ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አዲስ የብሔራዊ ባንክ ገዢ እና ሶስት ሚኒስትሮች ሾሙ

በሃሚድ አወል

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ላለፈው አራት ዓመት ከመንፈቅ የብሔራዊ ባንክ በገዢነት ሲያስተዳድሩ የቆዩትን ዶ/ር ይነገር ደሴ ከኃላፊነት አንስተው በምትካቸው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩት አቶ ማሞ ምህረቱን ሾሙ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ሳምንት ከኃላፊነታቸው በተሰናበቱ ሚኒስትሮች ምትክ ሹመቶች ሰጥተዋል።

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዢ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ ወደፊት ከመጡ ግለሰቦች መካከል አንዱ ናቸው። መንግስት ባለፉት አምስት ዓመታት ባደረጋቸው የኢኮኖሚ ሪፎርሞች ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ የሚነገርላቸው አቶ ማሞ ምህረቱ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት ውስጥ የመጀመሪያውን የኃላፊነት ቦታ ያገኙት በነሐሴ 2010 ዓ.ም ነበር። 

በጊዜው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የፖሊሲ ሪፎርም አማካሪ እና የዓለም ንግድ ድርጅትና የአካባቢያዊ ውህደት ድርድሮች ዋና ተደራዳሪ ሆነው ከተሾሙ በኋላ በኃላፊነቱ ላይ ለሶስት ዓመት ከመንፈቅ ቆይተዋል። አቶ ማሞ በብሔራዊ ባንክ ገዢነት እስከተሾሙበት ጊዜ ድረስ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ 27 የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በስሩ የያዘውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግን በዋና ስራ አስፈጻሚነት ሲመሩ ቆይተዋል። 

ዛሬ አርብ ጥር 12፤ 2015 ይፋ በተደረገው የከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ሹመት፤ ለሶስት የፌደራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አዳዲስ ሚኒስትሮች ተሹመዋል። በዚህም መሰረት በብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማህበራት ዘርፍ ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር አለሙ ስሜ፤ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ሆነዋል። ዶ/ር አለሙ፤ ከሚኒስትርነታቸው ከተሰናበቱ በኋላ የአፍሪካ ህብረት የሰላም ፈንድ ሴክሬተሪያት ዳይሬክተር የመምራት ኃላፊነት እንደሚረከቡ የሚጠበቁትን ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስን ይተካሉ። 

ዶ/ር አለሙ ስሜ በፌደራል ደረጃ ሹመት ሲያገኙ ይህ የመጀመሪያ አይደለም። በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን ዘመን የማዕድን የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር እንዲሁም የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ነበሩ። ብልጽግና ፓርቲ ከመመስረቱ በፊት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ጽህፈት ቤት ኃላፊ የነበሩት ዶ/ር አለሙ፤ የአሁኑ ሹመታቸውን ከማግኘታቸው በፊት ያለፉትን ዓመታት ያሳለፉት በገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማህበራት ዘርፍን በኃላፊነት በመምራት ነው። 

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ሀብታሙ ተገኝ፤ አቶ ታከለ ኡማን ተክተው የማዕድን ሚኒስትርነት ሹመትን አግኝተዋል። አቶ ታከለ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ቅዳሜ ከተሰናበቱ በኋላም ጭምር በስራ ላይ እንደነበሩ የሚያሳይ መረጃ ከትላንት በስቲያ በግል የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አጋርተው ነበር።  

በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አቶ ኡመር ሁሴን ይዘውት የነበረውን የግብርና ሚኒስትርነት ቦታ እንዲረከቡ ሹመት የተሰጣቸው  ዶ/ር ግርማ አመንቴ ናቸው። ዶ/ር ግርማ ይህን ሹመት ከማግኘታቸው በፊት በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመንግስት የልማት ተቋማት ክላስተር አስተባባሪ ሆነው በመስራት ላይ ነበሩ።

ከክልል ወደ ፌደራል የኃላፊነት ቦታ የመጡት ዶ/ር ግርማ አመንቴም ለሚኒስትርነት አዲስ አይደሉም። ዶ/ር ግርማ እስከ ሚያዚያ 2010 ዓ.ም የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል። ከአምስት አመት ገደማ በፊት የሚኒስትርነት ቦታቸውን ለተሾመ ቶጋ አስረክበው፤ የኦሮሚያ ክልል ከተማ ልማት እና ቤቶች ቢሮ ኃላፊ በመሆን ወደ ክልል ተዘዋውረዋል። የዶ/ር ግርማን ጨምሮ የሶስቱ አዲስ ሚኒስትሮች ሹመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቅ ይጠበቅበታል።

ከኃላፊነታቸው የተሰናበቱት ሶስት ሚኒስትሮች ጋር ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በተሸኙት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ተፈሪ ፍቅሬ ምትክም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ዛሬ አዲስ ግለሰብ ሾመዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊነትን ጭምር በሚያካትተው በዚህ የኃላፊነት ቦታ የተሾሙት ወ/ሮ አለምፀሐይ ጳውሎስ ናቸው።  

አለምፀሐይ ካለፈው ዓመት መስከረም ወር ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የአገልግሎቶች እና መልካም አስተዳደር ክትትል ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል። ተሿሚዋ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከመምጣታቸው በፊት በጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው ሰርተዋል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ሆነውም አገልግለዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዛሬው ዕለት ከሰጧቸው ስምንት ሹመቶች ውስጥ ሁለቱ የአማካሪ ሚኒስትርነት ኃላፊነት የያዙ ናቸው። በዚህ መሰረት ላለፉት አራት ዓመታት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር የነበሩት ታዬ አጽቀስላሴ የውጭ ፖሊሲ አማካሪ ሆነው ተሹመዋል። 

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የያዙት ታዬ፤ የተመድ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነው ከመሾማቸው በፊት በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተርም ነበሩ። የህገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን አባል የነበሩት ታዬ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ከእንግሊዙ ላንካስተር ዩኒቨርሲቲ በዓለምቀፍ ግንኙነትና ስትራቲጂያዊ ጥናት አግኝተዋል።

ተመሳሳይ ሹመት ያገኙት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚኒስትር ሆነዋል። ዲያቆን ዳንኤል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ ጊዜ ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ በመሆን ሲሰሩ ቆይተዋል። ለንባብ ባበቋቸው በርካታ መጽሐፍት የሚታወቁት ዲያቆን ዳንኤል፤ አዲስ አበባ ከተማን ወክለው ፓርላማ ከገቡ 23 ተወካዮች ውስጥ ብቸኛው የግል ተመራጭ ናቸው።    

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ዶ/ር አለሙ ስሜ ከዚህ ቀደም በአስተባባሪነት ሲመሩ ለቆዩት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከልም አዲስ ኃላፊ ሹመዋል። አዲሱ ተሿሚ የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ መለሰ ዓለሙ ናቸው። አቶ መለሰ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያን እንዲመሩ የተሾሙት በሚኒስትር ማዕረግ ነው።
(ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለዋል]