የአማራ ክልል ለሁለት ዓመት ገደማ ታግዶ የቆየውን የአዲስ ሰራተኞች ቅጥር በከፊል ፈቀደ

በአማኑኤል ይልቃል

የአማራ ክልል የሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኃብት ልማት ኮሚሽን፤ በክልሉ ከሚያዝያ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ታግዶ የቆየውን የሰራተኞች ስምሪት በከፊል ማንሳቱን አስታወቀ። ኮሚሽኑ በክልሉ የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በተያዘው በጀት ዓመት በተለቀቁ ክፍት የስራ መደቦች ላይ ብቻ ቅጥር እንዲፈጽሙ ፈቃድ ሰጥቷል። 

በአማራ ክልል ላለፈው አንድ ዓመት ከስምንት ወራት ያህል የሰው ኃይል ስምሪት ታግዶ የቆየው፤ በክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት በተላለፈ ውሳኔ ነው። የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት ውሳኔውን ያሳለፈው ክልሉ የ“በጀት እጥረት አለበት” በሚል ምክንያት ነበር። በክልሉ ያሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፤ የሰራተኞች ቅጥር፣ ዝውውር እና የደረጃ እድገት እንዳያከናውኑ የተወሰነው፤ በ“ወቅታዊ ሁኔታ” የተነሳ እንደነበር የአማራ ክልል የሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኃብት ልማት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወ/ሮ ካሣ አበባው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።   

ይህ እገዳ ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ በክልሉ የሚገኙ መስሪያ ቤቶች የሰራተኛ ቅጥርን ለመፈጸም በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረባቸውን የሚናገሩት ወ/ሮ ካሣ፤ ኮሚሽኑም “የማስታገሻ እርምጃዎችን” ሲወስድ መቆየቱን ገልጸዋል። በዚህም መሰረት “አንገብጋቢ” በሚባል ደረጃ የሰራተኛ እጥረት ያለባቸው መስሪያ ቤቶች፤ ጉዳያቸው በኮሚሽኑ እየታየ ቅጥር እንዲፈጽሙ ሲፈቀድ እንደነበር አስታውሰዋል።

የሲቪል ሰርቪስ እና የሰው ኃብት ልማት ኮሚሽኑ በክልሉ ለሚገኙ የዞን እና ሪጆፖሊታን ከተማ አስተዳደሮች ትላንት ማክሰኞ ጥር 2፤ 2015 በጻፈው ደብዳቤ ደግሞ፤ በተያዘው በጀት ዓመት ስራቸውን የለቀቁ ሰራተኞች ያሉባቸው መስሪያ ቤቶች ከኮሚሽኑ ፈቃድ ሳያገኙ አዲስ ቅጥር ማከናወን እንደሚችሉ አሳውቋል። በክልሉ የሚገኙ መስሪያ ቤቶቹ ሰራተኛ መቅጠር የሚችሉት ግን  “የበጀት ዓመቱ እስከሚጠናቀቅ” ድረስ ብቻ መሆኑ በደብዳቤው ተመልክቷል። 

ቅጥር እንዲፈጸም የተፈቀደባቸው የስራ መደቦች የበጀት ዓመቱ ሲጀመር ሰራተኛ የነበረባቸው መሆኑን የሚናገሩት ምክትል ኮሚሽነሯ፤ ለእነዚህ ቦታዎች ቀድሞውንም በጀት የተያዘ በመሆኑ ተጨማሪ ወጪ የማይጠይቁ መሆኑን አስገንዝበዋል። ሰራተኞች በለቀቁባቸው የክልሉ መስሪያ ቤቶች “ስራዎች እየቆሙ” መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ ካሣ፤ ስራዎች እንዳይስተጓጉሉ በሚል ኮሚሽኑ የአሁኑን ውሳኔ ማሳለፉን አስረድተዋል። 

ኮሚሽኑ በትላንትናው ዕለት ባሰራጨው ደብዳቤ ፈቃድ የሰጠበት ሌላኛው ጉዳይ፤ በክልሉ በሚገኙ መስሪያ ቤቶች “በታሳቢ የተቀጠሩ የመንግስት ሰራተኞች” ለደረጃ እድገት እንዲወዳደሩ የሚያደርግ ነው። በአንድ የስራ መደብ ላይ ለመቀጠር በቂ የትምህርት ዝግጅት ቢኖራቸውም ተፈላጊውን የስራ ልምድ የማያሟሉ ስራ ፈላጊዎች፤ በአማራ ክልል በ“ታሳቢ ሰራተኛነት” የሚቀጠሩበት አሰራር እንዳለ ወ/ሮ ካሣ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። 

እነዚህ ሰራተኞች ክፍት ለሆነ የስራ መደብ ቢቀጠሩም፤ የስራ ልምዳቸው እስከሚሟላ ድረስ የሚያገኙት ደመወዝ ዝቅተኛ ሆኖ እንደሚቆይ ምክትል ኮሚሽነሯ አስረድተዋል። ሰራተኞቹ ተፈላጊውን የስራ ልምድ ሲያሟሉ ግን ለቦታው የተወሰነውን ደመወዝ ከሌሎች ጋር ተወዳድረው የማግኘት ዕድል እንደሚኖራቸው አክለዋል። ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር በፊት በተላለፈው የስራ ስምሪት እገዳ ምክንያት ግን የስራ ልምድ ማሟላት የቻሉ ሰራተኞች ለደመወዝ ጭማሪ መወዳደር አለመቻላቸውን ጠቁመዋል። 

ለ“ታሳቢ ሰራተኞች” የሚደረገው ውድድር በትላንትናው ዕለት በተሰራጨው ደብዳቤ ቢፈቀድም፤ መስሪያ ቤቶቹ ለዚሁ የሚሆን በጀት እንዳላቸው በቅድሚያ ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸው ኮሚሽኑ አሳስቧል። በዚሁ ደብዳቤ ላይ ለመንግስት መስሪያ ቤቶች የተቀመጠው ሌላኛው ማሳሰቢያ፤ አሁን ከተፈቀዱት የስራ መደቦች ውጭ የሚደረግ የሰው ኃይል ስምሪትን የተመለከተ ነው። “ከተፈቀደላቸው የስራ መደቦች ውጭ የሰው ኃይል ስምሪት ውጭ መፈጸም በህግ የሚያስጠየቅ” መሆኑን ያስጠነቀቀው ኮሚሽኑ፤ በዚህ መልክ የተከናወነ የሰራተኞች ቅጥር፣ ዝውውር ወይም የደረጃ እድገት “ፈራሽ” እንደሚሆንም አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)