ኢትዮጵያ ወደብ ለማግኘት በምታደርገው ግፊት ወደ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ ወይም በሌሎች ጎረቤቶቿ ላይ “አንድ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት” እንደሌላት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ዛሬ ማክሰኞ ህዳር 4፤ 2016 በሰጡት ማብራሪያ “የማንንም ሉዓላዊነት የመንካት ፍላጎት የለንም፤ ማንንም የመውረር ፍላጎት የለንም” ሲሉ ተደምጠዋል።
አብይ በዛሬው የፓርላማ ቆይታቸው ማጠቃለያ ላይ ባለፉት ሳምንታት በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል ሌላ ጦርነት ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ስጋት ባጫረው የወደብ ጥያቄ ላይ ዘለግ ያለ ማብራሪያ አቅርበዋል። ወደብን በተመለከተ “ብዙ አይነት ንግግሮች፣ ትንበያዎች፣ ሴራዎች፣ ትንተናዎች ተደርገዋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ ጎረቤቶች እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ “ሊገነዘቡ ይገባል” ያሉትን የመንግስታቸውን “እውነተኛ ፍላጎት እና ችግር” ዘርዘር አድርገው አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ማብራሪያቸው “ኢትዮጵያ ወደብ ማግኘት አለባት” የሚል አቋማቸው በድጋሚ በጉልህ ተንጸባርቋል። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያላት “የህዝብ ቁጥር እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት”፤ አብይ ለወደብ አስፈላጊነት ያቀረቧቸው ገፊ ምክንያቶች ናቸው። በሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 150 ሚሊዮን እንደሚደርስ፤ ኢኮኖሚዋም እያደገ እንደሚሄድ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ጣጣ እንዳያመጣ እና ልጆቻችንን እንዳያባላ አሁን መፍትሔ እናበጅለት” ሲሉ ለፓርላማ አባላቱ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ጉዳዩን “በከፋ መንገድ” ሊመለከቱ እንደማይገባ ደጋግመው የተናገሩት አብይ፤ በጉዳዩ ምክንያት መንግስታቸው ወደ ግጭት የመግባት ፍላጎት እንደሌለው አስረግጠው ተናግረዋል። “እኛ ግጭት አላልንም። ግጭት እንዳይመጣ እንነጋገር ነው ያልንው” ሲሉ ተደምጠዋል። “ኢትዮጵያ፤ ወደ ኤርትራ፣ ወደ ሶማሊያ፣ ወደ ጅቡቲ፣ ወደ ኬንያ ወይም ወደ ሌሎች ጎረቤቶቻችን አንድ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የላትም። በሉዓላዊነታቸው ጥያቄ የላትም” የሚል ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
“በአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ አለን። እሱን እንጋራ እና ውሀ አጋሩን። በአፍሪካ አንደኛውን ግድብ ገንብተናል። እሱን እንጋራ እና አጋሩን፣ እናንተም የኢኮኖሚ ችግር አለባችሁ እኛም ችግር አለብን ተያይዘን እንደግ ነው ያልንው” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስታቸው ምርጫ ምን እንደሆነ ገልጸዋል። ችግሩ “በውይይት” እና “በንግግር” ካልተፈታ ግን “ምን ሊያጋጥም እንደሚችል መገመት አይቻልም” ሲሉም ማስጠንቀቂያ አዘል ንግግር አስደምጠዋል።
ኢትዮጵያ በጅቡቲ ወደብ ላይ ጥገኛ መሆኗን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ በአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካ መበላሸት ሳቢያ “ትላልቆቹ ሀገራት አንዳንዴ ሲጨቃጨቁ፤ በሚዲያ ሲጣሉ እኛ እንደነግጣለን” ሲሉ ተደምጠዋል። “የጅቡቲ ሕዝብ እና መንግስት ወንድማችን ነው፤ ችግር የለም” ያሉት አብይ፤ “ትላልቆቹ ቢጣሉ ጅቡቲ ላይ [የጦር] ካምፕ ስላላቸው፤ ድንገት ቢታኮሱ የእኛ ቦቴዎች ነዳጅ ሊያመጡ አይችሉም” በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

“ሰሞኑን ከየመን ሚሳይል ይተኮሳል፤ UAV ይተኮሳል ይባላል። በየመን እና በጅቡቲ መካከል ያለው ርቀት 28፣ 29፣ 30 ኪሎ ሜትር ነው። የባህሩ ስፋት በጣም ቅርብ ነው” ያሉት አብይ፤ እነዚያ ኃይሎች እነዚህን ካምፖች ኢላማ አድርገው ጥቃት ቢፈጽሙ ኢትዮጵያ ወደቡን ለመጠቀም እንደሚያዳግታት አስገንዝበዋል። “ይኼ የጅቡቲ መንግስት፣ ህዝብ የሚያደርግብን ጫና ሳይሆን የጂኦ ፖለቲካው መሳከር እና አንዳንድ ኃይሎች በርቀት መተኮስ፤ በርቀት መግደል አቅም ስለፈጠሩ፤ እኛ ጭንቀታችን ያ ነገር ቢያጋጥም 120 ሚሊዮን ህዝብ ምን እናደርገዋለን ነው” ሲሉም በአካባቢው ያለው የፖለቲካ ትኩሳት ለኢትዮጵያ ዳፋ እንደሚሆን አብራርተዋል።
የቀይ ባህርን በተመለከተ ኢትዮጵያ የያዘችው አቋም አዲስ እንዳልሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ “የባህር ኃይል ስንገነባ እኮ ሌላ አጀንዳ የለንም። ባህር እንፈልጋለን ነው” ሲሉ በጉዳዩ ላይ ጥያቄ ለሚያነሱ ወገኖች መልስ ሰጥተዋል። “ቀይ ባህር ያስፈልገናል” የማይል ዓለም አለመኖሩን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “ምነው እኛ ስንፈልገው ነውር ሆነ?” ሲሉም ጠይቀዋል። “ያስፈልገኛል ብሎ የማይረባረብ ዓለም በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ደሀ ናችሁ እና አያስፈልጋችሁም ካልሆነ በስተቀር፤ ‘ቀይ ባህር ያስፈልጋል’ ብሎ የማይጠብቅ፣ ‘የባህር ላይ ውንብድና አደጋ ነው’ ብሎ የማይጠብቅ ዓለም የለም” ያሉት አብይ፤ “ለእኛ ደግሞ ብቸኛ መተንፈሻችን ነው” ሲሉ ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄን ማንሳቷ “የኤርትራን ሉዓላዊነት ለመዳፈር ነው” የሚሉ ወገኖች መኖራቸውን በማብራሪያቸው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “እኛ የህዳሴ ግድብን የሰራነው የሱዳንን ሉዓላዊነት ለመዳፈር ነው እንዴ?” በሚል ጥያቄ የተዘዋዋሪ መልስ ሰጥተዋል። ኢትዮጵያ ግድቡን የምትሰራው “ኢነርጂ ለማምረት፣ ውሃውን ለወንድሞቻችን ለክተን ዓመቱን በሙሉ ለመላክ ነው። ህዳሴ ለግብጽም፣ ለሱዳንም፣ ለኢትዮጵያም ሲሳይ እንዲሆን ነው የምንፈልገው እንጂ እነሱ እንዲጎዱ አንፈልግም” ያሉት አብይ “ቀይ ባህርም እንደዚሁ ነው” የሚል አመክንዮ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ የወደብ ተጠቃሚነት ጥያቄ ምላሽ ካላገኘ ወደ ሳዑዲ አረቢያ፣ ታንዛንያ እና ደቡብ አፍሪካን የመሳሰሉ ሀገሮች የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር እንደሚችል ያስጠነቀቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “ከእኛ በላይ መጨነቅ ያለባቸው ወንድሞቻችን ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ 120 ሚሊዮን ሕዝብ እንዳላት በማብራሪያቸው ደግመው ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ “ለምሳሌ አምስት ሚሊዮን ኤርትራ፣ አምስት ሚሊዮን ጅቡቲ፣ አምስት ሚሊዮን ሶማሌ ቢሄድ መሸከም ይቻላል? ቀላል ነው?” ሲሉ ጠይቀው “አይቻልም” የሚል መልስ ራሳቸው ሰጥተዋል።
የወደብ ጥያቄው “በቢዝነስ ህግ እንዲፈታ” እና ሀገሪቱም “የማያወላዳ ምርጫ” እንድታገኝ እንደሚፈልጉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መንግስታቸው በጉዳዩ ላይ ከአሜሪካ፣ ቻይና፣ አውሮፓ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ እንደሆነም ጠቁመዋል። እነዚህ ሀገራት “ከህግ ውጪ፣ ከቢዝነስ ውጪ፣ ሰላም ከሚያረጋግጥ መንገድ ውጪ ኢትዮጵያ ያልተገባ ጥያቄ ጠይቃ ከሆነ ያነጋግሩን እና ‘እረፉ’ ይበሉን፤ እንተወዋለን” ሲሉ አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው በማብራሪያቸው ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር ወደ ጦርነት ትገባለች የሚል ስጋት መንግስታቸው እንደሌለው ለፓርላማ አባላቱ አስረድተዋል። “ከጎረቤቶቻችን የሆነ ኃይል ተነስቶ ኢትዮጵያን ሊመታ ይችላል የሚል ስጋት የለብንም” ያሉት አብይ ኢትዮጵያን “የመታደግ ከበቂ በላይ አቅም አለን” የሚል ማስተማመኛ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)