ትምህርት ሚኒስቴር በተማሪዎች የወሊድ ፈቃድ ላይ የጣለውን ገደብ “በፍጥነት” እንዲያስተካክል ጥሪ ቀረበ

ትምህርት ሚኒስቴር በቅርቡ ባወጣው ረቂቅ መመሪያ፤ የተማሪዎችን የወሊድ ፍቃድ በተመለከተ በጣለው ገደብ ላይ “በፍጥነት ማስተካከያ እንዲያደርግ” በሴቶች መብት ዙሪያ የሚሰሩ 10 የሲቪክ ማህብረሰብ ድርጅቶች ጠየቁ። ድርጅቶቹ መመሪያው “የሴቶችን መሠረታዊ የመማር መብቶች በግልጽ የሚነፍግ ነው” ሲሉ ተቃውመውታል።

ተቃውሞ የቀረበበት ገደብን የያዘው ረቂቅ መመሪያ “የአጠቃላይ ትምህርት የተማሪዎች ምዝና እና ከክፍል ወደ ክፍል የሚደረግ ዝውውርን” በተመለከተ በመስከረም 2016 የተዘጋጀ ነው። ትምህርት ሚኒስቴር መመሪያውን ያዘጋጀው “ተማሪዎች የጨበጡትን እውቀትና ክህሎት እንዲሁም ያጎለበቱትን አመለካከት ወጥ በሆነ መንገድ በመመዘን፤ ከክፍል ወደ ክፍል የሚያደርጉትን ዝውውር ለማከናወን እንዲቻል” መሆኑን በሰነዱ መግቢያ ላይ አስፍሯል። 

በስድስት ክፍሎች በተከፋፈለው ረቂቅ መመሪያ ውስጥ ከተካተቱ ጉዳዮች መካከል ስለተማሪዎች ትምህርት “ማቋረጥ” የሚመለከተው ይገኝበታል። በረቂቅ መመሪያው መሰረት፤ አንድ ተማሪ በአንድ-ወሰነ ትምህርት ለ12 ቀናት ከትምህርት ገበታው ከቀረ “ትምህርቱን እንዲቀጥል አይፈቀድለትም”። 

አንድ ተማሪ በወሊድ ምክንያት 15 ተከታታይ ቀናት ካረፈች በኋላ “ትምህርቷን መቀጠል እንደምትችል” የሚያስቀምጠው ረቂቅ መመሪያው፤ ሆኖም ከእነዚህ ቀናት በኋላ “ከትምህርት ገበታዋ ከቀረች ከዘመኑ ትምህርት ትታገዳለች” ሲል ደንግጓል። በረቂቅ መመሪያው የተካተተውን ይህን እርምጃ፤ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኀበርን ጨምሮ በሴቶች መብት ዙሪያ የሚሰሩ 10 የሲቪክ ማህብረሰብ ድርጅቶች “ኢ-ፍትሃዊ” ሲሉ ተቃውመውታል። 

ድርጅቶቹ  ዛሬ ሐሙስ ህዳር 20፤ 2016 በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ረቂቅ መመሪያው “ትምህርታቸውን ለሚከታተሉ ሴቶች የወሊድ ፍቃድ መብትን በእጅጉ የሚገድብ ነው” ሲሉ ነቅፈውታል። ረቂቅ መመሪያው “በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት የተደነገጉትን አወንታዊ የድርጊት ድንጋጌዎች የሚንድና የሴቶችን መሠረታዊ የመማር መብቶች በግልጽ የሚነፍግ ነው” ሲሉም ኮንነውታል። 

“ረቂቅ መመሪያው ለሴቶች ሌሎች አማራጮችን ከመፍጠር ይልቅ እንዳይበቁና በህብረተሰቡ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መሳተፍ እንዳይችሉ የሚያደርግ ቀጥተኛ ጥቃት ነው” ሲሉ በጋራ መግለጫቸው ያስታወቁት ድርጅቶቹ፤ ትምህርት ሚኒስቴር “ጉዳዩን እንደገና እንዲያጤነው” ጠይቀዋል። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በመመሪያው ላይ “በፍጥነት ማስተካከያ እንዲያደርግም” ጥሪያቸውን አቅርበዋል። 

ጥሪውን ካቀረቡ 10 ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ ሴቶች ማኀበራት ቅንጅት፣ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል፣ የኢትዮጵያ ሴቶች የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጥምረት እና የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ተሟጋች ይገኙበታል። ሴታዊት ንቅናቄ፣ ሴቶች ይችላሉ፣ ሲሃ ኔትወርክ፣ ሴቭድ ቱ ሴቭ እንዲሁም የሴቶች ማረፊያ ልማት ማህበር ሌሎቹ ጥሪውን ያቀረቡ የሲቪክ ማህብረሰብ ድርጅቶች ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)