አቶ ቴዎድሮስ ምህረት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ

• የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነዋል

በሃሚድ አወል እና በአማኑኤል ይልቃል

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ቤት መምህር የነበሩት ረዳት ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ምህረት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትን በፕሬዝዳንትነት እንደሚሩ ተሾሙ። ላለፉት 16 ዓመታት በተለያዩ ደረጃዎች ባሉ የፌደራል ፍርድ ቤቶች በዳኝነት ያገለገሉት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ የምክትል ፕሬዝዳንትነት ሹመት አግኝተዋል።

ሁለቱ የህግ ባለሙያዎች ሹመቱን ያገኙት፤ ላለፉት አራት ዓመታት ጠቅላይ ፍርድ ቤትን በፕሬዝዳንትነት የመሩት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ እና ምክትላቸው አቶ ሰለሞን አረዳ “በፍቃዳቸው ከስራቸው መልቀቃቸውን” ማስታወቃቸውን ተከትሎ ነው። ወ/ሮ መአዛ እና አቶ ሰለሞን የስራ መልቀቂያቸውን ለፓርላማ አስገብተው እንደነበር ዛሬ ማክሰኞ ጥር 9፤ 2015 በተካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገልጿል። 

በዚሁ ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአመራርነት የሾሟቸው ግለሰቦች የተመለከተ የውሳኔ ሃሳብ ቀርቦ ምክር ቤቱ ድምጽ ሰጥቶበታል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሹመት የተመለከተውን የውሳኔ ሀሳብ በንባብ ያሰሙት በፓርላማ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ናቸው።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተመለከተው፤ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትነት በዕጩነት የቀረቡትን የአቶ ቴዎድሮስን ሹመት ነው።  በህግ ትምህርት የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያገኙት አቶ ቴዎድሮስ፤ በተማሩበት ዩኒቨርስቲ ለሁለት ዓመት ገደማ የህግ አገልግሎት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል። በኮንስትራክሽን እና ቢዝነስ ባንክ በነገረ ፈጅነት እና በአቢሲኒያ ባንክ በከፍተኛ ነገረ ፈጅነት የሰሩት አቶ ቴዎድሮስ፤ የብርሃን ኢንሹራንስ የቦርድ ሰብሳቢ ነበሩ።

የአዲሱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሹመት በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው፤ በሶስት ድምፅ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምጽ ነው። በዛሬው ስብሰባ የተገኙ 295 የፓርላማ አባላት ድምጽ ከሰጡ በኋላ አዲሱ ተሿሚ ቃለ መሃላ ፈጽመዋል። የቃለ መሃላ ስነ ስርዓቱን ያስፈጸሙት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ አቶ ብርሃኑ አመነው ናቸው።

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾሙት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ በተመሳሳይ መልኩ የቃለ መሃላ ስነ ስርዓት አካሄደዋል። ሹመታቸው በፓርላማ አባላት ሙሉ ድምጽ የጸደቀው ወ/ሮ አበባ፤ በህግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የያዙት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው። አዲሷ ምክትል ፕሬዝዳንት በተመሳሳይ የትምህርት ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪያቸው ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሰቲ አግኝተዋል።    

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ የነበሩት ወ/ሮ አበባ፤ በፌደራል ስነምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአቃቤ ህግነትም ሰርተዋል። በ1999 ዓ.ም የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ተቀላቅለውም ለዘጠኝ ዓመታት የፌደራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው አገልግለዋል። ከ2008 እስከ 2011 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዳኝነት ሰርተዋል። 

ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የዛሬውን ሹመት እስካገኙበት ቀን ድረስ ደግሞ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኝነት በመስራት ላይ ነበሩ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወ/ሮ አበባን ጨምሮ 16 ዳኞችን በጠቅላይ ፍርድ ቤት በዳኝነት እንዲያገለግሉ የሾማቸው በሰኔ 2011 ዓ.ም ነበር። 

በዛሬው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራርነት ባቀረቧቸው በሁለቱም ተሿሚዎች ዕጩነት ላይ የጎላ አስተያየት ከምክር ቤቱ አባላት አልተደመጠም። አንድ የፓርላማ አባል በአንጻሩ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መአዛ እና ምክትላቸው አቶ ሰለሞን ስራቸውን የለቀቁበት ምክንያት እንዲገለጽ ጠይቀዋል።

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

እኚሁ የምክር ቤት አባሉ፤ “እንደሚታወቀው ከለውጡ በፊት ፍትህ ተቋማት ራሳቸውን ችለው አልነበረም እየተመሩ የነበረው፡፡ ተገደው የሚፈጽሙት ነገር እንደነበር እናውቃለን፡፡ ነገር ግን አሁንም እነዚህ ፕሬዝዳንቶች ሁለቱም የለቀቁበት ምክንያት እውነት በፈቃደኝነት ነው ወይ? ወይንስ የፍትህ ስርዓቱን harass የሚያደርግ ነገር ተፈጥሮባቸው ነው?” የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡

ለፓርላማ አባሉ ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤው ታገሰ ጫፎ፤ ከስራ የመልቀቅ ጉዳይ “በመደበኛነት የሚቀርብ ጥያቄ ነው” ሲሉ አስታውሰዋል፡፡ አፈ ጉባኤው አክለውም የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቷ እና ምክትላቸው፤  “በግል ጉዳያችን ምክንያት ስራችንን መቀጠል ስለማንችል ይሄ [መልቀቂያችን] ተቀባይነት እንዲያገኝ እንጠይቃለን” በማለት ደብዳቤ መጻፋቸውን ገልጸዋል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)