በሃዲያ ዞን ለሚገኙ መምህራን ደመወዝ በወቅቱ ባለመከፈሉ፤ 100 ሺህ ገደማ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን ኢሰመኮ ገለጸ 

በአዲስ መልክ በተደራጀው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃዲያ ዞን ለሚገኙ መምህራን “ተገቢው ደመወዝ በወቅቱ ባለመከፈሉ ምክንያት” የመንግስት ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን እና 100 ሺህ ገደማ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። በዞኑ ከደመወዝ አለመከፈል ጋር በተያያዘ “ቅሬታ እና ተቃውሞ ባሰሙ” ሰዎች ላይ፤ “ማስፈራራት፣ ዛቻ፣ ድብደባ” እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት “እስራት ጭምር” እንደደረሰባቸው ኮሚሽኑ ገልጿል። 

ኢሰመኮ ይህን የገለጸው፤ አዳዲስ የክልል አደረጃጀቶችን ተከትሎ በተለያዩ አካባቢዎች ተከስተዋል የተባሉ የደመወዝ መዘግየት እና መቋረጥን አስመልክቶ ያካሄደውን የሰብአዊ መብቶች ክትትል ምርመራ ውጤት ይፋ ባደረገበት መግለጫው ነው። ኮሚሽኑ የቀረቡለትን አቤቱታዎችን ጥቆማዎች መነሻ በማድረግ፤ በሃዲያ ዞን ስር በሚገኙት የሾኔ እና ሆሳዕና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የምሥራቅ ባድዋቾ፣ ምዕራብ ባድዋቾ እና ጎምቦራ ወረዳዎች በመገኘት የመስክ ምልከታ ማድረጉን በመግለጫው ተመልክቷል። 

ከጥቅምት 21 እስከ ህዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ በእነዚህ አካባቢዎች በተደረገው የማረጃ ማሰባሰብ ስራ የመንግስት ሰራተኞችን፣ የመንግስት አገልግሎት ማግኘት ያልቻሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን እና የሚመለከታቸው የመንግስት ኃላፊዎችን ማነጋገር መቻሉን ኢሰመኮ ገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ የጤና እና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ በተለያዩ የመንግስት ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ በአካል በመገኘት ምልከታ ማድረጉን አክሏል።

የኢሰመኮ ምርመራ በሸፈናቸው የሃዲያ ዞን አካባቢዎች ያሉ ከዘጠኝ ሺህ በላይ የመንግስት ሰራተኞች፤ ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ “የተቆራረጠ ክፍያ” ይደርሳቸው እንደነበር መግለጻቸውን ኮሚሽኑ ጠቅሷል። ካለፈው ነሐሴ ወር ጀምሮ ምርመራው እስከ ተከናወነበት ጊዜ ድረስ ደግሞ ደ”መወዝ ሙሉ በሙሉ በመቋረጡ ምክንያት”፤ የመንግስት ሰራተኞቹ “ለከፋ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ችግሮች መጋለጣቸውን” መረዳቱን ኮሚሽኑ በመግለጫው አስታውቋል።

ሌላ ገቢ እንደሌላቸው ለኢሰመኮ የገለጹ የመንግስት ሰራተኞች፤ ደመወዝ በመቋረጡ ምክንያት “ለራሳቸው እና ለቤተሰቦቻቸው የዕለት ጉርስ ለማግኘት እንደተቸገሩ” እና “የቤት ኪራይ መክፈል እንዳልቻሉ” መናገራቸው በመግለጫው ሰፍሯል። ከደመወዝ ጋር በተያያዘ በሚስተዋሉ ችግሮች ምክንያት ብድር ማግኘት እንዳልቻሉ፣ በአካባቢው ያሉ የብድር እና ቁጠባ ተቋማትም ለመንግስት ሰራተኞች ብድር መስጠት እንዳቋረጡ ከሰራተኞቹ መረዳቱን ኢሰመኮ ገልጿል። 

የመንግስት ሰራተኞቹ ህይወታቸውን ለማቆየት “የቤት እቃ ከመሸጥ ጀምሮ በተለያዩ የጉልበት ስራዎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ” ለኢሰመኮ ተናግረዋል ተብሏል። ለእንደዚህ አይነት ችግር ከተጋለጡ የመንግስት ሰራተኞች መካከል መምህራን እና የጤና ባለሙያዎች እንደሚገኙበት በመግለጫው ተመላክቷል። ምርመራ በሸፈናቸው የሃዲያ ዞን አካባቢዎች ያሉ የመንግስት ትምህርት ቤቶች፤ ለመምህራን ተገቢው ደመወዝ በወቅቱ ባለመከፈሉ ምክንያት መዘጋታቸውን ኮሚሽኑ በመስክ ምልከታው ወቅት አረጋግጧል። 

ፎቶ ፋይል፦ ምስራቅ ባድዋቾ ወረዳ መንግስት ኮሙኒኬሽን

በዚህም ምክንያት በሾኔ ከተማ፣ በምሥራቅ ባድዋቾ፣ በምዕራብ ባድዋቾ እንዲሁም በጎምቦራ ወረዳዎች በመንግስት ትምህርት ቤቶች ለመማር የተመዘገቡ ከ100 ሺህ በላይ ተማሪዎች፤ ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ተቋም ይፋ አድርጓል። በጤና ተቋምት ረገደም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳለ መመልከቱን ኢሰመኮ በመግለጫው ይፋ አድርጓል።

“ምልከታ በተደረገባቸው የከተማና ወረዳ አስተዳደሮች ውስጥ የሚገኙ ጤና ጣቢያዎች እና ጤና ኬላዎች ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ አገልግሎት [አለመስጠታቸውን] ለማረጋገጥ ተችሏል” ያለው ኮሚሽኑ፤ “በዚህም ምክንያት በተለይም በግል የጤና ተቋማት ለመታከም አቅም የሌላቸው እና ከዚህ በፊት በማኅበረሰብ ጤና መድህን ሽፋን በነዚህ ተቋማት አገልግሎት ሲያገኙ የቆዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በከፋ የጤና ችግር ውስጥ ይገኛሉ” ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት አጽንኦት ሰጥቷል።

የችግሩን ስፋት ለማሳየት ኢሰመኮ በመግለጫው ካካተታቸው የጤና ተቋማት ውስጥ፤ በምሥራቅ ባድዋቾ ወረዳ ተገንብተው አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ጤና ጣቢያዎች እና ጤና ኬላዎች ይገኙበታል። በወረዳው ከ144 ሺህ ሰው በላይ የሚገለገልባቸው፤ 6 ጤና ጣቢያዎች እና 27 ጤና ኬላዎች አገልግሎት የማይሰጡ መሆኑን ኮሚሽኑ በመግለጫው አስታውቋል።

ችግሩ መኖሩን ያመኑት የከተማ እና የወረዳ አስተዳደር ኃላፊዎች፤ ይህ የተከሰተው ለደመወዝ ይውል የነበረ “የውስጥ (የአካባቢ) ገቢ ማነስ” እና ከፌዴራል መንግስት ተመድቦ የሚመጣው በጀት ለማበዳሪያ ግዢ እና ለሌሎችም ጉዳዮች በመዋሉ መሆኑን ማስረዳታቸውን ኢሰመኮ በመግለጫው አስፍሯል። በተለያዩ ወቅቶች የተፈጸሙ እና “ያልተጠኑ የሰራተኞች ቅጥሮች” መኖራቸው ሌላው ችግር መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊዎቹ፤ ይህንንም “በተገቢው መንገድ ለማጥራት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ” መግለጻቸው በኮሚሽኑ መግለጫ ሰፍሯል።

የሃዲያ ዞን አስተዳደር ኃላፊዎችም፤ ችግሩ በዞኑ ውስጥ ካሉ 19 መዋቅሮች ውስጥ በስምንቱ መኖሩን ማረጋገጫ ሰጥተዋል ተብሏል። ኃላፊዎቹ “ምንም እንኳን ለዞኑ የሚላከው በጀት ከሚያስፈልገው መጠን ያነሰ ቢሆንም፤ ጉድለቱን በብድር በማሟላት ለከተማና ወረዳ አስተዳደሮች ለደመወዝ ክፍያ የሚያስፈልገውን ሙሉ የገንዘብ መጠን ሲልኩ መቆየታቸውን” መግለጻቸውም በመግለጫው ተጠቅሷል። የከተማ እና ወረዳ አስተዳደሮቹ በበኩላቸው  “ከሚላከው ገንዘብ ወደ ኋላ የነበሩ እዳዎች ስለሚከፈሉ፤ ችግሩ መቀጠሉን አስረድተዋል” ብሏል ኮሚሽኑ። 

የስራ መብት በተለያዩ ዓለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ሰነዶች ዕውቅና ካገኙ መሰረታዊ ሰብአዊ መብቶች መካከል አንዱ መሆኑን ያስታወሰው ኢሰመኮ፤ ይህም “የሰራተኞች ተገቢውን ክፍያ በሙሉ እና በወቅቱ የማግኘት መብትን የሚያጠቃልል” መሆኑን አስገንዝቧል። የሰብዓዊ መብት ተቋሙ፤ ሁሉም የክልል መስተዳድሮች ተገቢ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ “ለሰራተኞች ደመወዝ ወቅቱን ጠብቆ መከፈሉን ሊያረጋግጡ ይገባል” ሲል አሳስቧል። 

ኢሰመኮ በዛሬው መግለጫ ማጠቃላይ ላይ ምርመራውን ካደረገበት ወቅት ጀምሮ “በክልሎች ያለውን የደመወዝ ክፍያ ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ እርምጃዎች በመወሰድ ላይ” መሆናቸውን በአበረታችነት አንስቷል። ይህም ሆኖ ችግሩ በይበልጥ በታየባቸው የክልል እና የዞን አስተዳደሮች “ልዩ ትኩረት” በማድረግ “ዘላቂ መፍትሔ ማመቻቸት እንደሚገባ” ኮሚሽኑ ምክረ ሃሳቡን አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]