የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ አትሌቶችን የያዘ የልዑካን ቡድን ነገ ወደ መቐለ ሊጓዝ ነው  

በአማኑኤል ይልቃል

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች እና የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ አትሌቶችን የያዘ የልዑካን ቡድን፤ ነገ ማክሰኞ ጥር 2፤ 2015 ወደ መቐለ ከተማ ሊጓዝ ነው። በአትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አትሌት ደራርቱ ቱሉ የሚመራው ልዑክ ወደ መቐለ የሚጓዘው፤ የክልሉ ተወላጅ የሆኑ አትሌቶችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለማገናኘት መሆኑ ተገልጿል።

ወደ ትግራይ ክልል መዲና ነገ ረፋድ በአውሮፕላን የሚጓዘው ይህ የልዑካን ቡድን፤ በመቐለ ከተማ የሚኖረው ቆይታ የአንድ ቀን ብቻ መሆኑን በጉዞው ላይ ተሳታፊ የሆነ አንድ አትሌት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። ይህንኑ መረጃ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ለገሰ፤ የፌዴሬሽኑ አመራሮች እና አባላት በአንድ ቀን ቢመለሱም እዚያው የሚቆዩ አትሌቶች ግን ሊኖሩ ይችላሉ ብለዋል። 

በዚህ ጉዞ ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች፣ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እና “የተለያዩ የስራ ክፍል አባላት” ተሳታፊ እንደሚሆኑ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያው ገልጸዋል። በነገው ጉዞ ከሚሳተፉ የትግራይ ክልል ተወላጅ ከሆኑ አትሌቶች መካከል፤ በቶኪዮ ኦሎምፒክ እና በአሜሪካው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዎች የነበሩት ለተሰንበት ግደይ፣ ጎተይቶም ገብረ ስላሴ እና ጉዳፍ ጸጋይ እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ አትሌቶች በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት ከአንድ ዓመት ለሚልቅ ጊዜ ቤተሰቦቻቸውን ሳያገኙ መቆየታቸውን ያስታወሱት አቶ ቴዎድሮስ፤ የጉዞው ዋነኛ ዓላማ “አትሌቶቹን ወስዶ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ማገናኘት” መሆኑን አስረድተዋል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አትሌት ደራርቱ ቱሉ፤ በአሜሪካ ኦሪገን በተካሄደው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ደማቅ ውጤት ላስመዘገቡ አትሌቶች ባለፈው ሐምሌ ወር በተደረገ አቀባበል ስነ ስርዓት ይህንኑ ጉዳይ አንስታ ነበር።

“የትግራይ አትሌቶች ቤተሰቦቻቸውን የማግኘት እድል አሁንም አላገኙም” ስትል በወቅቱ የተናገረችው ደራርቱ፤ በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ እና የፌደራል መንግስት “ይህን እንደሚቀርፉ” ያላትን እምነት ገልጻ ነበር። የትግራይ ክልል መንግስትም ይህ እውን እንዲሆን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ ማድረጓም አይዘነጋም። ደራርቱ በዚሁ ንግግሯ በጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል የሚገኙ አትሌቶች በውድድሮች ላይ መሳተፍ አለመቻላቸው ጠቅሳ፤ በክልሉ ያሉ አትሌቶች “ስራቸውን እንዲጀምሩ”፣ ወደ አዲስ አበባ መምጣት ያለባቸውም መጓዝ እንዲችሉ፤ የፌደራሉ መንግስት “መንገድ እንዲከፍት” እና “መሰረታዊ ነገሮችን” እንዲያሟላ ተጨማሪ ጥያቄ ማቅረቧ ይታወሳል። 

ከነገው ጉዞ ዋነኛ ዓላማ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች በትግራይ ክልል ከሚገኙ የአትሌቲክስ ስፖርት ክለቦች ጋር ውይይት ለማድረግ ዕቅድ መያዛቸው ተገልጿል። ከክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች ከተውጣጡ የክለብ ተወካዮች ጋር የሚደረገው ይህ ውይይት፤ በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የአትሌቲክስ ስፖርት እንቅስቃሴ እንደገና “የሚነቃቃበትን ዕድል ይፈጥራል” የሚል እምነት እንዳላቸው የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያው ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)