በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች፤ በዚህ ዓመት ምርጫ ለማካሄድ መታቀዱ ተገለጸ

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “ከጸጥታ ጋር በተያያዘ” ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች፤ በተያዘው በጀት ዓመት ምርጫ ለማካሄድ ማቀዱን ገለጸ። ቦርዱ በአካባቢዎቹ ምርጫ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ ስለመኖሩ ማብራሪያ እንዲሰጠው ክልሎችን መጠየቁንም አስታውቋል። 

ምርጫ ቦርድ ይህን ያስታወቀው ትላንት ሰኞ ጥር 1፤ 2015 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረበ ጥያቄ በሰጠው ምላሽ  ነው። መግለጫውን የሰጡት የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ “ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ምርጫ ያልተደረገባቸው የተወሰኑ አካባቢዎች መኖራቸውን እናውቃለን፤ የቦርዱ ሃሳብ እና ዕቅድ ምርጫ ባልተደረገባቸው አካባቢዎች በዚህ በጀት ዘመን ምርጫ እንዲደረግባቸው ማድረግ ነው” ሲሉ ለጋዜጠኞች የተቋማቸውን ዕቅድ ገልጸዋል።  

“እያንዳንዱ ክልል በእነዚህ አካባቢዎች ያለውን የጸጥታ ሁኔታ ተመልክቶ ለምርጫ አስቻይ ሁኔታ መኖሩን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጠን ጽፈናል” ያሉት ብርቱካን፤ እስካሁን ከሶስት ክልሎች ምላሽ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። ምላሽ የሰጡት ክልሎች አማራ፣ አፋር እና ደቡብ ናቸው።

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

በአማራ ክልል በጸጥታ ችግር ምክንያት ሰኔ 14፤ 2013 ምርጫ ያልተካሄደባቸው የምርጫ ክልሎች አስር ናቸው። ከእነዚህ በተጨማሪም “በአሰራር ግድፈት” ምክንያት ስድስት ምርጫ ክልሎች ላይ ድጋሚ ምርጫ እንዲከናወን ቦርዱ መወሰኑ ይታወሳል። የአማራ ክልል በአጠቃላይ በተወካዮች ምክር ቤት 138 የፓርላማ ወንበሮች አሉት።

የአፋር ክልል ካሉት ስምንት የፓርላማ መቀመጫዎች መካከል ሁለቱ በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ አልተካሄደባቸውም። በፓርላማ 178 መቀመጫዎች ባሉት የኦሮሚያ ክልል፤ በተመሳሳይ የጸጥታ ችግር ምክንያት በሰባት የምርጫ ክልሎች ምርጫ አልተደረገም። የምርጫ አካባቢዎቹን የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ እስካሁን ለምርጫ ቦርድ ማብራሪያ ያልሰጠው የኦሮሚያ ክልል መሆኑን ብርቱካን በትላንቱ መግለጫቸው ተናግረዋል።

የቦርድ ሰብሳቢዋ የኦሮሚያ ክልል ለቦርዱ ማብራሪያ አለመስጠቱን ቢያነሱም “ኦሮሚያ ላይ ምርጫ ባልተደረገባቸው ምርጫ ክልሎች፤ አሁን ለምርጫ አስቻይ ሁኔታ ያለ አይመስለንም” ሲሉ ምርጫ ባልተደረገባቸው የክልሉ አካባቢዎች አሁንም የጸጥታ ችግር መኖሩን ጠቁመዋል። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ከጸጥታ ጋር በተያያዘ ምርጫ ያልተደረገባቸው አካባቢዎች መኖራቸውንም የቦርድ ሰብሳቢዋ አስታውሰዋል። 

ፎቶ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካሉት ዘጠኝ የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ ምርጫ የተከናወነው በሶስቱ ብቻ ነው። በተመሳሳይ ከ99 የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ ምርጫ ተካሄዶ በተወካዮች የተያዙት ሃያ ስምንቱ ብቻ ናቸው። እነዚህን መቀመጫዎች ያሸነፈው ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ነው።

በክልሉ ህገ መንግስት መሰረት ሃያ ስምንት የክልል ምክር ቤት መቀመጫዎች መንግስት ለመመስረት ስለማያስችሉ፤ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን በአሁኑ ወቅት እያስተዳደረ የሚገኘው ከስምንት አመት በፊት በ2007 ዓ.ም የተመሰረተው መንግስት ነው። በክልሉ የሚንቀሳቀሰው ተቃዋሚው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) በክልሉ በዚህ ዓመት ምርጫ እንዲካሄድ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

ቦዴፓ ምርጫ ያልተደረገባቸው አካባቢዎች በአሁኑ ወቅት “ለምርጫ አስቻይ የሆነ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ” የሚል እምነት እንዳለው በዚሁ መግለጫው አስታውቋል። ፓርቲው ይህን ቢልም የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ግን “በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እኛም ራሳችን ቡድን ልከን በደንብ መገምገም ያለብን ይመስለናል” ሲሉ የጸጥታ ሁኔታው ተጨማሪ ዳሰሳ እንደሚያስፈልገው በትላንቱ መግለጫቸው አመልክተዋል። ቦርዱ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ላይ የክልሉን የጸጥታ ሁኔታ የሚገመግም የመረጃ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ማካሄዱ አይዘነጋም። 

ምርጫ ቦርድ ይህን የግምገማ መርሃ ግብር ከማካሄዱ አምስት ወራት አስቀድሞ፤ በክልሉ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት ማድረግ ጀምሮ ነበር። በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በታህሳስ 2014 ሊካሄድ ታቅዶ ለነበረው ምርጫ ይደረግ የነበረው ዝግጅት፤ የድምጽ መስጪያ ጊዜው ከመድረሱ ሁለት ወራት አስቀድሞ ተቋርጧል። ቦርዱ ጊዜያዊ የምርጫ ሰሌዳ ካወጣ በኋላ ዝግጅቱን ያቋረጠው፤ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በመላው ኢትዮጵያ በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ነው።

ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ በጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ ካልተካሄደባቸው አካባቢዎች በተጨማሪ ድጋሚ ምርጫ የሚያከናውንባቸው አካባቢዎች መኖራቸውንም ትላንት በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ከእነዚህ አካባቢዎች መካከል አንዱ የሆነው በደቡብ ክልል የሚገኘው የቡሌ ምርጫ ክልል ነው። ለሁለተኛ ጊዜ የሚደረገው የድጋሚ ምርጫ በመጪው ጥር 29 እንደሚካሄድ የቦርዱ ሰብሳቢ ገልጸዋል።

የድጋሚ ምርጫውን በዚህ ቀን ለማድረግ የተወሰነው፤ የቡሌ ምርጫ ክልል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝበ ውሳኔ ከሚካሄድባቸው ዞኖች አንዱ በሆነው ጌዴኦ የሚገኝ በመሆኑ የድምጽ አሰጣጡን አንድ ላይ ለማድረግ በማሰብ መሆኑን ብርቱካን አስረድተዋል። ለድጋሚ ምርጫ አዲስ ምዝገባ እንደማይኖር የጠቀሱት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ፤ “ቀኑ በሚደርስበት ጊዜ እዚያ አካባቢ ያሉ መራጮች ይሄንኑ እንዲያውቁ እናደርጋለን” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)