የሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ሃሳቦችን የሚሰጡ ተወካዮችን ያስመረጡ ወረዳዎች ብዛት 327 መድረሱ ተገለጸ

በተስፋለም ወልደየስ

በኢትዮጵያ ካሉ ወረዳዎች መካከል 327 የሚሆኑት በሀገራዊ ምክክር ላይ የአጀንዳ ሃሳብ የሚሰጡ ተወካዮችን ሙሉ ለሙሉ መርጠው ማጠናቀቃቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ። የአማራ እና የትግራይ ክልሎች “አሁን ባሉባቸው ወቅታዊ ሁኔታዎች” ምክንያት ተወካዮችን የሚመርጡ ተሳታፊዎችን እስካሁን ድረስ መለየት አለመጀመራቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል። 

የኮሚሽኑ ቃል አቃባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ዛሬ አርብ ታህሳስ 12፤ 2016 በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ተወካዮችን መርጠው የጨረሱት ወረዳዎች በአምስት ክልሎች እና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ 119 ወረዳዎችን በመያዝ አብላጫውን ቁጥር በመያዝ ቀዳሚ የሆነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው። 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ሲዳማ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተወካዮቻቸውን መርጠው ባጠናቀቁ ወረዳዎች ብዛት አዲስ አበባን የሚከተሉ ናቸው። የጋምቤላ ክልል፣ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና የሐረሪ ክልልም እንዲሁ በዝርዝሩ ተካትተዋል። በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ 82 ወረዳዎች፤ ተወካዮቻቸውን በመምረጥ ሂደት ላይ መሆናቸውን አቶ ጥበቡ በዛሬው መግለጫ ላይ አመልክተዋል። 

“አሁን ተሳታፊዎችን ስንለይ፣ ለአጀንዳ ሃሳብ እንዲሰጡ ለየን ማለት ከእነርሱ መካከል ደግሞ በቀጣይ በሀገር አቀፍ ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ ተሳታፊዎች የሚወከሉት ከእነዚሁ መካከል ነው። ስለዚህ በአንድ ጊዜ ሁለት ስራ ነው እየተሰራ ያለው ማለት ነው። ለዚህም ነው በጥንቃቄ እና ጊዜ ተወስዶ ስራ እየተሰራ ያለው” ሲሉ የኮሚሽኑ ቃል አቃባይ የሀገራዊ ምክክሩ ሂደቱን አካሄዱን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት ተሳታፊዎችን የመለየት አሊያም ወኪሎቻቸውን በመምረጥ ሂደት ላይ ያሉ ወረዳዎች ብዛት 700 መድረሱ ቢነገርም፤ የአማራ እና የትግራይ ክልሎች ግን እስካሁንም ድረስ የተሳታፊዎች መለየት ስራ እንኳ አልጀመሩም። ሁለቱ ክልሎች ሂደቱን ያልጀመሩት “አሁን ባሉባቸው ወቅታዊ ሁኔታዎች” መሆኑን አቶ ጥበቡ ተናግረዋል። 

በትግራይ ክልል የተሳታፊዎች መለየት ስራ ያልተጀመረው፤ ክልሉ “ከጦርነት የመውጣት ሂደት ውስጥ ያለ በመሆኑ እና ብዙ ውስብስብ ችግሮች ስላሉ” መሆኑን የኮሚሽኑ ቃል አቃባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።  “ህብረተሰቡ በንቃት እና የሚሳተፍበትን አውድ ለመፍጠር ጊዜ ይፈልጋል። እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም” ሲሉም አክለዋል። 

“ይሄ ምክክር አሳታፊ መሆን አለበት። አካታች መሆን አለበት። ለመመካከር ምንን ይጠይቃል? መከባበርን፣ መቻቻልን፣ መደማመጥን፣ ትዕግስትን ይጠይቃል። [ህብረተሰቡ] በጦርነት፣ በድርቅ፣ በረሃብ እየተካለበ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ይሄን ነገር መፍጠር አይቻልም። ስለዚህ ሂደቶቹን ተከትሎ ከእውነታዎቹ ጋር በሚቀራረብ መንገድ ስራዎችን መስራት ተገቢ ነው ብለን እናስባለን። እርሱን ነው እየሰራን ያለነው” ሲሉም ኮሚሽኑ በዚህ ረገድ እያከናወነው ያለውን ቃል አቃባዩ አብራርተዋል። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሁለቱ ክልሎች ተሳታፊዎችን የመለየት ስራ ለመጀመር፤ “ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክሮች እየተካሄዱ” እና “ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ” መሆኑን አስታውቋል። ኮሚሽኑ በአማራ እና በትግራይ ክልሎች ላይ በቀጣይ ለሚሰራው ስራ፤ አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው ሌሎች ክልሎች ላይ ያሉ ስራዎቹን ማጠናቀቁ “ከፍተኛ ጥቅም” እንዳለው አቶ ጥበቡ አመልክተዋል።

የእነዚህ ስራዎች መጠናቀቅ፤ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ላይ “ሁኔታዎች ባመቹ ጊዜ በፍጥነት እና በጥራት ስራዎችን ለማከናወን ዕድል የሚሰጥ ነው” ሲሉ ቃለ አቃባዩ ጥቅሙን አስረድተዋል። በሁለቱ ክልሎች የተሳታፊዎች መለየት ስራ መቼ እንደሚጀመር ግን በጊዜ ማዕቀፍ ለይተው ከማስቀመጥ ተቆጥበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)