ለምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት በዕጩነት የሚቀርቡ ሁለት ግለሰቦች ማንነት፤ እስከ ህዳር ወር ማብቂያ ባለው ጊዜ ይገለጻል ተባለ   

በተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን የሚተኩ ዕጩዎችን እንዲመለምል የተቋቋመው ኮሚቴ፤ አጣርቶ የሚለያቸውን ሁለት ዕጩዎች የህዳር ወር ከመጠናቀቁ አስቀድሞ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እንደሚያቀርብ አስታወቀ። ኮሚቴው ጥቆማዎችን ከመጪው ሰኞ ህዳር 3፤ 2016 ጀምሮ ባሉት ተከታታይ አስር ቀናት እንደሚቀበል ገልጿል።  

የዕጩ መልማይ ኮሚቴው ይህን ያስታወቀው፤ የጥቆማ አቀራረብ ሂደቱን አስመልክቶ ዛሬ አርብ ጥቅምት 10፤ 2016 በሰጠው መግለጫ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በገዛ ፍቃዳቸው የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት ኃላፊነታቸውን በለቀቁት ብርቱካን ሚደቅሳ ምትክ ተተኪ ለመሾም ያስችላቸው ዘንድ መልማይ ኮሚቴ መሰየማቸውን ይፋ የተደረገው ከሶስት ቀናት በፊት ነበር። 

በፌደራልና በክልል የምርጫ ክልሎች “ነጻና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኝነት የማካሄድ ኃላፊነት” ለተጣለበት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ የስራ አመራር ቦርድ አባላትን ለፓርላማ አቅርበው የማሾም ስልጣን በሕገ መንግስቱ የተሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው። በ2011 ዓ.ም. የጸደቀው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋሙን የስራ አመራር ቦርድ አባላትን የሚመለምል “ገለልተኛ ኮሚቴ” ማቋቋም እንዳለባቸው ደንግጓል።

ኮሚቴው ከኢትዮጵያ ሃይማኖት ጉባኤ፣ ከኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ ከኢትዮጵያ ሰራተኞች ኮንፌዴሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ማህበራት ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ከሲቪል ማህበራት እና ከሃገር ሽማግሌዎች የሚመረጡ ስምንት አባላት ሊኖሩት እንደሚገባ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። ይህንን አዋጅ መሰረት በማድረግ ባለፈው አርብ ጥቅምት 23 በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተሰየመው ኮሚቴ፤ የውስጥ አሰራር መመሪያ እና የድርጊት የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ ወደ ስራ መግባቱን ሰብሳቢው ቀሲስ ታጋይ ታደለ በዛሬው መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅን መሰረት ያደረገ “የዕጩዎች መመልመያ መስፈርት” በኮሚቴው መዘጋጀቱንም ሰብሳቢው ለጋዜጠኞች ገልጸዋል። ለምርጫ ቦርድ የስራ አመራር ቦርድ አባል የሚሆን ግለሰብ፤ በዜግነት ኢትዮጵያዊ የሆነ፣ የማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆነ፣ መልካም ስነ ምግባር እና ሰብዕና ያለው እንዲሁም የተሰጠውን ኃላፊነት ለመሸከም የሚያስችል ከፍተኛ የአመራር ብቃት ያለው ሊሆን እንደሚገባ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። 

ከዚህም በተጨማሪ ለቦርድ አባልነት የሚታጭ ሰው “ከምርጫ ጉዳዮች ተያያዥነት ባላቸው በተለይም በሕግ፣ በፖለቲካል ሳይንስ፣ በሕዝብ አስተዳደር፣ በስታቲስቲክስ፣ በኢንፎሮሜሽን ቴክኖሎጂ እና ሌሎች ተዛማጅነት ባላቸው ዘርፎች ከፍተኛ ሙያዊ ብቃት ያለው” መሆን እንዳለበት በአዋጁ ላይ ተቀምጧል። የዕጩ መልማይ ኮሚቴው በአዋጁ ላይ ከተዘረዘሩት በተጨማሪ ዕጩው የቦርድ ሰብሳቢነቱን ለመቀበል ፍቃደኛነቱ፣ የሚሰጠውን ኃላፊነት በተዓማኒነት የሚወጣ መሆኑ እንዲሁም ከሌሎች ጋር የመስራት ክህሎትን በመስፈርትነት ማዘጋጀቱ ተገልጿል።   

የኮሚቴው ሰብሳቢ፤ ጠቋሚዎች ለዕጩነት የሚጠቁሟቸው ግለሰቦች እነዚህን መስፈርቶች “በሚገባ ማሟላታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው” ሲሉ በዛሬው መግለጫ ላይ አሳስበዋል። ጥቆማ አቅራቢዎች ኮሚቴው ያዘጋጀውን ቅጽ (ፎርም) በመጠቀም፤ የዕጩዎችን ማንነት እና ሌሎችንም መገለጫዎቻቸውን በዝርዝር በመሙላት፤ በኢ-ሜይል፣ በዋትስ አፕ፣ በቴሌግራም አሊያም በፖስታ መላክ እንደሚችሉም ገልጸዋል። 

የዕጩ ጥቆማዎቻቸውን በአካል ማቅረብ የሚሹ፤ በአዲስ አበባ አራት ኪሎ አካባቢ በሚገኘው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንግዳ መቀበያ ቢሮ በተዘጋጀ ዝግ ሳጥን ውስጥ የጥቆማ ወረቀታቸውን ማስገባት እንደሚችሉ ሰብሳቢው አመልክተዋል። የጥቆማ ማቅረቢያው የመጨረሻ ዕለት ሐሙስ ህዳር 13፤ 2016 ከቀኑ 11 ሰዓት ከ30 መሆኑን የዕጩ መልማይ ኮሚቴው በዛሬው መግለጫው ይፋ አድርጓል።

መግለጫውን በታደሙ ጋዜጠኞች ከቀረቡ ጥያቄዎች አንዱ፤ በኢትዮጵያ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ጥቆማ የሚቀርብበት የጊዜ ገደብ  “አላጠረም ወይ?” የሚል ነበር። ቀሲስ ታጋይ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ “ከስራው አስፈላጊነት አንጻር፤ እንደውም እኛ ሰፊ ጊዜ ነው የሰጠነው” ብለዋል። “በብዙ ክልሎቻችን ምርጫው ተሟልቶ ያልተካሄደ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ምክንያት እየተጓተተ መሆኑን እንረዳለን። በዚህ የተነሳ ይሄ ኮሚቴም ባጠረ ጊዜ ስራውን ሰርቶ ማስረከብ እንዳለበት ነው የተነጋገርነው” ሲሉም አብራርተዋል።

ከቀነ ገደቡ መጠናቀቅ በኋላ፤ ኮሚቴው ከጠቋሚዎች በሚቀርቡለት ዕጩዎች ላይ “እስከ ሶስት ጊዜ የማጣራት ስራ” እንደሚሰራ ሰብሳቢው አስረድተዋል። ኮሚቴው በስተመጨረሻ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያስተላልፋቸው ዕጩዎች ብዛት ሁለት እንደሚሆንም ገልጸዋል። የመጨረሻዎቹ ዕጩዎች ብዛት ሁለት እንዲሆን የተደረገው፤ በምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት መሆኑን ከኮሚቴው አባላት አንዷ የሆኑት ርግበ ገብረሃዋርያ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። 

የምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ “ኮሚቴው የሚያዘጋጀው የዕጩዎች ዝርዝር ምልመላው በሚካሄድበት ወቅት በስራ አመራር ቦርዱ ካሉት ክፍት ቦታዎች ቁጥር እጥፍ መሆን ይኖርበታል” ይላል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፤ ሰብሳቢ እና ምክትል ሰብሳቢን ጨምሮ “በሙሉ ጊዜ የሚያገለግሉ” አምስት አባላት እንደሚኖሩት በአዋጅ ተደንግጓል። የምርጫ ቦርድ የስራ አመራር ቦርድን ለአራት ዓመት ከመንፈቅ በሰብሳቢነት የመሩት ብርቱካን ሚደቅሳ ከነሐሴ 1፤ 2015 ጀምሮ “በጤና ምክንያት” ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ የቦርዱ አባላት ብዛት ተጓድሎ ቆይቷል።

ምርጫ ቦርድ በ2011 ዓ.ም. በአዲስ መልክ ከተዋቀረ በኋላ በተቋቋመው የስራ አመራር ቦርድ፤ ተመሳሳይ መጓደል ከዚህ ቀደምም አጋጥሟል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰኔ 2011 ዓ.ም. ሹመታቸው ከጸደቀላቸው አምስት የቦርድ አባላት ውስጥ አንዱ የነበሩት ዶ/ር ጌታሁን ካሳ፤ ከአንድ ዓመት በኋላ ከኃላፊነታቸው በገዛ ፍቃዳቸው መልቀቃቸው ይታወሳል። የእርሳቸው ተተኪ የሆኑት ፍቅሬ ገብረ ህይወት በፓርላማ ሹመታቸው የጸደቀው ከአንድ ወር በኋላ እንደነበር አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)