አሜሪካ በኢትዮጵያ ለሚገኘው ኤምባሲዋ አዲስ አምባሳደር ልትሾም ነው

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኢትዮጵያ ለሚገኘው የሀገራቸው ኤምባሲ በሙሉ አምባሳደርነት የሚያገለግሉ ዲፕሎማትን በዕጩነት አቀረቡ። ፕሬዝዳንት ባይደን ለአምባሳደርነት በዕጩነት ያቀረቡት፤ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ተቀዳሚ ምክትል ጸሀፊ በመሆን እያገለገሉ የሚገኙትን ኢርቪን ሆዜ ማሲንጋን ነው።

ኢርቪን ማሲንጋ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው እንዲሰሩ መታጨታቸው ይፋ የተደረገው በዋይት ሐውስ በኩል ትላንት ማክሰኞ ታህሳስ 25፤ 2015 በወጣው መግለጫ ነው። የትላንቱ መግለጫ፤ ጆ ባይደን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአሜሪካ ምክትል ተወካይ የሚሆኑ ግለሰብን ጨምሮ፤ ሰባት ዲፕሎማቶች ለሹመት መታጨታቸው ይፋ የተደረገበት ነው። 

ፕሬዝዳንት ባይደን የዕጩ ዲፕሎማቶቻቸውን ዝርዝር በአሜሪካ ሴኔት እንዲጸድቅ ማስተላለፋቸው በመግለጫው ተጠቅሷል። የአሜሪካ ሴኔት የኢርቪን ማሲንጋን ሹመት ካጸደቀ፤ ከየካቲት 2014 ጀምሮ በ“ቻርዥ ደ አፌር” ደረጃ ሲመራ የቆየው በኢትዮጵያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ሙሉ ስልጣን ያለው አምባሳደር ያገኛል ማለት ነው። 

በአዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ላለፉት 11 ወራት “ቻርዥ ደ አፌር” በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት ትሬሲ አን ጃኮብሰን ናቸው። ትሬሲ ጃኮብሰን ይህን ኃላፊነት የተረከቡት፤ በኢትዮጵያ ለአንድ ዓመት የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩትን ጊታ ፓሲን በመተካት ነበር። 

የአምባሳደርነት ሹመታቸው ከጸደቀ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ኢርቪን ማሲንጋ፤ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ተቀዳሚ ምክትል ጸሀፊ ሆነው ማገልገል የጀመሩት ከ14 ወራት ገደማ በፊት ነው። ዲፕሎማቱ ወደ አፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ ከመሸጋገራቸው በፊት፤ በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ስር በሚገኘው የደቡብ እና ማዕከላዊ እስያ ጉዳዮች ቢሮ የፓኪስታን ጉዳዮች ምክትል ረዳት ጸሀፊ ሆነው ሰርተዋል። ከዚህ በተጨማሪ የቢሮው የፓኪስታን ጉዳዮች ቢሮ ዳይሬክተር ነበሩ።

ኢርቪን ማሲንጋ በኢትዮጵያ ጎረቤት በሆነችው ሱዳን፤ ለሁለት ዓመታት ያህል በዲፕሎማትነት አገልግለዋል። ማሲንጋ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ምክትል ዋና የተልዕኮ መሪ በመሆነ የሰሩት ከ2008 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ነው። ዲፕሎማቱ ወደ ካርቱም ከመምጣታቸው አስቀድሞ፤ በሌላኛው የአፍሪካ ሀገር ጊኒ ለሶስት ዓመታት በተመሳሳይ የኃላፊነት ቦታ ሰርተዋል።  

ማሲንጋ በአፍሪካ አህጉር የነበራቸው የዲፕሎማሲ ስራ አይቮሪ ኮስትንም የጨመረ ነው። ዲፕሎማቱ ከዚህ በተጨማሪ በቻይና፣ ዶመኒካን ሪፐብሊክ እና ቻይና ባሉ ኤምባሲዎች በተለያዩ የስራ ኃላፊነቶች ተመድበው ማገልገላቸውን የህይወት ታሪካቸው ዝርዝር ያሳያል። የጆርጅ ታውን እና ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲዎች ምሩቅ የሆኑት ኢርቪን ማሲንጋ፤ ከእንግሊዘኛ በተጨማሪ ፈረንሳይኛ፣ ስፓኒሽ እና የቻይና ማንዳሪን ቋንቋዎችን የሚናገሩ ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)