በሃሚድ አወል
ለአንድ ወር ገደማ በእስር ላይ የቆዩት በደቡብ ክልል ምክር ቤት የጉራጌ ዞን ተወካይ አቶ ታረቀኝ ደግፌ በመቶ ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ በፍርድ ቤት ተፈቀደላቸው፡፡ ዋስትናው የተፈቀደው ዛሬ ሰኞ ታህሳስ 24፤ 2015 በዋለው የደቡብ ክልል የሀዋሳ ማዕከል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ነው፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን የሰጠው የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የጠየቀውን 14 የምርመራ ቀናት ውድቅ በማድረግ ነው፡፡ የፖሊስ ጥያቄ በፍርድ ቤቱ ውድቅ የተደረገው፤ “ፖሊስ በቂ ጊዜ ነው የተሰጠው፤ እስካሁን ምርመራውን ማጠናቀቅ ነበረበት” በሚል መሆኑን የአቶ ታረቀኝ ጠበቃ አቶ ዮሴፍ ኡራጎ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል፡፡
በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ለደቡብ ክልል ምክር ቤት አባልነት የተመረጡት አቶ ታረቀኝ እና አቶ ሰንብት ነስሩ፤ በቁጥጥር ስር የዋሉት በጉራጌ ዞን “ወልቂጤ ከተማ የተቀሰቀሰን ሁከት መርተዋል” በሚል ተጠርጥረው መሆኑን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስታውቆ ነበር፡፡
ፖሊስ 14 የምርመራ ቀናትን የጠየቀው ከብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት መረጃዎችን ለማምጣት እና ለመተንተን እንዲሁም የምስክሮችን ቃል ለመስማት በሚል እንደነበር ጠበቃው አክለዋል፡፡ ፖሊስ ከዚህ በፊት በነበሩት የችሎት ውሎዎች ለሶስት ጊዜያት ያህል የምርመራ ቀናት ተፈቅደውለት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለፖሊስ አንድ ጊዜ ሰባት ቀናት፤ ለሁለት ጊዜያት ያህል ደግሞ አስር ቀናት ለምርመራ ተፈቅደውለት ነበር፡፡
አቶ ታረቀኝን እና ከእሳቸው ጋር አብረው ፍርድ ቤት የቀረቡት አቶ ሰንብት ነስሩን የወከሉት ጠበቃው በበኩላቸው ፍርድ ቤቱ የደንበኞቻቸውን የዋስትና መብት እንዲያከብር ጠይቀዋል፡፡ “ፖሊስ ማስረጃ የመሰብሰብ እንጂ የመተንተን ስልጣን የለውም” ሲሉ የተከራከሩት ጠበቃው ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የጠየቀውን የምርመራ ቀናት ውድቅ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ ከምስክር ቃል መቀበል ጋር በተያያዘም “ፖሊስ ከዕቅዱ በላይ የአስር ምስክሮችን ቃል ተቀብሏል” የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል፡፡ ፖሊስ ከዚህ በፊት በነበሩት የችሎት ውሎዎች የዘጠኝ ምስክሮችን ቃል እንደሚቀበል ለፍርድ ቤት ገልጾ ነበር፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው የክልሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት “ፖሊስ በቂ ጊዜ ነው የተሰጠው፤ እስካሁን ምርመራውን ማጠናቀቅ ነበረበት” በሚል የፖሊስን ጥያቄ ውድቅ አድርጎ ለተጠርጣሪዎቹ የመቶ ሺህ ብር ዋስትና ፈቅዷል፡፡ የደቡብ ክልል ምክር ቤት የኢዜማ ተወካይ የሆኑት አቶ ታረቀኝ እና አቶ ሰንብት ያለፈውን አንድ ወር ከሳምንት በእስር ላይ ያሳለፉት በሀዋሳ ከተማ በሚገኝ ማረሚያ ቤት ነበር፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)