስሪያ ቤት በመልቀቅ፤ የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲን በመምህርነት ተቀላቅለዋል። 

“አስቱ” በሚል መጠሪያው ይበልጥ በሚታወቀው በዚህ ዩኒቨርስቲ ለአንድ ዓመት ከአራት ወራት ያስተማሩት አቶ ሳንዶካን፤ ወደ መንግስት የስራ ኃላፊነት የመጡት በ2007 ዓ.ም. ነው። አቶ ሳንዶካን በመጀመሪያው የመንግስት ተቋም ሹመታቸው፤ አብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት በዋና ዳይሬክተርነት የመሩትን የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከልን ለአንድ ዓመት ከሶስት ወራት መርተዋል።

ፎቶ፦ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን

አቶ ሳንዶካን ከዚያ በኋላ በኃላፊነት በተሾሙባቸው ሁለት ተቋማት የነበራቸው ቆይታም ተመሳሳይ ነበር። በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት በዳይሬክተርነት ለአንድ ዓመት የሰሩት አቶ ሳንዶካን፤ በኢትዮጵያ ባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በምክትል ዳይሬክተርነት ለአንድ ዓመት ከሁለት ወራት አገልግለዋል። ከግንቦት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በነበሩት ሁለት ዓመታት ደግሞ ስያሜውን ወደ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት ወደቀየረው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል በመመለስ በዋና ዳይሬክተርነት ኃላፊነት ቆይተዋል። 

ወጣቱ የመንግስት የስራ ኃላፊ የብዙዎቹን ትኩረት የሳቡት፤ ሌላኛዋን ወጣት ባለስልጣን ለሊሴ ነሜን በመተካት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ በመሆን በሰኔ 2012 ዓ.ም. ሲሾሙ ነበር። ከመንግስት ግዙፍ የልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን፤ አቶ ሳንዶካን ከተረከቡት በኋላ ከምስረታው ጀምሮ ከነበረበት ኪሳራ በመውጣት 340 ሚሊዮን ብር ትርፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ማስመዝገቡን አስታውቋል። 

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አዲስ አበባን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች የሚገኙ 10 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በስሩ የሚያስተዳድር ነው። ኮርፖሬሽኑ በ2014 በጀት ዓመት 1.2 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን ይፋ ካደረገ ከወራት በኋላ ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ በዋና ስራ አስፈጻሚነት ሲመሩት የቆዩት አቶ ሳንዶካን የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ተሹመዋል።

ፎቶ፦ የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር

አቶ ሳንዶካን በፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የነበራቸው ኃላፊነት፤ በአካባቢ ጥበቃ፣ የአየር ንብረት እና የስነ ህዝብ ጉዳዮች ላይ “ፖለቲካዊ አመራር” መስጠት መሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ አስፍረው ነበር። አቶ ሳንዶካን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በነበራቸው ቆይታ የአየር ንብረትን በተመለከቱ ዓለም አቀፋዊ ስብሰባዎች ላይ ኢትዮጵያን በመወከል በተደጋጋሚ ተገኝተዋል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፍ መድረኮች የነበራት ሚና “ደካማ ሆኗል” የሚል ትችት በቅርቡ መሰንዘራቸው ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)