በአማኑኤል ይልቃል
በኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ የወባ በሽታ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር “ከፍተኛ” መሆኑን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ። ካለፈው ዓመት ሐምሌ እስከ ህዳር ወር በወባ በሽታ ተጠረጥረው ምርመራ ከተደረገላቸው 6.3 ሚሊዮን ሰዎች ውስጥ፤ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በሽታው እንደተገኘባቸው ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።
በኢንስቲትዩቱ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቅኝት እና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ወሰን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ያለው የወባ በሽታ ስርጭት “በወረርሽኝ ደረጃ” የሚቀመጥ ነው። ከአዲስ አበባ ከተማ፣ ከሀረሪ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ውጭ ባሉ አካባቢዎች ያለው የበሽታው ስርጭት፤ “ከፍተኛ” የሚባል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የጋምቤላ ክልል ካለው የህዝብ ብዛት አንጻር ሲመዘን፤ በርካታ የወባ በሽታ ተጠቂዎች የተመዘገቡበት መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ የወባ በሽታ በምርመራ ከተገኘባቸው ታማሚዎች ውስጥ ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበው ግን በአማራ ክልል መሆኑን አቶ መስፍን ጠቁመዋል። ከአጠቃላይ የታማሚዎች ቁጥር ውስጥ ከ35 እስከ 40 በመቶ የተመዘገቡት በዚህ ክልል መሆኑንም አክለዋል።

በአማራ ክልል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በወባ በሽታ የመጠቃታቸው ምክንያት፤ በክልሉ ካሉ በርካታ የቀን ሰራተኞች ጋር የተያያዘ መሆኑን በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት የወባ ማጥፋት ቡድን አስተባባሪ አቶ ጉዲሳ አሰፋ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ምርታማ በሆኑት የአማራ ክልል ምዕራባዊ አካባቢዎች ለስራ የሚንቀሳቀሱ የቀን ሰራተኞች፤ በስፍራዎቹ ባለው ሙቀት ምክንያት ከቤት “ውጭ ማደራቸው” ለበሽታው ተጋላጭ እንዳደረጋቸው አቶ ጉዲሳ አብራርተዋል።
ከአማራ ክልል በመቀጠል ከፍተኛ የወባ በሽታ ታማሚዎች ቁጥር የተመዘገበው በኦሮሚያ ክልል መሆኑን ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በኦሮሚያ ክልል ለበሽታው ስርጭት መስፋፋት አስተዋጽኦ ካደረጉት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ፤ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ባለሙያዎች ይጠቅሳሉ።
በሚኒስቴሩ የወባ ማጥፋት ቡድን አስተባባሪ፤ በክልሉ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የወባ በሽታን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በጤና ተቋማት አማካኝነት መሰራት ያለባቸው ስራዎች ላይ “መላላት” መታየቱን ለዚህ በማሳያነት አንስተዋል። በእነዚህ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት መድኃኒት ባለመድረሱ እና ወደ ጤና ተቋም የሚወስዱ መንገዶች በመዘጋታቸው፤ በወባ የተያዙ “የተወሰኑ ሰዎች” ህይወታቸው እንዳለፈም አቶ ጉዲሳ አስረድተዋል።

በሁለቱ ክልሎች ከተጠቀሱት ከእነዚህ መንስኤዎች ባሻገር፤ ሀገር እና ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው ሌሎች ምክንያቶች በወባ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ለመጨመሩ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን የወባ ማጥፋት ቡድን አስተባባሪው ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም በወባ ላይ የተሰሩ ስራዎች “በጣም ከፍተኛ ውጤት” ማስመዝገቡን የሚናገሩት አቶ ጉዲሳ፤ ይህ “ያስከተለው መዘናጋት” በሀገር አቀፍ ደረጃ ለወባ ስርጭት መጨመር የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።
“ ‘ወባ ጠፍቷል’ በሚል በህብረተሰቡ፣ በባለሙያ፣ በአመራር ደረጃ የመዘናጋት ነገሮች ነበሩ። በመዘናጋት ምክንያት ሰዎች የወባ መከላከል እርምጃዎችን አይወስዱም። ‘ወባ ጠፍቷል’ በሚል የመኝታ አልጋ አጎበር አይጠቀሙም፤ ያስቀምጡታል። እኛ ሁሌ በመኝታ ሰዓት እንዲጠቀሙ ነው የምንመክረው” ሲሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከታዩ ችግሮች መካከል አንዱን ጠቅሰዋል።
ዓለም አቀፋዊ ይዘት ካላቸው ምክንያቶች ውስጥ ደግሞ በኮቪድ-19 መከሰት ምክንያት የወባ መድኃኒት እና መከላከያ ቁሳቁስ አምራች የሆኑ ኩባንያዎች ምርት አቋርጠው መቆየታቸውን በምሳሌነት አንስተዋል። በዚህ ምክንያት የወባ መድኃኒቶችን እና አጎበር “በጊዜ” ማግኘት እንዳልተቻለ የሚገልጹት አቶ ጉዲሳ፤ “በተለይ ባለፈው ዓመት ቶሎ መተካት የነበረባቸው አጎበሮች ሳይተኩ ቆይተዋል። በዚህ ዓመት እሱን የማካካስ ስራ እየሰራን ነው” ሲሉ ችግሩ የፈጠረው ተጽእኖ ይበልጥ እንዳይባባስ እየተደረገ ያለውን ጥረት ገልጸዋል።

የጤና ሚኒስቴር ከ“ግሎባል ፈንድ” እና USAID በተገኘ ገንዘብ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር የ19.7 ሚሊዮን አጎበር ግዢ መፈጸሙን የወባ ማጥፋት ቡድን አስተባባሪ ተናግረዋል። ከውጭ ሀገር ከተገዛው ከዚህ አጎበር ውስጥ 12 ሚሊዮን ገደማው ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ወደተለያዩ ወረዳዎች መሰራጨቱንም አክለዋል። ግዢ የተፈጸመበት ቀሪው አጎበር ጅቡቲ መድረሱን እና እስከ የካቲት ወር ድረስ ተሰራጭቶ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)