በሃሚድ አወል
የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ከነገ በስቲያ ረቡዕ ጥር 3፤ 2015 የጋራ ልዩ ስብሰባ ሊያደርጉ ነው። ምክር ቤቶቹ የጋራ ስብሰባ የሚያደርጉት በንብረት ታክስ ባለቤትነት ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ተረፈ በዳዳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የፌደራል መንግስትን ገቢ ለማሳደግ በተያዘው በጀት ዓመት ተግባራዊ ይደረጋሉ ከተባሉ የታክስ አይነቶች አንዱ የንብረት ታክስ (property tax) ነው። የነዳጅ ኤክሳይስ ታክስም ከ2015 ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ መወሰኑ ይታወሳል። የገንዘብ ሚኒስቴር የ2015 በጀት ሰነድን ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት፤ በበጀት ዓመቱ ተግባራዊ ከሚደረገው የንብረት ታክስ ከሚገኘው ገቢ 25 በመቶው ለፌደራል መንግስት እንዲሆን የሚያስችል ረቂቅ ለፌደሬሽን ምክር ቤት መላኩን አስታውቆ ነበር።
በፌደሬሽን ምክር ቤት የፊስካል ጉዳዮች እና የክልሎች የተመጣጠነ ዕድገት ጥናት ዳይሬክተር ዋቅቶሌ ዳዲ፤ ረቡዕ በሚደረገው የሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ላይ የገቢ አሰባሰቡን በተመለከተ ሁለት አማራጮች እንደሚቀርቡ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚያቀርባቸው እነዚህ አማራጮች፤ ከንብረት ታክስ የሚገኘውን ገቢ የመሰብሰብ ስልጣን የክልሎች ብቻ እንዲሆን አሊያም የፌደራል መንግስት እና ክልሎች ገቢውን በጋራ እንዲከፋፈሉ የሚያደርግ ነው።
ሁለቱም አማራጮች ያላቸው ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ምን እንደሆኑ በረቡዕ የጋራ ስብሰባ ላይ ለሁለቱ ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ እንደሚሰጥ አቶ ዋቅቶሌ ገልጸዋል። የንብረት ታክሱን የመሰብሰብ ኃላፊነት “የማን ይሆናል የሚለውን ነገር ሁለቱ ምክር ቤቶች በጋራ በሚያደርጉት ስብሰባ ይወስናሉ” ሲሉም አክለዋል። ሁለቱ ምክር ቤቶች በዚሁ ስብሰባቸው የንብረት ታክስ ለፌደራል እና ለክልል መንግስታት እንዲሆን ከወሰኑ፤ ቀጣዩ ሂደት በፌደሬሽን ምክር ቤት ቀመር ማዘጋጀት መሆኑን አቶ ዋቅቶሌ አስረድተዋል።
የንብረት ታክስን የመሰብሰብ ስልጣን “የፌደራል መንግስት ብቻ ይሁን” የሚል አማራጭ ያልቀረበበት ምክንያት አቶ ዋቅቶሌ ሲያስረዱ፤ “የፌደራል ነው ብሎ አሁን ምክረ ሃሳብ ማቅረብ አይቻልም። ምክንያቱም ንብረት ክልል ላይ ነው ያለው፤ በየቦታው ነው ያለው” ብለዋል። በኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሰረት፤ የፌደራል እና የክልል መንግስታት የገቢ ክፍፍል የሚያደርጉት የፌደራል አደረጃጃትን በተከተለ መልኩ ነው።
የፌደራል መንግስት በባለቤትነት ከሚያስተዳድራቸው ቤቶች እና ሌሎች ንብረቶች ገቢ ላይ ግብር የመጣል፣ የመሰብሰብ እና ኪራይ የመወሰን ስልጣን በህገ መንግስቱ ተሰጥቶታል። ህገ መንግስቱ በተመሳሳይ መልኩ የክልል መስተዳድሮች በግል ባለቤትነት ስር ካሉ ቤቶችና ሌሎች ንብረቶች በሚገኝ ገቢ ላይ ግብር እንደሚጥሉ እና እንደሚሰበስቡ ደንግጓል። ከዚህ በተጨማሪም የክልል መስተዳድሮች በባለቤትነት በሚያስተዳድሯቸው ቤቶች እና ሌሎች ንብረቶች ላይ ኪራይ እንደሚያስከፍሉ በህገ መንግስቱ ሰፍሯል።
ከእነዚህ ድንጋጌዎች ውጪ በ1987 ዓ.ም. በወጣው ህገ መንግስት ላይ የንብረት ታክስ አሰባሰብን በተመለከተ በግልጽ የተቀመጠ አንቀጽ የለም። ሆኖም ህገ መንግስቱ፤ በህጉ ተለይተው ያልተሰጡ ታክስ እና ግብር የመጣል ስልጣኖችን ወደፊት እንዴት እንደሚደነገጉ ራሱን የቻለ አንቀጽ አካትቷል። እንዲህ አይነት ስልጣኖች የሚወሰኑት፤ የፌዴሬሽን እና የተወካዮች ምክር ቤት በጋራ በሚያደርጉት ስብሰባ በሁለት ሶስተኛ ድምጽ ሲወስኑ መሆኑን በህገ መንግስቱ ተቀምጧል።
ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ጥሪ እንደተላለፈላቸው ሁለት የፓርላማ አባላት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ነገር ግን የስብሰባው አጀንዳ እንዳልተገለጸላቸው አመልክተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)