በተስፋለም ወልደየስ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከሚገኘው ዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዝ ባስከተለው ጎርፍ የተፈናቀሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች፤ የዕለት አስቸኳይ እርዳታ በአግባቡ እየደረሳቸው ባለመሆኑ ችግር ላይ መውደቃቸውን አንድ የአካባቢው ተመራጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በክልሉ ምክር ቤት የዳሰነች ልዩ ምርጫ ክልል ተወካይ አቶ ከበደ ሳህሌ፤ የአካባቢው አርብቶ አደሮች ለመፈናቀላቸው ዋነኛው ተጠያቂ “መንግስት ነው” ሲሉ ተችተዋል።
በደቡብ ኦሞ ዞን ስር ካሉ የአስተዳደር መዋቅሮች አንዱ የሆነው የዳሰነች ወረዳ፤ በውስጡ 16 ደሴቶችን የያዘ እና በ40 ቀበሌዎች የተከፋፈለ ነው። በየዓመቱ በክረምት ወቅት የኦሞ ወንዝ ሙላትን ተከትሎ በሚከሰተው ጎርፍ፤ በርካታ ነዋሪዎች ቀያቸውን ለወራት ጥለው ሲሰደዱ ቆይተዋል።
ሆኖም ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ በጎርፍ የሚጠቁ አካባቢዎች ብዛት እና ድግግሞሹ እየጨመረ፣ የተፈናቃዮች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ በመምጣቱ የዳሰነች ወረዳ ነዋሪዎች ለችግር መዳረጋቸውን አቶ ከበደ ይናገራሉ። በሃያ ስምንት ቀበሌዎች የሚኖሩ የዳሰነች ወረዳ ነዋሪዎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት የሆኑት፤ በኦሞ ወንዝ ላይ የተገነቡት የግልገል ጊቤ አንድ፣ ሁለት፣ ሶስት እና ኮይሻ ግድቦች መሆናቸውን የአካባቢው ተወካይ ያስረዳሉ።
ከዚህ ቀደም በነበሩት ዓመታት በሚከሰተው የውሃ መጥለቅለቅ፤ በኦሞ ወንዝ ዳርቻ እና በደሴቶች ላይ የሚኖሩ አርብቶ አደሮች የሚፈናቀሉት ከሐምሌ እስከ መስከረም አጋማሽ ባለው ጊዜ እንደነበር አቶ ከበደ ያስታውሳሉ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በግድቦቹ ምክንያት “አመቱን ሙሉ ውሃ ተኝቶ የሚቆይ በመሆኑ” እና የአርብቶ አደሮቹ ዋነኛ የኑሮ መደገፊያ የሆኑት የቀንድ ከብቶች የሚመገቡት ሳር በማጣታቸው፤ የምግብ እጥረት መከሰቱን ያብራራሉ።
“አርብቶ አደሮቹ አሁን የዕለት አስቸኳይ እርዳታ ነው እየተደረገላቸው ያለው። ይሄም በቂ አይደለም። ከተፈናቀሉ ወራቶች ተቆጥረዋል። አሁን የአንድ ወር ቀለብም በአግባቡ እየደረሳቸው አይደለም” ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አባሉ የሁኔታውን አሳሳቢነት አጽንኦት ይሰጣሉ። የዳሰነች ወረዳ በአሁኑ ወቅት ያለው የህዝብ ብዛት 85 ሺህ የሚገመት መሆኑን የሚናገሩት ተወካዩ፤ በኦሞ ወንዝ ላይ የተገነቡት ግድቦች የሚያስከተሉት ጎርፍ በአብዛኛው ነዋሪ ላይ “ተጽዕኖ አሳድሯል” ይላሉ።
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ፌዴሬሽን ከአንድ ሳምንት በፊት ባወጣው መረጃ በዳሰነች ወረዳ ከሚገኘው ህዝብ 85 በመቶ ያህሉ በጎርፍ ሳቢያ መፈናቀሉን አስታውቆ ነበር። በጎርፉ ጤና ጣቢያዎችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ የመስኖ አውታሮችን የመሳሰሉ ማህበራዊ መሰረተ ልማቶች ክፉኛ መጎዳታቸውንም የግብረ ሰናይ ድርጅቱ ገልጿል።
“ኢንተርናሽናል ሪስኪዩ ኮሚቴ” የተሰኘው በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው ሌላኛው የግብረ ሰናይ ድርጅት በበኩሉ የኦሞ ወንዝ ባስከተለው ጎርፍ በዳሰነች ወረዳ የተፈናቀለው ህዝብ ብዛት 79 ሺህ እንደሚጠጋ ማስታወቁን አሶሴትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ከሁለት ሳምንት በፊት ዘግቦ ነበር። በኦሞ ወንዝ ላይ ግድቦች ሲሰሩ የታችኛው የህብረተሰብ ክፍሎች ሊያጋጥማቸው የሚችሉ ችግሮች በገለልተኛ አካል ጥናት መደረጉን የሚጠቅሱት አቶ ከበደ፤ “የመፍትሔ ሃሳቦች ተግባራዊ ባለመደረጋቸው እና ግድቦቹ ቀድመው በመሰራታቸው” ነዋሪዎች ለመፈናቀል እና ለምግብ እጥረት ተጋልጠዋል ሲሉ መንግስትን ይነቅፋሉ።
“ይሄንን ህብረተሰብ ያፈናቀልነው እኛው የመንግስት አካላት ነን። በግልጽ ለመናገር በዋነኛነት መንግስት ነው። ስለዚህ መንግስት እስካፈናቀለው ድረስ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል። በዚህ ዙሪያ በቀጣይ ኃላፊነት ወስዶ መስራት ይጠይቃል” ሲሉ አቶ ከበደ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የዳሰነች ወረዳ ተወካዩ ይህንኑ ሃሳባቸውን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በተካሄደው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አንጸባርቀዋል።
በስብሰባው ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፤ “ ‘በዳሰነች ወረዳ የሚገኙ አርብቶ አደሮች መፈናቀል ምክንያት ወይም ደግሞ አፈናቃይ መንግስት ነው’ ተብሎ የቀረበው ትክክል አይደለም” ብለዋል። “ግድቦች በሌሉባቸው ወንዞችም ሰው እየተፈናቀለ ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህም በክልሉ የሚገኘውን የወይጦ ወንዝ እና በሶማሌ ክልል የሚገኘው የሸበሌ ወንዝ በመሙላታቸው የተከሰተውን መፈናቀል በምሳሌነት አንስተዋል።
በዳሰነች ወረዳ በተከታታይ ጊዜያት አርብቶ አደሮች መፈናቀላቸውን ያመኑት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የእዚህ መንስኤው የግድቦች መሰራት ሳይሆን የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው ችግር መሆኑን ተናግረዋል። ከአየር ንብረት መዛባት በተጨማሪ በክልሉ ያለው “የአካባቢ ጥበቃ ስራ ደካማ መሆን”፤ ወንዞች “ከተጠበቀው በላይ” በዜጎች ላይ ጉዳት ለማድረሳቸው ምክንያት መሆኑን አቶ ጥላሁን ጨምረው ገልጸዋል።
የፌደራል መንግስት ግድቦችን በኦሞ ወንዝ ላይ መገንባት ሲጀምር ዝርዝር የመፍትሔ አማራጮችን ማቅረቡን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከዚህ ቀደም ወደ ዳሰነች በሄዱበት ወቅት ከአካባቢው ነዋሪ ጋር ከመግባባት ላይ የደረሱበትን ጉዳይ ለክልሉ ምክር ቤት አባላት አስረድተዋል። “ባለፈው ሄደን የተግባባነው፤ አርብቶ አደሮቹ ለጎርፍ መፈናቀል ተጋላጭ ከሆኑባቸው አካባቢዎች፤ መኖሪያ ቤታቸውን እና የሚሰበሰቡበትን አካባቢ ትንሽ ራቅ አድርገው፤ ያንን ቦታ ለከብቶቻቸው ግጦሽ ወይም ደግሞ ለእርሻ የሚሆንበት ሁኔታ እንዲመቻች [ነው]” ብለዋል አቶ ጥላሁን።
ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ከፌደራል፣ ከክልል የተውጣጣ ግብረ ኃይል “የተቀናጀ ስራ” እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። “በክልል፣ በፌደራል በኩል ተቀናጅተን ይሄንን ‘በቶሎ እንፍታ’ ብለን የጀመርነው፤ የአርብቶ አደሩ ድርሻ፣ የክልል፣ የዞኑ፣ የወረዳ፣ በጋራ ተቀናጅተን ከሰራን በአጭር ጊዜ ውስጥ ያ አካባቢ መልክ እንዲይዝ እናደርጋለን” ሲሉ ርዕሰ መስተዳድሩ የአጭር እና የረጅም ጊዜ መፍትሔ ለማበጀት ቃል ገብተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)