ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት በኢትዮጵያ በተከሰሰበት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ወንጀል የ18 ዓመታት እስራት የተበየነበት እና ለኔዘርላንድ ተላልፎ የተሰጠ ኤርትራዊ ዛሬ ማክሰኞ ፍርድ ቤት ቀረበ። ስቮለ በተባለች የኔዘርላንድ ከተማ በሚገኝ ችሎት ፊት የቀረበው ግለሰብ፤ ተወልደ ጎይቶም የተባለ “በሰዎች ማዘዋወር ወንጀል የሚፈለግ ግለሰብ ነው” ብለው እንደሚያምኑ የሀገሪቱ ዐቃብያነ ህግ ለፍርድ ቤት ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሰኔ 2013 በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ከወሰነበት በኋላ ባለፈው መስከረም ወር ለኔዘርላንድ ተላልፎ የተሰጠው ይኸው ተጠርጣሪ፤ አማኑኤል ይርጋ ዳምጤ ወይም ወሊድ በሚል ስም የሚጠራ ነው። ተጠርጣሪው ዛሬ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ስሙ ዳህላክ ኪሮስ ያያ መሆኑን በመግለጽ፤ የኔዘርላንድ ዐቃብያነ ህግ የሚፈልጉት ተጠርጣሪ እንዳልሆነ ለችሎት አስረድቷል።
የኔዘርላንድ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ከዛሬው የችሎት ውሎ በኋላ ባወጣው መግለጫ ግን ተጠርጣሪው በኢትዮጵያ የ18 ዓመታት እስር የተበየነበት እና ለኔዘርላንድ ተላልፎ የተሰጠ መሆኑን ገልጿል። ግለሰቡ በሰዎች ማዘዋወር፣ እገታ እና ብዝበዛ የተሰማራ እና ወሲባዊ ጥቃትን ጨምሮ ሁከት የሚፈጽም የወንጀል ድርጅት ውስጥ በመሳተፍ መጠርጠሩን ቢሮው በዚሁ መግለጫው አስታውቋል።
በተጠርጣሪው ድርጊት ሰለባ የሆኑት አብዛኞቹ ሰዎች ወደ ኔዘርላንድ የተጓዙ ኤርትራውያን መሆናቸውን የጠቀሰው መግለጫው፤ ስደተኞቹ ጉዟቸውን ባስተባበሩት የሰዎች አዘዋዋሪዎች ለኃይለኛ ሁከት መጋለጣቸውን አመልክቷል። የሰዎች አዘዋዋሪዎቹ በሊቢያ ባዘጋጇቸው ቤቶች፤ ስደተኞቹ ታስረው እንዲቆዩ ያደርጓቸው እንደነበርም መግለጫው አትቷል። በኔዘርላንድ የሚገኙ የስደተኞቹ ቤተሰቦች ለማስለቀቂያ ገንዘብ እንዲከፍሉ ይገደዱ እንደነበርም መግለጫው አክሏል።
መኖሪያቸውን በዚያው በኔዘርላንድ ያደረጉ እና “አስገድዶ ገንዘብ በማስከፈሉ ድርጊት ተሳትፈዋል” የተባሉ ሌሎች አምስት ሰዎችም ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ የኔዘርላንድ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ገልጿል። ከአንድ ሳምንት በፊት በሱዳን በቁጥጥር ስር የዋለው እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በእስር ላይ የሚገኘው ኪዳነ ዘካርያስ በተባለ ተጠርጣሪ ላይም ተመሳሳይ ክስ እንደሚመሰረት ቢሮው በዛሬው መግለጫው ጠቅሷል።
ኔዘርላንድ ይኸው ተጠርጣሪ ተላልፎ እንዲሰጣት ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በይፋ ጥያቄ እንደምታቀርብም መግለጫው ጠቁሟል። ኪዳነ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በእስር ላይ የሚገኘው በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ተጠርጥሮ ነው። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በመራችው ዓለም አቀፍ የፖሊስ ተልዕኮ በሱዳን በቁጥጥር ስር የዋለው ኪዳነ ዘካርያስ፤ በኢትዮጵያ በእስር ላይ እያለ ያመለጠ እንደነበር የፌደራል ፖሊስ ባለፈው ሳምንት ማስታወቁ አይዘነጋም።
ተጠርጣሪው “ከፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ፖሊስ እጅ” ያመለጠው በየካቲት 2013 እንደነበር የፌደራል ፖሊስ በወቅቱ ገልጿል። በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በኢትዮጵያ ፍርድ ቤት ክሱን እየተከታተለ የነበረው ኪዳነ፤ ከእስር ካመለጠ በኋላ የዕድሜ ልክ ተፈርዶበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)