ለ“ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” ህዝበ ውሳኔ፤ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ድምጽ ሰጪዎች መመዝገባቸውን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

በሃሚድ አወል


የ“ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል”ን ለመመስረት በመጪው ጥር 29 ለሚደረገው ህዝበ ውሳኔ፤ 2.9 ሚሊዮን ድምጽ ሰጪዎች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ለህዝበ ውሳኔው የተመዘገቡት ድምጽ ሰጪዎች ቁጥር፤ ቦርዱ በግምት ካስቀመጠው የመራጮች ብዛት በ200 ሺህ ገደማ ያነሰ ነው። 

ምርጫ ቦርድ በነባሩ የደቡብ ክልል በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ለሚያካሄደው ህዝበ ውሳኔ ይመዘገባሉ ብሎ የገመታቸው ድምጽ ሰጪዎች ብዛት 3.1 ሚሊዮን ነበር። ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ለሁለት ሳምንት ገደማ ያህል ሲያካሄድ የቆየውን የመራጮች ምዝገባ መጠናቀቁን በይፋ ያስታወቀው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ታህሳስ 26፤ 2015 ነበር። ቦርዱ ለህዝበ ውሳኔው መራጮችን ሲመዘግብ የነበረው በ3,769 ምርጫ ጣቢያዎች ነበር።

ቦርዱ አጠቃላይ የህዝበ ውሳኔውን ሂደት በተመለከተ ዛሬ ሰኞ በሰጠው መግለጫ፤ “ከፍተኛ የሆነ የህግ እና የአፈጻጸም ጥሰት” ተከስቶባቸዋል ባላቸው 24 የምርጫ ጣቢያዎች ድጋሚ ምዝገባ እየተካሄደ እንደሆነ ገልጿል። መግለጫውን የሰጡት የቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ “እነዚህ ጣቢያዎች ላይ የነበሩትን የመራጮች ምዝገባ ሂደት እንዳለ ሰርዘን ድጋሚ የመራጮች ምዝገባ እንዲደረግ አድርገናል። ዛሬም እየተከናወነ ነው። በሚቀጥሉት ሁለት እና ሶስት ቀናት፤ የመራጮች ምዝገባ በእነዚህ 24 ጣቢያዎች ላይ እንደ አዲስ የሚከናወን ይሆናል” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የመራጮች ካርድ መሰጠት ለሌለበት ግለሰብ መሰጠት፣ ጣቢያ ያልተገኙ ሰዎች በመራጭነት መመዝገብ እንዲሁም ከጣቢያ ውጭ ካርዶች ሲታደሉ መገኘታቸው በእነዚህ የምርጫ ጣቢያዎች ተፈጸሙ የተባሉ ጥሰቶች ናቸው። እነዚህ ጥሰቶች በራሱ በቦርዱ ክትትል የተረጋገጡ መሆናቸውን ሰብሳቢዋ ገልጸዋል። ጥሰቱን ተከትሎ ስለተወሰዱ እርምጃዎች ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ብርቱካን፤ ቦርዱ የወሰደው የመጀመሪያ እርምጃ በምርጫ ጣቢያዎቹ ሲደረግ የነበረው የመራጮች ምዝገባ እንዲሰረዝ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።  

ምርጫ ቦርድ የምዝገባ ሂደቱ እንዲቆም እና ከዚህ ቀደም የተደረገው ምዝገባ እንዲሰረዝ ውሳኔ ያሳለፈው የዛሬ ሳምንት ሰኞ ታህሳስ 24፤ 2015 ነበር። ውሳኔውን ተከትሎም የመራጮች ምዝገባው በተሰረዘባቸው ጣቢያዎች ካለፈው ሳምንት ረቡዕ ታህሳስ 26 ጀምሮ የመራጮች ምዝገባ በድጋሚ ማካሄድ ጀምሯል። ምዝገባው ከነገ በስቲያ ረቡዕ ጥር 3 እንደሚጠናቀቅ በዛሬው መግለጫ ተነስቷል።

ቦርዱ የወሰደው ሁለተኛ እርምጃ ደግሞ፤ በምርጫ ጣቢያዎቹ ሲሰሩ የነበሩ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ውል በማቋረጥ ከስራ ማባረር መሆኑን ብርቱካን አስረድተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ቦርዱ የራሱ ሰራተኞች በሆኑ የምርጫ አስፈጻሚዎች እና ከአስፈጻሚዎች ጋር ተባብረው “ህገ ወጥ ተግባር ሲፈጽሙ ነበሩ” ባላቸው የአስተዳደር አካላት ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ለፌደራል ፖሊስ ደብዳቤ መጻፉን አክለዋል።

ከፌደራል ፖሊስ “ቶሎ ምላሽ አልተሰጠንም” ያሉት የቦርድ ሰብሳቢዋ፤ “የፍትህ አካላት እርምጃውን በአስቸኳይ እና በስርዓቱ መውሰድ አለባቸው” ብለዋል። “ይሄ ወንጀል ከሚኖረው መጥፎ ገጽታ እና ተጽዕኖ [አንጻር]፤ በአንድ ጣቢያ እንደተፈጸመ ወንጀል ወይም በአንድ ቦታ ብቻ እንደተደረገ ወንጀል እዚያ ከላይ እንደሚወሰን አድርገን አንወስደውም” ሲሉ ቦርዱ ለጉዳዩ የሰጠውን ክብደት ለጋዜጠኞች አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]