ኢቢሲ “ኢትዮጵያን አይመስልም” የሚል ትችት በፓርላማ አባላት ቀረበበት

ዛሬ ማክሰኞ ታህሳስ 9፤ 2016 በተካሄደው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ፤ አቶ ጌትነት ታደሰ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው በሙሉ ድምጽ ተሹመዋል። አቶ ጌትነት አዲሱን ሹመት ከማግኘታቸው በፊት በነበሩት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን በዋና ስራ አስፈጻሚነት ሲመሩ ቆይተዋል።

በኢቢሲ አዲስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሹመት ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ሁለት የፓርላማ አባላት፤ ተቋሙ “ኢትዮጵያን አይመስልም” የሚል ትችት አቅርበዋል። ከኦሮሚያ ክልል መቱ ወረዳ ተመርጠው ወደ ፓርላማ የገቡት ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ፤ ኢቢሲ “ከለውጡ ወዲህ ብዙ መሻሻሎች “ ቢያደርግም “አሁንም ግን ብዙ የሚቀሩት ነገሮች አሉ” ብለዋል።

“ኢቢሲ ይከተላቸው የነበራቸው ፓተርኖች እንደየጊዜው ይለያያሉ” ያሉት ኡስታዝ ካሚል፤ በቅርብ ጊዜያት በነበሩ ስርዓቶች “የሚንጸባረቅበት እና የሚሄድባቸው ሂደቶች በብዛት ኢትዮጵያን የሚመስሉ አልነበሩም” ሲሉ ተደምጠዋል። “ብዝሃነታችንን የሚገልጹት፣ የሚያንጸባርቁት፣ የሚሳዩት ሚዲያዎቻችን ናቸው። ስለዚህ የሆነን ማህብረሰብን ብቻ በየጊዜው የሚያንጸባርቁ፣ የሚያሳዩ ሲሆኑ፤ ያ ኢትዮጵያ አይደለም” ያሉት የፓርላማ አባሉ፤ አዲሱ ዋና ስራ አስፈጻሚ “ተቋሙን በትክክል ከላይ ታች መፈተሽ እንደሚገባቸው” አሳስበዋል።


ኢቢሲ “ከሰራተኛው፣ ከሚያቀርበው ፕሮግራም፣ ከሃይማኖት እና ከሌሎችም” አንጻር “ኢትዮጵያን የሚመስል ተቋም እንዲሆን  አመራሩ ይሰራል” የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ኡስታዝ ካሚል ገልጸዋል። ከኦሮሚያ ክልል ላሎ የምርጫ ክልል የተመረጡት የሆኑት አቶ አየለ ነገሪም ይህንኑ ሃሳብ አስተጋብተዋል።   

“ብዙ መስሪያ ቤቶች ኢትዮጵያን አይመስሉም። ይህን በግልጽ መነጋገር ነው የሚገባው። አንደኛ ሰው ተኮር፣ ሁለተኛ ብዝሃነትን በአግባቡ ያስተናገደ መሆን አለበት” ብለዋል እኚሁ የፓርላማ አባል። “ኢቢሲ ላይ እዚህ ቤት ብዙ ጊዜ ተነጋግረናል። ለምን አነሳችሁ ተብለን ተገምገምናል። የተወሰነ ብሔር ብሔረሰብ ያለበት ነው። የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ የለበትም” ሲሉ ነቅፈዋል።

የፓርላማ አባላቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን እና የሬድዮ ጣቢያዎችን በሚያስተዳድረው ኢቢሲ ላይ የሰላ ትችት ቢሰነዝሩም፤ ተቋሙን በስራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የቀረቡት የአቶ ጌትነት ሹመት ግን በሙሉ ድምጽ ከመጽደቅ አልተገታም። (በተስፋለም ወልደየስ – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)