የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አዲስ ዋና ዳይሬክተር ተሾመለት 

በሃሚድ አወል

የቀድሞው ዋና ዳይሬክተሩ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉበት የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት፤ ከአንድ ወር በኋላ አዲስ ኃላፊ ተሾመለት። አዲሱ ተሿሚ የሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ሙሉቀን አማረ ናቸው።

የቀድሞው የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ላይ ነበር። የፌደራል ዐቃቤ ህግ፤ በአቶ ቴዎድሮስ ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱን ይፋ ያደረገው ዛሬ ማክሰኞ ማክሰኞ ጥር 2፤ 2015 ነው። ዐቃቤ ህግ ክሱን የመሰረተው፤ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ነው።

 አቶ ቴዎድሮስ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት ለሁለት ዓመት ገደማ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎትን በዋና ዳይሬክተርነት መምራታቸውን፤ የተቋሙ የህዝብ ግንኙነት ስራ አስፈጻሚ አቶ እንዳለ አሰፋ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። አገልግሎት መስሪያ ቤቱ፤ የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ደህንነትን ለማረጋገጥ፤ መረጃዎችን በማሰባሰብና በመተንተን ለሚመለከታቸው የህግ አስከባሪ አካላት የማሰራጨት ስልጣን ያለው ነው።  

ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሆነው ይህ መስሪያ ቤት፤ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመርዳት ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን መነሻ፣ የአፈጻጸም ስልት፣ አይነት፣ ባህሪ እና አደጋ በማጥናት የመፍትህ አቅጣጫ የመጠቆም ኃላፊነት ተጥሎበታል።    

ይህ መንግስታዊ ተቋም በሙስና ተጠረጥረው በቁጥጥር ስር በዋሉት ዋና ዳይሬክተሩ ምትክ ኃላፊ እስከሚሾምለት ድረስ፤ ስራዎቹን “በህጉ አግባብ ሲያከናውን” እንደቆየ አቶ እንዳለ አስረድተዋል። ባለፈው ዓመት የካቲት ወር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባወጣው የተቋሙ ማቋቋሚያ ደንብ መሰረት፤ ዋና ዳይሬክተሩ በማይኖሩበት ጊዜ እርሳቸውን ወክሎ የመስራት ኃላፊነት ያለው ምክትል ዳይሬክተሩ ነው። 

በዚህ ሁኔታ ስራውን ለአንድ ወር ሲያከናውን የቆየው ተቋሙ፤ የዛሬ ሁለት ሳምንት ገደማ አዲስ ዋና ዳይሬክተር ተሹሞለታል። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙት አዲሱ ዋና ዳይሬክተር ስራ የጀመሩት ባለፈው ሳምንት ሰኞ መሆኑን አቶ እንዳለ  ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አዲሱ ተሿሚ በዛሬው ዕለት ከተቋሙ ሰራተኞች ጋር ትውውቅ ማድረጋቸውንም አክለዋል።

አቶ ሙሉቀን አማረ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው እስከተሾሙበት ጊዜ ድረስ ለሶስት ዓመት ገደማ የሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ አገልግሎትን በዋና ዳይሬክተርነት መርተዋል። በፋይናንስ እና በኮምፒዩተር ሳይንስ ሁለት የመጀመሪያ ዲግሪዎችን ያገኙት አቶ ሙሉቀን፤ የሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ሆነው ለአራት አመት ያህል ሰርተዋል። 

አቶ ሙሉቀን የመጀመሪያ ዲግሪዎቻቸውን ከተማሩበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢንፎርሜሽን ሳይንስ እንዲሁም ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በአመራር እና መልካም አስተዳደር የማስተርስ ዲግሪዎችን አግኝተዋል፡፡ የሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ አገልግሎትን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተርነት የተቀላቀሉት አቶ ሙሉቀን፤ በሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች በተለያዩ በኃላፊነቶች አገልግለዋል። አዲሱ ዋና ዳይሬክተር ከሰሩባቸው የመንግስት ተቋማት መካከል ፍትህ ሚኒስቴር እና እህል ንግድ ድርጅት ይጠቀሳሉ።

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቋቋም የነበረው ስያሜ “የፋይናንስ ደህንነት መረጃ ማዕከል” የሚል ነበር። መስሪያ ቤቱ፤ አሁን ያለውን ስያሜ የያዘው ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ በወጣው የአስፈጻሚ አካላት ስልጣን እና ተግባርን መወሰኛ አዋጅ ነው። የስያሜ ለውጡን ተከትሎም የአገልግሎቱ ማቋቋሚያ ደንብ፤ ከ12 ዓመታት በኋላ ባለፈው ዓመት ተሻሽሎ ወጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)