የነዳጅ ማደያዎች ያገኙት በነበረው የትርፍ ህዳግ ላይ ከሁለት ዓመት በኋላ ማሻሻያ ተደረገ 

በአማኑኤል ይልቃል

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፤ ነዳጅ አዳዮች ለሁለት ዓመት ገደማ ሲሰሩበት በነበረው የትርፍ ህዳግ ላይ ማሻሻያ አደረገ። በአዲሱ ማሻሻያ መሰረት በማደያዎች ለሽያጭ ከሚቀርበው ነዳጅ በሊትር ይገኝ የነበረው ትርፍ፤ በ64.4 ሳንቲም እንዲጨምር ተደርጓል። 

ይህ ማሻሻያ ይፋ የሆነው፤ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከትላንት እሁድ ታህሳስ 30፣ 2015 እኩለ ለሊት ጀምሮ ተግባራዊ ባደረገው የጥር ወር የነዳጅ ምርቶች ችርቻሮ ዋጋ ላይ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሲያደርገው የቆየውን የነዳጅ ድጎማ ከሐምሌ 2014 በከፊል ካነሳ ወዲህ በነዳጅ ምርቶች ላይ ማስተካከያ ሲደረግ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

በትላንትናው የዋጋ ማስተካከያ መሰረት፤ 57 ብር የነበረው የአንድ ሊትር ቤንዚን መሸጫ ወደ 61 ብር ከፍ ብሏል። የሰባት ብር ገደማ ጭማሪ የተደረገበት የነጭ ናፍጣ መሸጫ ደግሞ 67 ብር ሆኗል። የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ይህን የዋጋ ማስተካከያ በተመለከተ ለነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች በላከው ደብዳቤ፤ አዲሱ የነዳጅ መሸጫ ዋጋ በትርፍ ህዳግ ላይ የተደረገውን ማሻሻያ ያካተተ እንደሆነ አስታውቋል።

በዚህ ማሻሻያ መሰረት ከዚህ ቀደም የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች ከእያንዳንዱ የነዳጅ ምርት በሊትር ያገኙት የነበረው የ23 ሳንቲም ገደማ የትርፍ ህዳግ፤ አሁን ወደ 88 ሳንቲም አድጓል። የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች በተደጋጋሚ ሲጠይቁ በነበሩት የትርፍ ህዳግ ማስተካከያ ላይ ማሻሻያ የተደረገው፤ የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን ያካሄደውን ጥናት መሰረት በማድረግ ነው። 

ባለስልጣኑ የትርፍ ህዳጉ እንዲሻሻል ያደረገው በሶስት ምክንያቶች መሆኑን የመስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖስ ወርቁ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የትርፍ ህዳጉ አነስተኛነት፤ ነዳጅ በሀገር ውስጥ በጥቁር ገበያ እንዲሸጥ ምክንያት መሆኑ በጥናት እንደተደረሰበት አቶ ሄኖስ ገልጸዋል። ነዳጅ በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ወጥቶ በኮንትሮባንድ ለመሸጡም የትርፍ ህዳጉ አነስተኛነት አስተዋጽኦ እንዳለው የጥናቱ ግኝት አመላክቷል ብለዋል። 

የአሁኑን ማሻሻያ ለማድረግ በነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን በሶስተኛነት የተቀመጠው ምክንያት፤ የቀድሞ የትርፍ ህዳግ “አዋጪ አለመሆኑ” ነው። “የትርፍ ህዳጉ ከአንድ ቦቴ የሚያስገኘው ወደ አስር ሺህ ብር አካባቢ ስለነበር አዋጪ አልነበረም” የሚሉት አቶ ሄኖስ፤ ይህም የነዳጅ ግብይቱን “ለህገወጥ” ድርጊቶች እንዳጋለጠ አስረድተዋል።

አሁን የተደረገው የ64 ሳንቲም ጭማሪ፤ የነዳጅ ማደያ ባለቤቶች በተደጋጋሚ ሲያነሱት ለነበረው ጥያቄ ምላሽ ቢሰጥም “በቂ አይደለም” የሚል ትችት ተሰንዝሮበታል። የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማህበር ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ለባለስልጣኑ እና ለንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባቀረበው ጥናት፤ የትርፍ ህዳጉ 1 ብር ከ25 ሳንቲም እንዲሆን ጠይቆ ነበር።

የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማህበር የስራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ፤ መንግስት የትርፍ ህዳጉን “ለማስተካከል የሄደበትን ርቀት እና ተነሳሽነት” ማህበሩ እንደሚያደንቅ ገልጸው፤ ሆኖም ጭማሪው “አርኪ” አለመሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አሁን የተደረገው ማሻሻያ ነዳጅ አዳዮች ከሁለት ዓመት በፊት ሲያገኙት ከነበረው ትርፍ ጋር እንዲቀራረብ ያደረገ መሆኑን በመጥቀስም፤ “የነበረው ተካካሰ እንጂ ትርፋችን አልጨመረም” የሚል ሀሳብ ሰንዝረዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት በአንድ ቦቴ የሚጫን 45 ሺህ ሊትር ነዳጅ አንድ ሚሊዮን ብር ገደማ ይገዛ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ኤፍሬም፤  ይህ ዋጋ አሁን ወደ ሶስት ሚሊዮን ብር ማሻቀቡን ገልጸዋል። በዚህ የግብይት ወቅት ነዳጅ አዳዮች ከአንድ ቦቴ ያገኙት የነበረው ትርፍ 10,620 ብር እንደነበር የማህበሩ የስራ አመራር ቦርድ አባሉ ይጠቅሳሉ።

በአሁኑ ማሻሻያ ከአንድ ቦቴ የሚገኘው ትርፍ 39 ሺህ ብር ቢሆንም፤ ከሁለት ዓመት በፊት ይገኝ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ግን ጭማሪው 0.25 በመቶ ብቻ መሆኑን ያብራራሉ። የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማህበር፤ የትርፍ ህዳጉ ወደ 1 ብር ከ25 ሳንቲም እንዲያድግ ጥያቄ ሲያቀርብ የአንድ ሊትር ነዳጅ ዋጋ 35 ብር ገደማ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ኤፍሬም፤ አሁን ባለው የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋ መሰረት የትርፍ ህዳጉ መሆን የነበረበት 1 ብር ከ50 ሳንቲም እንደሆነ ይከራከራሉ።

የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሄኖስ ስለ ማህበሩ ቅሬታ ለቀረበላቸው ጥያቄ “ሁሉም ሰው የተሻለ ትርፍ ማካበት ይፈልጋል። ግን አጠቃላይ ማክሮ ኢኮኖሚው ሊሸከመው የሚችል፤ ተገቢ የሆነ የትርፍ ህዳግ ማሻሻያ ነው የተደረገው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የትርፍ ህዳጉ በየዓመቱ የሚሻሻል በመሆኑ የአሁኑ ጭማሪ “እንደ መነሻ” ተወስዶ፤ ወደፊት ተጨማሪ ማስተካከያ ሊደረግ እንደሚችል ጠቁመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)