በግጭት የወደሙ የጤና ተቋማትን በሶስት ዓመት ውስጥ መልሶ ለመገንባት እቅድ መያዙን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ

በአማኑኤል ይልቃል

በኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች በግጭት ምክንያት የወደሙ የጤና ተቋማትን ወደ ስራ ለማስገባት፤ የሶስት ዓመት እቅድ አውጥቶ ወደ ተግባር መግባቱን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። የመልሶ ግንባታ እቅዱ በተለያዩ ምዕራፎች እንደሚከናወን የገለጸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ ቅድሚያ የሚሰጣቸው በግብአት መሟላት ወደ ስራ መመለስ የሚችሉ ተቋማት መሆናቸውን ይፋ አድርጓል።

ጤና ሚኒስቴር ይህንን ያስታወቀው በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ግንባታን አስመልክቶ ትላንት ማክሰኞ ጥር 2፤ 2015 በሰጠው መግለጫ ነው። የጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በሰጡት በዚሁ መግለጫ፤ በግጭት ምክንያት የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ የመገንባት ስራ “በአጭር ጊዜ የሚቋጭ ሳይሆን የተለያዩ ደረጃዎች ባሉት መልኩ የሚሰራ” መሆኑን ተናግረዋል።

ፎቶ፦ ጤና ሚኒስቴር

የመልሶ ግንባታ ስራው በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከተጎዱት የትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ባሻገር፤ የተለያዩ ግጭቶችን ያስተናገዱትን የኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እንደሚያካትት ገልጸዋል። በደቡብ ክልል ግጭት የተፈጠረባቸው “የተወሰኑ አካባቢዎችም” የእቅዱ አካል እንደሆኑ አመልክተዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወነው የመልሶ ግንባታ ስራ እቅድ የተዘጋጀው በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ሊያ፤ “ሰፊ ጥናት ተደርጎ፣ ሰፊ እቅድ ተሰርቶ፤ ቢያንስ  ወደ ሶስት ዓመት የሚፈጅ ስራ እንደሚሆን ታሳቢ በማድረግ ነው ወደ ስራ የተገባው” ብለዋል። በጦርነት እና ግጭቶች ምክንያት በጤና ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለመመለስ የተሰራው ጥናት፤ ለመልሶ ግንባታ 1.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ማመላከቱን ሚኒስትሯ አስታውቀዋል። 

ይሁንና ተጨማሪ ጥናቶች ሲደረጉ ለመልሶ ግንባታው ያስፈልጋል የተባለው የገንዘብ ግምት “ሊበልጥ እንደሚችል” ታሳቢ መደረጉን በመግለጫው ላይ ተናግረዋል። ለመልሶ ግንባታው የሚውለው ገንዘብ በመንግስት ከሚመደብ በጀት እና የዓለም ባንክን ጨምሮ “ከተለያዩ አካላት” ከሚገኝ ድጋፍ ይሸፈናል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

ዶ/ር ሊያ የመልሶ ግንባታው “ሰፊ የሆነ በጀት እና ግብዓት” የሚጠይቅ በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ችግሮችን “ደረጃ በደረጃ” የመፍታት አካሄድን እንደሚከተል ጠቁመዋል። ለስራው የሚሆን ድጋፍ ከተለያዩ አካላት ቢገኝም እንኳን አፈጻጸሙ “አስቸጋሪ” ስለሚሆን ይህንን አካሄድ ለመከተል መታሰቡንም አስረድተዋል። ጤና ሚኒስቴር ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች የጤና አገልግሎትን ለመመለስ በሚከተለው አካሄድ በቶሎ ወደ ስራ መግባት ለሚችሉ የጤና ተቋማት ቅድሚያ መስጠቱንም አክለዋል።

በጦርነት ጉዳት በደረሰባቸው የአማራ እና አፋር ክልሎች ተመሳሳይ አካሄድ መከተሉን ያወሱት ሚኒስትሯ፤ በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ ሆስፒታሎች በመጀመሪያ የድንገተኛ እና የእናቶች ጤና አገልግሎቶችን እንዲጀምሩ መደረጉን አንስተዋል። ከሆስፒታሎች ቀጥሎ አገልግሎት እንዲጀምሩ የተደረጉት ጤና ጣቢያዎች እንደነበሩም አስታውሰዋል። 

በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ፤ በትግራይ ክልል የሚገኙ የጤና ተቋማትን ወደ ስራ ለማስገባት ሚኒስቴሩ ወደ ከ30 በላይ ቡድኖችን ወደ ስፍራው መላኩን ዶ/ር ሊያ በትላንቱ መግለጫቸው ጠቅሰዋል። የጤና ሚኒስቴር ቡድኖች ባደረጉት እገዛም፤ በትግራይ ክልል የሚገኙ 12 ሆስፒታሎች እና 28 የጤና ጣቢያዎች ወደ ስራ መመለሳቸውን ተናግረዋል። ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ግምታቸው 243.6 ሚሊዮን ብር የሆኑ መድሃኒቶች እና የህክምና ግብዓቶች ወደ ክልሉ መላኩንም ጨምረው ገልጸዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች በሚያከናውነው የመልሶ ግንባታ ስራ ላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሆስፒታሎች መሆኑን ዶ/ር ሊያ አመልክተዋል። ሆስፒታሎች ቅድሚያ የተሰጣቸው “ሰፋ ያለ አገልግሎት” ስለሚሰጡ መሆኑንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል። ሆስፒታሎችን ተከትሎ የጤና ጣቢያ እና ጤና ኬላዎች መልሶ ግንባታ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል። 

“ጤና ኬላዎች በጣም መሰረታዊ የሆነ የጤና ስርዓታችን አካል ናቸው። አገልግሎት በቶሎ መጀመር አለባቸው” ያሉት ዶ/ር ሊያ፤ በሶስተኛ ደረጃ እንዲቀመጡ የተደረጉት ካለው የሀብት ፍላጎት እና መሰረታዊ ችግር አንጻር መሆኑን አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)