በአማኑኤል ይልቃል
ለአንድ ሳምንት ያህል በእስር ላይ የቆዩት አራት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ሰራተኞች፤ የገንዘብ ዋስትና በማስያዝ እንዲለቀቁ በፍርድ ቤት ተወሰነላቸው። በኦሮሚያ ክልል የሰበታ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ዋስትናውን የፈቀደው፤ ዐቃቤ ህግ የሰራተኞቹን በዋስ መውጣት እንደማይቃወም በመግለጹ ነው።
ፍርድ ቤቱ የኢሰመጉን ሰራተኞች ጉዳይ የተመለከተለው፤ ትላንት በዋለው ችሎት ፖሊስ የጠየቀው ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ውድቅ ከተደረገ በኋላ በአዲስ መዝገብ አቤቱታ በመቅረቡ ነበር። የኢሰመጉ ሰራተኞች በጠበቃቸው በኩል ትላንት ከሰዓት በኋላ ያቀረቡት አቤቱታ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው የሚጠይቅ ነው።
ይህንን አቤቱታ ዛሬ ሐሙስ ጥር 4 ረፋዱን የተመለከተው የሰበታ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት፤ ዐቃቤ ህግ በአቤቱታው ላይ ያለውን አስተያየት እንዲሰጥ መጠየቁን የሰራተኞቹ ጠበቃ አቶ አዲሱ አሸናፊ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አስተያየት የተጠየቀው አቃቤ ህግም “ምርመራውን ስለጨረስን እና የዋስ መብት የማያስከለክል ስለሆነ በዋስ ቢወጡ አንቃወምም” የሚል ምላሽ መስጠቱን ጠበቃው ገልጸዋል።
ይህንን ተከትሎም ፍርድ ቤቱ የኢሰመጉን ሰራተኞች “ደመወዝ እና ኢኮኖሚያዊ አቅም” በግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የገንዘብ ዋስትና መፍቀዱን አስታውቀዋል። በዚህም መሰረት ሶስቱ የኢሰመጉ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች የአራት ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና ሲፈቀድላቸው፤ የድርጅቱ አሽከርካሪ የሆነው ሰራተኛ ደግሞ በሶስት ሺህ ብር የገንዘብ ዋስትና እንዲወጣ መወሰኑን አስረድተዋል።
ከዛሬው ችሎት መጠናቀቅ በኋላ ሰራተኞቹን ከእስር ለማስፈታት “አስፈላጊ ሂደቶች” እየተፈጸሙ መሆኑን አቶ አዲሱ ገልጸዋል። ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ታህሳስ 27 በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት አራቱ የኢሰመጉ ሰራተኞች በእስር ላይ የቆዩት፤ በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ አስተዳደር ገላን ጉዳን ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ነው።
አራቱ ሰራተኞች በፖሊስ የተያዙት፤ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ አካባቢዎች እየተካሄደ የነበረ “የቤት የማፍረስ ዘመቻን ለማጣራት” በተሰማሩበት እንደሆነ ኢሰመጉ አስታውቆ ነበር። በሰበታ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት በትላትናው ዕለት በነበረ ችሎት፤ ሰራተኞቹ “ከመስሪያ ቤታቸው ደብዳቤ ሳይዙ በቦታው ላይ ለምርመራ ተሰማርተዋል” ሲል ፖሊስ ውንጀላ አቅርቦ እንደነበር ጠበቃቸው አቶ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የኢሰመጉ ሰራተኞች “ከፖሊስ ፍቃድ ሳያገኙ የፖሊስ ታፔላን ፎቶ አንስተዋል” የሚል ተጨማሪ ውንጀላም በትላንቱ ችሎት ቀርቦባቸው እንደነበር ጠበቃቸው ገልጸዋል። ሰራተኞቹ “በብሔር እና ብሔር መካከል ጠብን በሚቀሰቅስ መልኩ፤ ‘ቤቶች እየፈረሱ ያሉት ለአንድ ብሔር የወገነ በሚመስል መንገድ ነው’ እያሉ ነበር” ሲል ፖሊስ በትላንትናው የችሎት ውሎ መናገሩንም ጠቅሰው ነበር።
ሰራተኞቹ በዋስትና ከወጡ በኋላ ስለሚኖረው ሂደት የተጠየቁት አቶ አዲሱ፤ ይሄ የሚታወቀው ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ህግ ካቀረበ በኋላ መሆኑን አስረድተዋል። “አቃቤ ህግ [መዝገቡን ተመልክቶ] የሚያስከስስ ከሆነ ሊከስ ይችላል። የማያስከስስ ከሆነ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ፋይሉን ሊዘጋ ይችላል” ሲሉ ለ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)