በተስፋለም ወልደየስ
ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤትን በኃላፊነት የመሩት ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ አምስት አባላት ያሉበትን የምርጫ ቦርድ የስራ አመራር ቦርድ በሰብሳቢነት እንዲመሩ በዛሬው ዕለት ተሹመዋል። የቦርዱ ሰብሳቢ ሹመታቸው በፓርላማ የጸደቀላቸው በአንድ ጽምጸ ተዐቅቦ ነው።
ምርጫ ቦርድን ለአራት ዓመት ከመንፈቅ በሰብሳቢነት የመሩት ብርቱካን ሚደቅሳን የተኩት ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ ከ30 ዓመት በላይ ሀገራቸውን በተለያዩ የስራ መስኮች ያገለገሉ መሆናቸው በዛሬው የፓርላማ ስብሰባ ላይ ተገልጿል። ተሿሚዋ በሙያቸው ካገለገሉባቸው ተቋማት መካከል መንግስታዊው የጉሙሩክ ባለስልጣን እና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሆነው ኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርስቲ ይጠቀሳሉ።
ሜላትወርቅ በኢትዮጵያ ጉምሩክ ባለስልጣን በነበራቸው የአስር ዓመታት ቆይታ፤ የመስሪያ ቤቱን የኦፕሬሽን መምሪያ እንዲሁም የህግ አፈጻጸም መምሪያን በኃላፊነት እስከ መምራት ተጉዘዋል። ኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በተቋቋመበት ወቅት፤ የተለያዩ የትምህርት መስኮችን ስርዓተ ትምህርት ቀረጻ የመምራት ሚና መጫወታቸው እና የዩኒቨርስቲ ኮሌጁ የሴኔት አባል ሆነው ማገልገላቸው ተነግሯል።
አዲሷ ተሿሚ በግላቸው ባቋቋሙት ድርጅት የህግ ማማከር እና ስልጠና፤ የህግ ሰነዶች ዝግጅት፣ የድርድር እና የግልግል አገልግሎትን ለደንበኞቻቸው ሲሰጡ መቆየታቸውም በስራ ልምድ ዝርዝራቸው ላይ ተጠቅሷል። ሜላትወርቅ በዚሁ ድርጅታቸው አማካኝነት፤ ለሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች የስትራቴጂ እና የፖሊሲ ሰነዶችን የመቅረጽ አገልግሎት ይሰጡ እንደነበርም ተመላክቷል።
ሜላትወርቅ ዛሬ በቦርድ ሰብሳቢነት እንዲመሩት የተሾሙበትን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በጽህፈት ቤት ኃላፊነት የተቀላቀሉት፤ መስሪያ ቤቱ ሀገር አቀፍ ምርጫን ከማካሄዱ ከአንድ አመት በፊት ነበር። የተሿሚዋን ዝርዝር የስራ ልምድ እና የትምህርት ዝግጅት ለፓርላማ አባላት ያቀረቡት በተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፤ ሜላትወርቅ በዚሁ ኃላፊነታቸው ወቅት “ከመላው ሰራተኛ እና የቦርድ አመራር ጋር በመሆን ምርጫ 2013 እንዲሁም በክልሎች የተካሄዱ ህዝበ ውሳኔዎችን በብቃት የመሩ [ናቸው]” ብለዋል።
“በአጠቃላይ በምርጫ ቦርድ የሪፎርም ስራዎች በብቃት በመሳተፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱ፤ እስካሁን በተመደቡበት በታማኝነት በትጋት እና በቅንነት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ የቆዩ ናቸው” ሲሉም አቶ ተስፋዬ የምርጫ ቦርድን አዲሷን የቦርድ ሰብሳቢ አሞካሽተዋቸዋል። ሜላትወርቅ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ቦርድ አባል ያለመሆናቸውን የጠቀሱት የመንግስት ተጠሪው፤ ባላቸው “ሰፊ ልምድ” “የምርጫ ቦርድን ስራ በወጤታማነት ይመራሉ ተብሎ እምነት የተጣለባቸው በመሆኑ” ፓርላማው ሹመታቸውን እንዲያጸድቅ ጠይቀዋል።

አዲሷን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሹመት በተመለከተ በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ አስተያየት ከሰጡ ስድስት የፓርላማ አባላት ውስጥ፤ ለየት ያለ ሃሳብ ያቀረቡት ዶ/ር ፈትሒ ማህዲ ብቻ ናቸው። ገዢው ብልጽግና ፓርቲን በመወከል ከሐረሪ ክልል ጀጎል ልዩ የምርጫ ክልል የተመረጡት ዶ/ር ፈትሒ፤ ምርጫ ቦርድ የሐረሪ ብሔረሰብ የምርጫ ውክልናን በተመለከተ ከዚህ ቀደም የወሰዳቸውን ውሳኔዎች ነቅፈዋል።
የኢትዮጵያ ህገ መንግስት በደነገገው መሰረት “አናሳ ብሔረሰቦች” በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 20 መቀመጫ እንደተመደበላቸው ያስታወሱት የፓርላማ አባሉ፤ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ለሐረሪ ብሔረሰብ አባላት ተወዳዳሪዎች ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል። ሆኖም ባለፈው ሀገር አቀፍ ምርጫ ወቅት፤ በዚህ መቀመጫ ላይ “የሐረሪ ብሔረሰብ አባላት ያልሆኑ ሌሎች ተመራጮች እንዲወዳደሩበት ሆኗል” ሲሉ አስረድተዋል።
ይህ ድርጊት የተፈጸመው፤ ጉዳዩን በተመለከተ የተወካዮች ምክር ቤት የሰጠውን ውሳኔ የምርጫ ቦርድ አመራሮች “ሳይቀበሉ በመቅረታቸው ነው” ሲሉ ተችተዋል። ዛሬ ሹመታቸው የጸደቀው የቀድሞው የምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና ሌሎች የምርጫ ቦርድ አመራሮች፤ ጉዳዩን የተመለከተው የሰበር ሰሚ ችሎት “ባለፉት አምስት የምርጫ ሂደቶች የነበረውን አሰራር ተግባራዊ አድርጉ” በሚል ያስተላለፈውን ውሳኔ “እንደገና ሲሸራርፉ ነበር” ሲሉ ወንጅለዋቸዋል።
“አሁን የሚመደቡት አመራሮችም ይሁኑ በምርጫ ቦርድ ውስጥ ያሉ አመራሮች፤ የኢትዮጵያን ብዝሃነት ያገናዘቡ፣ ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ እንደመሆኗ መጠን ቀጣይ እንደዚህ አይነት ጥያቄዎች ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ጉዳዩን አጽንኦት ሰጥተው፤ በጥንቃቄ፣ ቃለ መሃላ በሚገቡት፣ በህገ መንግስቱ መሰረት፤ ገለልተኛ፣ ነጻ ሆነው፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ከጫፍ እስከ ጫፍ በሀቀኝነት ማስተናገድ እንዳለባቸው ማስገንዘብ እፈልጋለሁ” ሲሉ የፓርላማ አባሉ ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።
ዶ/ር ፈትሒ “አግባብነት የሌለው” ሲሉ የገለጹትን የምርጫ ቦርድ ውሳኔ በተመለከተ ማብራራት ሲጀምሩ፤ አፈጉባኤ ታገሰ ጫፎ የሚሰጡት አስተያየት በቦርድ ሰብሳቢዋ ሹመት ላይ ብቻ ያተኮር እንዲሆን በማሳሰብ አቋርጠዋቸው ነበር። አዲሷ ተሿሚ የምርጫ ሂደቱ “አካል የነበሩ በመሆናቸው”፤ አሁን ደግሞ በከፍተኛ አመራር ስለተሾሙ “እንደዚህ አይነት ስህተቶች እንዳያደገሙ” እና “የቦርዱ አመራር ወደፊት ትምህርት እንዲወስድበት” ማብራሪያቸውን እንዲያቀርቡ እንዲፈቀድላቸው የፓርላማ አባሉ ጠይቀዋል።
አፈ ጉባኤ ታገሰ ለፓርላማ አባሉ አስተያየታቸውን የማቅረብ እድል ቢሰጧቸውም፤ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን ሹመት ለማጽደቅ የድምጽ አሰጣጥ በሚካሄድበት ወቅት ግን ዶ/ር ፈትሒ ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል። በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ከተገኙ 272 የፓርላማ አባላት ውስጥ በሹመቱ ላይ ተቃውሞ ያቀረበ ባለመኖሩ፤ የሜላትወርቅ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]