በአማኑኤል ይልቃል
ኢትዮ ቴሌኮም በደቡብ ሱዳን ያለውን የቴሌኮም ገበያ የሚቀላቀልበትን አማራጭ ለመለየት የአዋጪነት ጥናት እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ። ተቋሙ በሚያደርገው ጥናት በደቡብ ሱዳን በአገልግሎት ሰጪነት አልያም በቴሌኮም መሠረተ ልማት አቅራቢነት ለመግባት የተሻለውን አማራጭ እንደሚለይ ገልጿል።
በ2015 በጀት ዓመት “መሪ” የተሰኘ እና ለቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት የሚመራበትን የዕድገት ስትራቴጂ መተግበር የጀመረው ኢትዮ ቴሌኮም፤ በዚህ ስትራቴጂው ከያዛቸው እቅዶች ውስጥ አንዱ የሚሰማራበትን “የቴሌኮም ገበያ ማስፋት” ነው። የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የተቋሙን የስድስት ወራት አፈጻጸም በተመለከተ ትላንት ሐሙስ ጥር 4፤ 2015 በሰጡት መግለጫ ላይ፤ ከዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ጥያቄ ከጋዜጠኞች ቀርቦላቸው ነበር።
በዋና ስራ አስፈጻሚዋ የተመራ የተቋሙ ከፍተኛ አመራር ቡድን ባለፈው ታህሳስ ወር በደቡብ ሱዳን ስላደረገው ጉብኝት የተጠየቁት ፍሬሕይወት፤ “የገቢ ምንጫችንን ማስፋት፣ የምንሰራበትን ገበያ ማስፋት በስትራቴጂያችን የተያዘ [ጉዳይ] ነው። ስትራቴጂውን ይፋ ስናደርግ እንደዚህ አይነት ነገሮች እንደሚኖሩን አሳውቀን ነበር” ብለዋል።
እንደ ፍሬሕይወት ገለጻ፤ የተቋሙ አመራሮች ጉብኝት አንደኛው ምክንያት ደቡብ ሱዳን ከዓለም አቀፍ የቴሌኮም የፋይበር መስመር ጋር በኢትዮ ቴሌኮም በኩል ለመገናኘት ፍላጎት ያላት መሆኑ ነው። ደቡብ ሱዳን አብዛኛውን የቴሌኮም አገልግሎት የምታገኘው የሌሎች አገራት ሳተላይትን በመጠቀም መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጹት የተቋሙ ቺፍ ኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ መሳይ ውብሸት፤ በዚህ ምክንያት በአገሪቱ ያለው የቴሌኮም አገልግሎት ዋጋ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በደቡብ ሱዳን ያለው የቴሌኮም ገበያ “የዋጋ ተመጣጣኝነት ጥያቄ ያለበት” መሆኑን በትላንቱ መግለጫቸው የጠቀሱት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ “ይህ ለእኛ መልካም አጋጣሚ ነው ብለን እናስባለን” ብለዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት አራት ዓመታት በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ እስከ 86 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ማድረጉ ይታወሳል።
ተቋሙ ለሚያቀርበው የኢንተርኔት አገልግሎት በዋነኛነት የሚጠቀመው ዓለም አቀፍ ባህር ጠለቅ የኢንተርኔት መገናኛ መስመር መሆኑ፤ ደቡብ ሱዳን ከምትጠቀምበት ሳተላይት በረከሰ መልኩ አገልግሎት ለማቅረብ እንደሚያስችለው አቶ መሳይ አስረድተዋል። በባህር ውስጥ የተዘረጋው ዓለም አቀፍ የኢንተርኔት መገናኛ መስመር ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው፤ በጅቡቲ፣ በኬንያ፣ እና በሱዳን በኩል በተዘረጉ የፋይበር መስመሮች ነው።
መስመሩ ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ በኋላ ኢትዮ ቴሌኮም ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የፋይበር መስመሮችን በመዘርጋት የቴሌኮም አገልግሎትን እንደሚያቀርብ አቶ መሳይ አብራርተዋል። የተቋሙ ቺፍ ኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር “ፋይበር መዘርጋቱ አንድ ጊዜ ወጪ ሊያስወጣ ይችላል እንጂ፤ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግል ስለሆነ ኢንተርኔት በቀላል ዋጋ ማቅረብ ያስችላል” ሲሉ ደቡብ ሱዳን ከምትጠቀምበት ሳተላይት አንጻር አዋጪነቱን ገልጸዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን የፋይበር መስመር ከኢትዮጵያ ወደ ደቡብ ሱዳን በመዘርጋት፤ ከዓለም አቀፉ የኢንተርኔት መገናኛ መስመር ጋር እንዲያገናኝ ጥያቄ መቅረቡን አክለዋል። ተቋሙ እስከ ደቡብ ሱዳን ድንበር ድረስ ይህንን መስመር ቢዘረጋም እንኳ፤ በሀገሪቱ ውስጥ ይህንን ተቀብሎ ለማሰራጨት የሚያችል መሰረተ ልማት እንደሌለ ፍሬሕይወት በትላንቱ መግለጫቸው ተናግረዋል።
“ለሌላ ጎረቤት ሀገራት ስንሸጥ አቅሙ ስላላቸው በፋይበር ዘርግተን እንሸጣለን። እነሱ ጋር ግን ይህንን የሚቀበል የለም” ሲሉም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ በደቡብ ሱዳን ያለውን የተለየ ሁኔታ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ኢትዮ ቴሌኮም ይህ መሰረት ልማት የሚሟላበትን እና ከደቡብ ሱዳን የቀረበው ጥያቄ “መሬት የሚወርድበትን” መንገድ ለመፈለግ ጥናት እያደረገ መሆኑን ፍሬሕይወት ተናግረዋል።
የተቋሙ ቺፍ ኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ መሳይ፤ የቴሌኮም መሰረተ ልማቱን “እኛ እራሳችን ነው የምንገነባው ወይስ ከሌሎች ጋር ተባብረን ነው የምንሰራው የሚለውን ጥናቱ ይመልሳል” ሲሉ አብራርተዋል። ኢትዮ ቴሌኮም በደቡብ ሱዳን የመሰረተ ልማት ዝርጋታውን ለማከናወን በሀገሪቱ የቴሌኮም ኦፕሬተርነት ፍቃድ ማግኘት እንዳለበት አቶ መሳይ አመልክተዋል። አሁን እየተደረገ ያለው ጥናት ይህ አማራጭ አዋጭ መሆኑን የሚያረጋግጥ ከሆነ፤ ኢትዮ ቴሌኮም “ራሱን ችሎ” በደቡብ ሱዳን በቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢነት ስራ ሊሰማራ እንደሚችል አመልክተዋል።
ቀድሞውኑ በሀገሪቱ የቴሌኮም ዘርፍ ፈቃድ ካላቸው ኩባንያዎች ጋር በትብብር መስራት የሚለውን አማራጭም ተቋሙ ሊከተል እንደሚችል መሆኑን ቺፍ ኮሚዩኒኬሽን ኦፊሰሩ ጠቁመዋል። አቶ መሳይ ተቋሙ ሁለት አማራጮች እንዳሉት ቢናገሩም፤ በ2013 ዓ.ም የተሻሻለው የኢትዮ ቴሌኮም ማቋቋሚያ ደንብ ግን ተቋሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢንቨስትመንት መሳተፍ የሚችለው “የአክስዮን ድርሻ በመያዝ” እንደሆነ ደንግጓል።
ኢትዮ ቴሌኮም የደቡብ ሱዳን የቴሌኮም ገበያ ውስጥ የሚገባበትን መንገድ ለመወሰን በሚደረገው ጥናት፤ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው የጸጥታ ሁኔታ፣ የመንግስት አሰራር እና የሰው ኃይል ከግምት ውስጥ እንደሚገቡ አቶ መሳይ ገልጸዋል። በሀገሪቱ ሀብትን በተፈለገው መንገድ አንቀሳቅሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ያለ አመቺነትም የጥናቱ አካል እንደሆነ አመልክተዋል።
ኢትዮ ቴሌኮም ከደቡብ ሱዳን ውጪ በሌላ ጎረቤት ሀገር የቴሌኮም ገበያ ውስጥ ለመግባት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ፍሬሕይወት በትላንቱ መግለጫ ላይ ጠቁመዋል። ተቋሙ ከጅቡቲ የቴሌኮም ኩባንያ ጋር በተያያዘ “የሪፎርም ስራዎች” ላይ ለመስራት ንግግር ማድረጉን ገልጸው፤ “[በጅቡቲ] ገበያችንን ከማስፋት አንጻር እየሰራን ያለነው ስራ ፍሬ ሲያፈራ የምናሳውቃችሁ ይሆናል” ሲሉ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)