ከሚኒስትርነታቸው የተሰናበቱት ዳግማዊት ሞገስ፤ የአፍሪካ ህብረት የሰላም ፈንድ ሴክሬተሪያትን በዳይሬክተርነት ሊመሩ ነው 

በአማኑኤል ይልቃል

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትርነት መሰናበታቸው የተገለጸው ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ፤ የአፍሪካ ህብረት የሰላም ፈንድ ሴክሬተሪያትን በዳይሬክተርነት ለመምራት ተወዳድረው መመረጣቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ዳግማዊት በአፍሪካ ህብረት በዳይሬክተርነት ለመቀጠር ያስፈልጋቸው የነበረውን “የመንግስት የውክልና ፈቃድ” ከኢትዮጵያ መንግስት ማግኘታቸውንም ለእርሳቸው ቅርበት ያላቸው ምንጮች አስታውቀዋል።

የአፍሪካ ህብረት ለሚያከናውናቸው የሰላም እና የጸጥታ እንቅስቃሴዎች የፋይናንስ ድጋፍ የማድረግ ኃላፊነት የተጣለበት የሰላም ፈንድ የተቋቋመው በ1985 ዓ.ም ነው። በአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የጸጥታ ምክር ቤት ማቋቋሚያ ፕሮቶኮል መሰረት የተመሰረተው ይህ ፈንድ፤ ለ26 ዓመታት ገደማ እምብዛም ትኩረት ሳይሰጠው ቆይቷል። ህብረቱ የሰላም ፈንዱ እንቅስቃሴዎች መልሰው እንዲያንሰራሩ ያደረገው ከ2011 ዓ.ም በኋላ ነው።

የሰላም ፈንዱ፤ በአፍሪካ የሚከሰቱ ግጭቶችን የመከላከል፣ ከተከሰቱም በኋላ የመቆጣጠር እና መፍትሔ የማበጀት እንዲሁም በአህጉሪቱ ለሚከሰቱ ቀውሶች አፋጣኝ እና ውጤታማ ምላሾችን የማመቻቸት ኃላፊነት ያለው የአፍሪካ ሰላም እና ጸጥታ አርክቴክቸር ስትራቴጂካዊ ማዕቀፍ አካል ነው። በአፍሪካ ግጭቶች እንዳይቀሰቀሱ ለሚደረጉ የቅደመ መከላከል የዲፕሎማሲ ጥረቶች እና የሽምግልና ሂደቶች የሰላም ፈንዱ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል። የአፍሪካ ህብረት የሚያከናውናቸው የሰላም ድጋፍ ስራዎችም የሰላም ፈንዱ ድጋፍ ከሚያደርግባቸው የትኩረት መስኮች ውስጥ የተካተቱ ናቸው።

የአፍሪካ ህብረት የሰላም ፈንድ የተቋቋመባቸውን ዓላማዎች የሚያስፈጽሙ አምስት አካላት አሉት። ከእነዚህ አካላት ውስጥ የፈንዱን የዕለት ተዕለት ስራዎች የማከናወን ኃላፊነት የተጣለበት፤ በዳይሬክተር የሚመራው የተቋሙ ሴክሬተሪያት ነው። የሰላም ፈንዱ በአዲስ መልክ እንቅስቃሴ ከጀመረ አራት ዓመታት ቢቆጠሩም፤ ሴክሬተሪያቱን የሚመራ ዳይሬክተር ግን እስካሁን ሳይቀጠር ቆይቷል። 

የፈንዱን ወደ ስራ የማስገባት እንቅስቃሴዎችን የሚከታተለው የተቋሙ ባለአደራ ቦርድ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ባወጣው መግለጫ፤ ለሴክሬተሪያቱ ዳይሬክተር የመቅጠር ሂደት መጀመሩን አስታውቆ ነበር። ይህ የዳይሬክተር የቅጥር ሂደት “ብቃትን መሰረት ያደረገ፣ ክፍት እና ግልጽ” አሰራርን እንደሚከተል በፈንዱ ማቋቋሚያ ደንብ ላይ ሰፍሯል። 

እስካለፈው ሳምንት ድረስ የኢትዮጵያ ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን ሲመሩ የቆዩት ወይዘሮ ዳግማዊት፤ የአፍሪካ ህብረት የሰላም ፈንድ ሴክሬተሪያትን በዳይሬክተርነት ለመምራት “በመደበኛ የቅጥር ሂደት እና ውድድር” ማለፋቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቀዋል። ሚኒስትሯ በዚህ ቦታ ለመወዳደር ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል “የውክልና ፈቃድ” ያስፈልጋቸው እንደነበር የጠቀሱት ምንጮቹ፤ ይህንኑ ይሁንታ ከመንግስት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል። 

አዲሱ ስራቸውን በቀጣዩ የካቲት ወር እንደሚጀምሩ የሚጠበቁት ዳግማዊት፤ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ እንደሚሆን ምንጮች አክለዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ካቢኔ ውስጥ በሚኒስትርነት ለአራት ዓመታት የሰሩት ወይዘሮ ዳግማዊት፤ አብዛኛውን የመንግስት የስራ ኃላፊነት ዘመናቸውን ያሳለፉት በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ነው። በመስተዳድሩ በነበራቸው ቆይታ ከክፍለ ከተማ ስራ አስፈጻሚነት እስከ ምክትል ከንቲባነት ባሉ የኃላፊነት ቦታዎች ሰርተዋል። 

ወይዘሮ ዳግማዊት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድርን የተቀላቀሉት፤ በ2001 ዓ.ም የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ስራ አስፈጻሚነትን በመረከብ ነበር። ዳግማዊት በፌደራል መንግስት ሹመት ከማግኘታቸው በፊት በነበሩት ዓመታት የአዲስ አበባ ከተማ አራት ቢሮዎችን በኃላፊነት እና በምክትል ኃላፊነት መርተዋል። የከተማ አስተዳደሩን የንግድና ኢንዱስትሪ እንዲሁም የአቅም ግንባታ ቢሮዎች ምክትል ኃላፊ የነበሩት ዳግማዊት፤ የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮን እና የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮን በኃላፊነት አስተዳድረዋል። 

ከሐምሌ 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ወራት ያህል ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማን በምክትል ከንቲባነት አገልግለዋል። በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ያልነበሩት አቶ ታከለ ኡማ፤ የምክትል ከንቲባ ማዕረግ ይዘው ከተማዋን በከንቲባነት ይመሩ ነበር። ዳግማዊት የትራንስፖርት ሚኒስትር በመሆን ወደ ፌደራል የተዛወሩት በጥቅምት 2011 ዓ.ም ነበር። 

ከአዲስ አበባ ወደ ፌደራል፣ ከፌደራል ወደ አህጉራዊ ተቋም የተሻገሩት ዳግማዊት፤ የስራ መነሻቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ነው። ዳግማዊት በረዳት ምሩቅ ደረጃ በመምህርነት ስራ የጀመሩት፤ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ካገኙበት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው። ዳግማዊት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የያዙት በህዝብ አመራር እና ልማት አስተዳደር ነው። በህዝብ አስተዳደር እና ፖሊሲ ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ዳግማዊት በአድማስ ዩኒቨርስቲም በመምህርነት አገልግለዋል።

በሚኒስትርነት ለአራት ዓመታት የሰሩት ዳግማዊት ከኃላፊነታቸው ተነስተው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሽኝት የተደረገላቸው ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ጥር 6፤ 2015 ነበር። በዕለቱ እርሳቸውን ጨምሮ አራት የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የካቢኔ አባላት ተመሳሳይ ሽኝት ተደርጎላቸዋል። ከሽኝቱ በኋላ ሚኒስትሯ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት “የምወዳት ሀገሬ ኢትዮጵያን እና ህዝቤን በታላቅ ኃላፊነት ለማገልገል በመታደሌ ደስታዬ ወደር የለውም” ብለው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)