በእስር ላይ በሚገኙት የኢሰመጉ ሰራተኞች ላይ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገ

በአማኑኤል ይልቃል

ላለፉት ስድስት ቀናት በእስር ላይ በሚገኙት አራት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ሰራተኞች ላይ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገ። የኢሰመጉ ሰራተኞች ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ለመመልከት ለነገ ሐሙስ ጥር 4፤ 2015 በፍርድ ቤት ቀጠሮ ተሰጥቷል። 

የኢሰመጉ ሶስት የሰብአዊ መብቶች ባለሙያዎች እና አንድ አሽከርካሪ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት፤ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች እየተካሄደ የነበረ “የቤት የማፍረስ ዘመቻን ለማጣራት ተሰማርተው” በነበረበት ወቅት እንደሆነ ጉባኤው አስታውቆ ነበር። አራቱ የኢሰመጉ ሰራተኞች ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ታህሳስ 27 በቁጥጥር ስር የዋሉት፤ በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ አስተዳደር ገላን ጉዳን ክፍለ ከተማ እንደሆነ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ገልጿል።

አራቱ የድርጅቱ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር በዋሉ ማግስት፤ በኦሮሚያ ክልል የሰበታ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበው አምስት የምርመራ ቀናት ተፈቅዶባቸው ነበር። ዛሬ ረቡዕ ጥር 3፤ 2015 ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ በቀረቡት የኢሰመጉ ሰራተኞች ላይ፤ መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ 14 የምርመራ ቀናትን መጠየቁን ጠበቃቸው አቶ አዲሱ አሸናፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

መርማሪ ፖሊስ በዛሬው ችሎት፤ ተጠርጣሪዎቹ “ከመስሪያ ቤታቸው ደብዳቤ ሳይዙ በቦታው ላይ ለምርመራ መሰማራታቸውን” ለፍርድ ቤት ማስረዳቱን ጠበቃው ገልጸዋል። ተጠርጣሪዎቹ “ከፖሊስ ፍቃድ ሳያገኙ የፖሊስ ታፔላን ፎቶ አንስተዋል” የሚል ውንጀላ እንደቀረበባቸውም አቶ አዲሱ አክለዋል። የኢሰመጉ ሰራተኞች “በብሔር እና ብሔር መካከል ጠብን በሚቀሰቅስ መልኩ፤ ‘ቤቶች እየፈረሱ ያሉት ለአንድ ብሔር የወገነ በሚመስል መንገድ ነው’ እያሉ ነበር” ሲል መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤት መናገሩን ጠቅሰዋል።

ፖሊስ ባለፈው ሳምንት በችሎት በተፈቀዱለት ቀናት ያከናወናቸውን ተግባራትም ለፍርድ ቤቱ መዘርዘሩን ጠበቃው ተናግረዋል። በስፍራው ላይ ከነበሩ ሰዎች የቃል ማስረጃ መውሰዱን ለፍርድ ቤት ያስረዳው መርማሪ ፖሊስ፤ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ መረጃ ለማግኘት ለመስሪያ ቤታቸው ደብዳቤ መጻፉንም ገልጿል። ፖሊስ የሰነድ ማስረጃዎችን የማሰባሰብ ስራ እያከናወነ በመሆኑ ተጨማሪ የምርመራ ቀናት እንዲፈቀድለትም ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ ማቅረቡን ጠበቃው አስረድተዋል። 

ተጠርጣሪዎቹ “በዋስ ቢወጡ ማስረጃዎች ሊያጠፉ ይችላሉ” በሚል ስጋት በፖሊስ በኩል የተነሳውን ሃሳብ በተመለከተ፤ አቶ አዲሱ መከራከሪያቸውን ለፍርድ ቤቱ ማቅረባቸውን ተናግረዋል። “እነዚህ ሰዎች የሚያጠፉት ሰነድ የለም። ይጠፋሉ የተባሉት ሰነዶችም በማስረጃ የተረጋገጡ አይደሉም” ሲሉ ጠበቃው የፖሊስን አስተያየት ተቃውመዋል። የኢሰመጉ ሰራተኞች “የተጠረጠሩበት ጉዳይ ከ15 ዓመት በላይ የሚያስፈርድ ወይም ከባድ ወንጀል ባለመሆኑ የዋስትና መብት የሚያስከለክል አይደለም” ሲሉ መከራከራቸውንም ጠበቃው ገልጸዋል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የሰበታ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት፤ የፖሊስን የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን ጠበቃው አስታውቀዋል። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው ከዚህ ቀደም ለፖሊስ የተፈቀደው የምርመራ ጊዜ በቂ መሆኑን በመጥቀስ ነው። ተጠርጣሪዎቹ “ከመንግስት በልጠው የሰነድ ማስረጃ ያጠፋሉ ተብሎ እንደማይታመን እና እንደማይገመት” የጠቀሰው ፍርድ ቤቱ፤ “ሌላ መዝገብ በማስከፈት” የዋስትና መብታቸውን መጠየቅ እንደሚችሉም መግለጹንም አክለዋል።

ይህን ውሳኔ መሰረት በማድረግ ዛሬውኑ የዋስትና መዝገብ ተከፍቶ ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ መቅረቡን አቶ አዲሱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጉዳዩን ለመመልከት ለነገ ሐሙስ ጥር 4 ቀን ቀጠሮ መስጠቱን ጠቁመዋል። አራት ሰራተኞቹ የታሰሩበት ኢሰመጉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ እስሩ “የህግ ስነ-ስርዓትን ያልተከተለ” እና “ህገ-ወጥ ድርጊት” ሲል ኮንኖታል። ሰራተኞቹም “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ” ጥሪ አቅርቧል። 

መቀመጫውን በለንደን ያደረገው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትላንት ጥር 2 ባወጣው መግለጫ፤ የኢሰመጉ ሰራተኞ “በአፋጣኝ እና ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ” እንዲፈቱ በተመሳሳይ መልኩ ጠይቋል። የተቋሙ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዳይሬክተር ቲገረ ቻጉታህ “እነዚህ አራቱ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ይኼ ነው የሚባል አንድም ወንጀል አልፈጸሙም። የአዲስ አበባ ድሃ ነዋሪዎች በግዳጅ መፈናቀልን የመሰነድ ጠቃሚ ስራ እየሰሩ ነበር” ማለታቸው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።

አራቱ የኢሰመጉ ሰራተኞች ቀድሞውንም መታሰር እንዳልነበረባቸው የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ “ወሳኝ የሰብዓዊ መብቶች ስራ በማከናወኑ ማንም ሊታሰር አይገባም” በማለት የኢትዮጵያን መንግስት እርምጃ ነቅፈዋል። ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የኢሰመጉ ሰራተኞች “በሰብዓዊ መብቶች ስራቸው አንዳች በቀል” እንዳይገጥማቸው ሊያረጋግጡ እንደሚገባ ተናግረዋል። የመንግስት ባለስልጣናት የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾችን ማስፈራራት እና ማዋከብ በአፋጣኝ ሊያቆሙ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሰሩ 12 የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅቶች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባወጡት የጋራ መግለጫም ተመሳሳይ ሃሳብ አንስተዋል። የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅቶቹ የኢሰመጉ ሰራተኞችን እስር የገለጹት፤ “በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ላይ የሚሰሩ ሌሎች ተቋማትን የሚያሸማቅቀ ድርጊት” በማለት ነው። ድርጅቶቹ በዚሁ መግለጫቸው የኢሰመጉ ሰራተኞች “በአስቸኳይ እንዲፈቱ” እና “የዘፈቀደ እስራቱን” የፈጸሙ የመንግስት አካላት በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)