በሃሚድ አወል
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚያቀርቧቸውን የአስፈጻሚ አካላትን ሹመት ለማጽደቅ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ ማክሰኞ ስብሰባ ሊያደርግ ነው። ሁለት የፓርላማ አባላት የነገው አጀንዳ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቧቸውን ተሿሚዎች ሹመት ማጽደቅ” መሆኑን የሚገልጽ መልዕክት እንደደረሳቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
የተወካዮች ምክር ቤት ለመገናኛ ብዙሃን ዛሬ ባሰራጨው መረጃም ነገ ከቀኑ 7:30 ጀምሮ በሚካሄድ ስብሰባ ፓርላማው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡ ሹመቶችን መርምሮ እንደሚያጸድቅ አስታውቋል። አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የፓርላማ አባል፤ በምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት በኩል የተላለፈው መልዕክት “ማንም የምክር ቤት አባል እንዳይቀር” የሚል ማሳሰቢያ መያዙን አክለዋል።
አራት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ካቢኔ አባላት ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ከኃላፊነት መነሳታቸው ይታወሳል። ከኃላፊነት ተነስተው “በክብር ሽኝት” እንደተደረገላቸው የተገለጹት ሚኒስትሮች፤ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስተሯ ዳግማዊት ሞገስ፣ የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ እና የግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴን ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ተፈሪ ፍቅሬም እንደዚሁ ከኃላፊነታቸው መሰናበታቸው መገለጹ ይታወሳል። ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ከሶስት ሳምንት በፊት ሹመት ከሰጧቸው አስራ አራት አምባሳደሮች መካከል አቶ ኡመር ሁሴን እና አቶ ተፈሪ ፍቅሬ ይገኙበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሚኒስትር ደረጃ ለመጨረሻ ጊዜ ሹመት የሰጡት ከአምስት ወራት በፊት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ላይ ነበር። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመት የተሰጣቸው፤ አቶ ላቀ አያሌውን ተክተው የገቢዎች ሚኒስትር የሆኑት ወይዘሮ አይናለም ንጉሴ ናቸው። አቶ ላቀ የሚኒስትርነት ኃላፊነታቸውን የለቀቁት፤ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ለመከታተል ወደ ውጭ ሀገር ስለሚጓዙ መሆኑ በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
ገዢው ብልጽግና ፓርቲ ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ማሸነፉን ተከትሎም፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ካቢኔ አዲስ አባላትን በማካተት እንደገና መደራጀቱ ይታወሳል። ባለፈው ዓመት መስከረም ወር በተደረገው በዚህ የካቢኔ ሹም ሽር፤ ሶስት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በሚኒስትርነት ተሹመዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)