በተስፋለም ወልደየስ
በኢትዮጵያ በከፍተኛ ወርቅ አምራችነት ከተመዘገቡ 13 ኩባንያዎች ውስጥ፤ በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ምርት ያመረቱት ሁለቱ ብቻ መሆናቸውን የማዕድን ሚኒስትሩ አቶ ሀብታሙ ተገኝ ተናገሩ። ቀሪዎቹ ኩባንያዎች በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የስራ አፈጻጸማቸውን የማያስተካክሉ ከሆነ፤ የማዕድን ሚኒስቴር በፍቃዳቸው ላይ “ተገቢውን እርምጃ” እንደሚወስድም አስጠንቅቀዋል።
ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው ወርቅ፣ ታንታለም፣ ሊትየም፣ የከበሩ ድንጋዮች እና ሌሎች የማዕድን ውጤቶች ለማግኘት ያቀደችው የውጭ ምንዛሬ 514 ሚሊዮን ዶላር ነው። ሀገሪቱ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከወርቅ ሽያጭ ለማስገባት በእቅድ የያዘችው 112.8 ሚሊዮን ዶላር ቢሆንም፤ ከውጥኗ ማሳካት የቻለችው ግን “ትንሽ” መሆኑ ዛሬ ሰኞ ህዳር 17፤ 2016 በተካሄደ የተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ተገልጿል።
ይኸው ቋሚ ኮሚቴ ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ባካሄደው ስብሰባ ላይ፤ የኢትዮጵያ የወርቅ ምርት በሁለት ዓመታት ውስጥ በአምስት እጥፍ ሊያድግ እንደሚችል የማዕድን ሚኒስትሩ ተናግረው ነበር። ይሁንና አቶ ሀብታሙ ዛሬ የመስሪያ ቤታቸውን የሶስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለማቅረብ ወደ ተወካዮች ምክር ቤት ሲመለሱ፤ በዘንድሮው ሩብ ዓመት የተገኘው የወርቅ ሽያጭ ገቢ “አጥጋቢ አይደለም” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ለውጭ ገበያ ያቀረበችው የወርቅ መጠን ከሌላው ጊዜ ጋር ሲነጻጸር “በከፍተኛ ሁኔታ” መቀነሱን ብሔራዊ ባንክ በወቅቱ አስታውቆ ነበር። ኢትዮጵያ በ2014 ዓ.ም. 11 ወራት ውስጥ ካመረተችው 8.1 ቶን ወርቅ ውስጥ ያገኘችው ገቢ 513 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል። በኢትዮጵያ ፍቃድ አግኝተው ከሚንቀሳቀሱ 13 የማዕድን ኩባንያዎች፤ በዓመት 17 ቶን ወርቅ መመረት እንደሚችል አቶ ሀብታሙ በዛሬው የቋሚ ኮሚቴ ስብስባ ላይ ተናግረዋል።
በከፍተኛ ወርቅ አምራቾች ደረጃ በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለማምረት ታቅዶ የነበረው 996.1 ኪሎ ግራም ወርቅ እንደነበር የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ አጠቃላይ አፈጻጸሙ በመቶኛ ሲሰላ 72.2 በመቶ መሆኑን ገልጸዋል። ከወርቅ ምርት ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ሚድሮክ ኩባንያ መሆኑን እና ስቴላ የተሰኘው ኩባንያ በተወሰነ መጠን እያመረተ እንደሚገኝ አቶ ሀብታሙ በዛሬው ሪፖርታቸው አመልክተዋል።
ምርት ከማያመርቱ ኩባንያዎች አብዛኞቹ “በዝግጅት ላይ” መሆናቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ አንዳንዶቹ ደግሞ “ደካማ” መሆናቸውን አስታውቀዋል። የኩባንያዎቹን የስራ አፈጻጸም በተመለከተ ከራሳቸው ከድርጅቶቹ ጋር ግምገማ በተደረገበት ወቅት፤ የተወሰኑቱ በየአባባቢያቸው ባለ የመሰረተ ልማት ችግር ምክንያት በክረምት ወቅት ወርቅ ለማምረት ተቸግረው እንደነበር ማንሳታቸውን ሚኒስትሩ ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አብራርተዋል።
ለወርቅ አምራች ኩባንያዎች ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት ፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር ሙሉ ለሙሉ አለመቀረፉም ሌላው በምክንያትነት የተነሳ ጉዳይ መሆኑንም አቶ ሀብታሙ አስታውሰዋል። በአሁኑ ወቅት ወርቅ በማምረት ላይ ከሚገኙት ሚድሮክ እና ስቴላ ኩባንያዎች ውጪ ሌሎቹ ኩባንያዎች በእርግጥም የሚገኙት “የጸጥታ ችግር ባለባቸው” አካባቢዎች መሆናቸውን የማዕድን ሚኒስትሩ አምነዋል።
“እንዳለመታደል ያው ሪሶርሱም ያለው በዚያ አካባቢ ነው። ግጭትም የሚስተዋለው በእነዚህ አካባቢ ነው። በሌሎች በተለያዩ ሽፋኖች ሪሶርሱን የመሻማት ፍላጎትም እንደሆነ ያሳያል” ሲሉ የወርቅ ማዕድን በሚገኝባቸው አካባቢዎች አላባራ ያለው ግጭት መንስኤ አንዱ ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚችል አቶ ሀብታሙ ጥቆማ ሰጥተዋል።
ሆኖም በአንዳንድ ቦታዎች ያለው ሁኔታ እየተሻሻለ በመምጣቱ፤ ኩባንያዎቹ በሚቀጥለው መንፈቅ ዓመት የስራ አፈጻጸማቸውን መቀየር እንዳለባቸው ሚኒስትሩ አሳስበዋል። ወርቅ አምራች ኩባንያዎቹ ይህን የማያደርጉ ከሆነ ግን በፌደራል መንግስት በተሰጣቸው ፍቃድ ላይ “አስፈላጊውን እርምጃ ወደ መውሰድ የምንገባ ይሆናል” ሲሉ የማዕድን ሚኒስትሩ አስጠንቅቀዋል።
የፌደራል መንግስቱ በሚያስተዳድራቸው ፍቃዶች ስራቸውን የሚያከናውኑ ኩባንያዎች ችግሮች ቢታዩባቸውም፤ በሩብ ዓመቱ በወርቅ ምርት ረገድ “ትንሽ ሻል ያለ ነገር ያላቸው” እነርሱ መሆናቸውን አቶ ሀብታሙ አልሸሸጉም። በዘንድሮው የበጀት ዓመት ሶስት ወራት ውስጥ ከተሰበሰበው ወርቅ ውስጥ፤ ከክልሎች ፍቃድ አውጥተው በሚንቀሳቀሱ በአነስተኛ እና ባህላዊ አምራቾች የተመረተው 22 በመቶ መሆኑን ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላቱ አስታውቀዋል።
“ትልቁ ምርት ሲመረት የነበረው፣ እጥፍ ምርት ሲመረት የነበረው ከባህላዊ ማዕድን አምራቾች ነው። ይሄ የክልሎች ኃላፊነት ነው። ወዴትም ልንወስደው የምንችለው ነገር አይደለም። ባለፍቃዶቹ ራሳቸው ናቸው ፍቃዱን ማስተዳደር ያለባቸው” ሲሉ አቶ ሀብታሙ አጽንኦት ሰጥተዋል። በኢትዮጵያ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት የወርቅ ማዕድን የሚገኝባቸው አካባቢዎች የሚገኙት በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ትግራይ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልሎች ውስጥ ነው።
ባለፉት ዓመታት በባህላዊ ወርቅ አምራቾች ረገድ ከፍተኛውን መጠን ሲያቀርብ የቆየው የኦሮሚያ ክልል እንደነበር የገለጹት አቶ ሀብታሙ፤ በዚህ ሩብ ዓመት ግን “የሚፈለገውን አላመጣም” ሲሉ ተችተዋል። “[ኦሮሚያ ክልል] በርካታ የሪፎርም እና የማስተካከያ ስራዎች እየሰሩ እንደሆነ ነው ሪፖርት ያለን። ነገር ግን አፈጻጸሙ በጣም ደካማ ነው” ሲሉ የማዕድን ሚኒስትሩ አክለዋል።
በ2016 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከሌሎች ጋር ሲነጻጸር “ጥሩ ሊባል የሚችል” የወርቅ ምርት የነበረው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሆኑን አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል። የጋምቤላ ክልልም እንዲሁ በሶስቱ ወራት ጥሩ አፈጻጸም ማስመዝገቡን አመልክተዋል። በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት በነበሩ ዓመታት ከከፍተኛ ወርቅ አምራቾች አንዱ የነበረው የትግራይ ክልል ጉዳይም በሚኒስትሩ ተነስቷል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር “ሙሉ ለሙሉ ቦታ ላይ ሆኖ ነገሮችን እያስተካከለ” መሆኑን የገለጹት አቶ ሀብታሙ፤ በዚህም ምክንያት “ህገ ወጥ ኮንትሮባንዲስቶች እና ሌሎች” ሲሉ የጠሯቸው አካላት የክልሉን የወርቅ ምርት ወደ “ሌላ አካባቢ ሲያወጡ” መቆየታቸውን አስረድተዋል። የትግራይ ክልል የወርቅ ምርት ገና “ወደ ማዕከላዊ ገበያ አልመጣም” ያሉት ሚኒስትሩ፤ ሆኖም ከዚህ ወር ጀምሮ ወደ ብሔራዊ ባንክ መምጣት ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)