አዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 36.2 ቢሊዮን ብር የተሻሻለ በጀት አጸደቀ 

በተስፋለም ወልደየስ

ባለፈው ዓመት ነሐሴ በይፋ የተመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ በስሩ ያሉ መዋቅሮቹ ያደረጉትን የአደረጃጀት ለውጥ ታሳቢ ያደረገ የተሻሻለ በጀት አጸደቀ። የክልሉ ምክር ቤት ዛሬ ሐሙስ ታህሳስ 4 ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው፤ ለክልሉ መንግስት የ2016 እቅድ ማስፈጸሚያ የሚሆን 36.2 ቢሊዮን ብር በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በህዝበ ውሳኔ ከቀድሞው የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችን እና ህዝቦች ክልል በተነጠለበት ወቅት፤ ለነባሩ ክልል ተመድቦ ከነበረው በጀት ውስጥ 54.24 በመቶ ድርሻ እንዲያገኝ ከስምምነት ተደርሶ ነበር። በዚህ ክፍፍል መሰረት ክልሉ 11 ቢሊዮን ብር ያህል በጀት ይዞ ይፋዊ ምስረታውን አከናውኗል።

በነባሩ ክልል የተደረገው የድርሻ ክፍፍል ከዚህ ቀድም የነበሩ መዋቅሮችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ እና የአዲሱ ክልል ማዕከል ድርሻ በግልጽ አለመለየቱ፤ የበጀት ማስተካከያውን ለማድረግ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸው በዛሬው የምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪ በአዲሱ ክልል ስር ያሉ የተዋቀሩ አዲስ ዞኖች የገቢ እቅዳቸውን ለማሻሻል መፈለጋቸው እና ነባር ዞኖች በበኩላቸው “የገቢ አቅማቸውን አሟጠው ለመጠቀም” በመወሰናቸው የበጀት ማስተካከያው መዘጋጀቱ ተነግሯል። 

በአዲሱ ክልል ስር ያሉ መዋቅሮች፤ ለመሰብሰብ ባቀዱት ገቢ ላይ ባደረጉት ማሻሻያ ቀድሞ ከተያዘው 11 ቢሊዮን ብር የገንዘብ መጠን 5.5 ቢሊዮን ብር ጭማሪ መምጣቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ ለክልሉ ምክር ቤት አባላት አብራርተዋል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ካሉበት “ብዙ ችግሮች፣ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች፣ የመልማት ፍላጎት” እና በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ካለው “የዋጋ ግሽበት” አንጻር “ገቢን አሟጥጦ መሰብሰብ አስፈላጊ” በመሆኑ የበጀት ማስተካከያው ለምክር ቤቱ መቅረቡንም ገልጸዋል።

ፌዴሬሽኑን በመቀላቀል አስራ ሁለተኛ ክልል የሆነው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከዚህ ቀደም ከነባሩ ደቡብ ተነጥሎ የራሱን ክልል እንደመሰረተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሁሉ ለመንግስት ሰራተኞች በወቅቱ ደመወዝ የመክፈል ችግር ገጥሞታል። ይሄንኑ ጉዳይ በዛሬው መደበኛ ጉባኤ ላይ በተደጋጋሚ ያነሱት የክልሉ ምክር ቤት አባላት፤ የክልሉ መንግስት ለችግሩ መፍትሔ እንዲያበጅ ጠይቀዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ለጥያቄዎቹ በሰጡት ምላሽ ችግሩ መኖሩን አምነዋል። “መምህራን፣ የጤና ባለሙያዎች የደመወዝ ክፍ ሊቋረጥ ወይንም ደግሞ ጊዜ ሊያልፍባቸው አይገባም” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ደመወዝ በጊዜ እንዳይከፈል ምክንያት የሆነው በተለይ “ከዕዳ ጋር በተያያዘ ያለው ጉዳይ” መሆኑን ገልጸዋል። 

“እንዴት ነው ከዕዳ ነጻ መሆን የምንችለው? የቱ ጋር ነው የተበላሸው? የቱ ጋር ነው የተቆለፈው?” ሲሉ የጠየቁት አቶ ጥላሁን፤ ህዝብን በማስተባበር በሚደረግ የገንዘብ ማሰባሰብ ከችግሩ መውጣት እንደሚቻል አመልክተዋል። “ባለፈው 15 ቀን ነው የክልል የምስረታ ድጋፍ ገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ የጀመርነው። የክልሉ መንግስት በ15 ቀን ውስጥ 585 ሚሊዮን ብር ነው ከህዝቡ የሰበሰበው። ሲሰበስብ ብዙ ነው። ደመወዝም ሲሰበሰብ ብዙ ነው” ሲሉ ለክልሉ ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።

በክልሉ ያሉ ወረዳዎች ወይም ተቋማት “የውስጥ አቅማቸውን አሟጥጠው በመጠቀም” እና “ገቢ በማሰባሰብ”፤ አሁን እያገለገሉ ላሉ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ ለመክፈል ስራዎችን መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል። የደመወዝ ክፍያንም ሆነ የካፒታል ፕሮጀክት ስራዎችን ለመስራት መፍትሔው “በእጃችን ያለውን ጸጋ ጠጋ ብለን [መመልከት ነው]” ሲሉም ተደምጠዋል።  

በይፋ ከተመሰረተ አራት ወራት ያለፉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ “በግብር አስተዳደር እና አሰባሰብ ላይ የሚታዩ ማነቆዎችን በመፍታት” ገቢውን ማሳደግ እንደሚጠበቅበትም አቶ ጥላሁን አስገንዝበዋል። የአዳዲስ መዋቅሮችን ጥያቄን ለጊዜው ጋብ በማድረግ፤ ክልሉ ሲቋቋም በተፈጠሩት የወረዳ እና የዞን አደረጃጀቶች “ወደ ስራ መግባት” እንደሚገባም አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)