በንብረት ላይ የሚጣለውን ታክስ፤ ክልሎች በባለቤትነት እንዲያስተዳድሩ ተወሰነ   

በሃሚድ አወል

የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች፤ በንብረት ላይ የሚጣለውን ታክስ ባለቤትነት ለክልሎች የሚያደርገውን ውሳኔ በአብላጫ ድምጽ አጸደቁ። ሁለቱ ምክር ቤቶች ዛሬ ረቡዕ ጥር 3፤ 2015 ባደረጉት ልዩ ስብሰባ ውሳኔውን ያጸደቁት፤ በአራት ተቃውሞ እና በአምስት ድምጸ ተዐቅቦ ነው።

ምክር ቤቶቹ ከንብረት የሚሰበሰበው ታክስ የክልሎች እንዲሆን የወሰኑት፤ “ከተሞች ከንብረት የሚገኘውን ገቢ በሚገባ በመሰብሰብ የመሰረተ ልማት አቅርቦትን ለማሻሻል፤ የማህበራዊ አገልግሎት ተቋማትን ለመገንባት እንዲጠቀሙበት በማድረግ በመላ ሀገሪቱ ባሉ ከተሞች የሚታየውን ችግር ለማቃለል ይችላሉ” በሚል ምክንያት ነው። በዛሬው ስብሰባ ቀርቦ የነበረው ሁለተኛ አማራጭ፤  የፌደራል እና የክልል መንግስታት በጋራ የንብረት ታክስ የመሰብሰብ ስልጣን እንዲኖራቸው እና በፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚወሰነው ቀመር መሰረት ገቢውን እንዲከፋፈሉ የሚያደርግ ነው።

አማራጮቹን ለሁለቱ ምክር ቤቶች ያቀረቡት፤ በፌደሬሽን ምክር ቤት የድጎማ በጀት እና የጋራ ገቢዎች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም በፓርላማው የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ናቸው። የውሳኔ ሃሳቡን ለሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት በንባብ ያሰሙት፤ የድጎማ በጀት እና የጋራ ገቢዎች ቋሚ ኮሚቴ ጸሀፊው አቶ ኃይሉ ኢፋ ናቸው።

የሁለቱ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች “ከንብረት ታክስ የሚገኘው ገቢ ለአካባቢ መስተዳድሮች መሆን ይገባዋል” የሚል ውሳኔ ማሳለፋቸውን አቶ ኃይሉ ለምክር ቤቶቹ አባላት ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ህገ መንግስት የሚያውቀው የፌደራል እና የክልል መንግስታትን ብቻ መሆኑን ያነሱት አቶ ኃይሉ፤ “ ‘የእዚህ ታክስ ስልጣን ለክልል መንግስታት ተሰጥቶ፤ ክልሎቹ ባላቸው ህገ መንግስታዊ ስልጣን ለአካባቢ መስተዳድሮች ቢሰጡ ይሻላል’ የሚለው አማራጭ በሁለቱም ምክር ቤቶች የቋሚ ኮሚቴዎች ተደግፎ ቀርቧል” ሲሉ የውሳኔ ሃሳቡን ጭብጥ አብራርተዋል።

ቋሚ ኮሚቴዎቹ ሁለተኛውን አማራጭ ያልተቀበሉት በሁለት ምክንያቶች መሆኑን አቶ ኃይሉ ተናግረዋል። የመጀመሪያው ምክንያት ክልሎች የራሳቸውን ወጪ በራሳቸው ገቢ መሸፈን ባልቻሉበት ሁኔታ “የሚሰበሰበውን ውስን ሀብት የጋራ ገቢ አካል ማድረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል” የሚል ነው። በህገ መንግስቱ አንቀጽ 62 ንዑስ አንቀፅ 7 መሰረት፤ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የጋራ ገቢዎች ተካፋይ ሊሆኑ አለመቻላቸው ደግሞ በሁለተኛነት የተቀመጠ ምክንያት ነው።

አቶ ኃይሉ የጠቀሱት የህገ መንግስቱ አንቀጽ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ስልጣን እና ተግባር የሚዘረዝር ነው። ይህ ድንጋጌ የፌዴሬሽን  ምክር ቤት “የክልሎች እና የፌደራሉ መንግስት የጋራ ተብለው የተመደቡ ገቢዎች በሁለቱ መካከል የሚከፋፈሉበትን፤ እንዲሁም የፌደራሉ መንግስት ለክልሎች ድጎማ የሚሰጥበትን ቀመር ይወስናል” ይላል። ዛሬ ለሁለቱ ምክር ቤቶች የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ፤ የንብረት ታክስን የጋራ ገቢ አካል ማድረግ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማን የገቢው ተካፋይ እንዳይሆኑ ስለሚያደርጋቸው “የፍትሃዊነት ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል” ሲል አስፍሯል።

በንብረት ላይ የሚጣለውን ታክስ የተመለከተ የውሳኔ ሃሳብ ከቀረበላቸው በኋላ አስተያየታቸውን የሰነዘሩ አብዛኛዎቹ የምክር ቤት አባላት፤ ታክሱን በባለቤትነት የማስተዳደር ስልጣን ለክልሎች መሰጠቱን ደግፈዋል። በውሳኔ ሃሳቡ ላይ የተለየ አስተያየት የሰጡት የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ የፓርላማ አባላት ናቸው።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ አንዱ የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፤ የንብረት ታክስ አስፈላጊነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል። ዶ/ር ደሳለኝ “መንግስት ተጨማሪ የታክስ አማራጮችን ከማስፋት ይልቅ የወጪ ቅነሳ ፖሊሲ አቅጣጫ መከተል የማይችለው ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል። አብዛኛው የከተማ ነዋሪ የቤት ባለቤት የሚሆነው “በረዥም ጊዜ ብድር እና ቁጠባ” መሆኑን ያወሱት ዶ/ር ደሳለኝ “ ‘የንብረት ታክስ ክፈል ብንለው’  ይችለዋል ወይ?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል።

ሌላኛው የአብን ተወካይ የፓርላማ አባል አቶ አበባው ደሳለው ደግሞ በሁለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ተቀባይነት ያገኘውን አማራጭ ተቃውመው አስተያየት ሰጥተዋል። ሁለተኛውን አማራጭ እንደሚደግፉ የተናገሩት አቶ አበባው፤ የንብረት ታክስ የጋራ ገቢ መሆን “ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የእድገት ልዩነት እንዳይፈጠር ይረዳል” ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል። በአዲስ አበባ እንዲሁም “በጥቂት የክልል ከተሞች” እና በወረዳ ከተሞች መካከል “ከፍተኛ የልማት ልዩነት አለ” ያሉት የፓርላማ አባሉ አማራጩ ልዩነቱን “የበለጠ የሚያሰፋ ነው” የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፤ በንብረት ላይ የሚጣል ታክስ የመንግስትን የታክስ አማራጮች የማስፋት አንድ አካል መሆኑ ጠቅሰዋል። “በሀገራችን የምንሰበስበው የታክስ መጠን ከGDP በታች እና ዝቅተኛ ነው። አሁንም ታክስ በመሰብሰብ ደረጃ በጣም ብዙ ስራ መሰራት አለበት” ሲሉ ተደምጠዋል።

“በሀገሪቱ ንብረት ያፈሩት ሰዎች የተሻለ ገቢ ያላቸው ሰዎች ናቸው” ያሉት አቶ አህመድ፤ የሚጣለው ታክስ ሰዎች ባፈሩት ንብረት ዋጋ መጠን እና ጫናን በማይፈጥር መልኩ እንደሚሆን ገልጸዋል። በንብረት ላይ የሚጣለው ታክስ መጠን ከመወሰኑ በፊት የምክከር መድረኮች እንደሚኖሩም ተናግረዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ በንብረት ላይ የሚጣለው ታክስ አንድ ወጥ እንዲሆን፤ አዋጅ እንደሚወጣ ተናግረዋል። ወደ ፊት በፓርላማው የሚጸድቀው አዋጅ ለክልሎች እንደሚላክ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ክልሎችም ባላቸው ስልጣን ከአዋጁ ጋር “ተመጣጣኝ እና ተቀራራቢነት ያለው የህግ ማዕቀፍ” እንደሚያወጡ አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)  

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]