በሃሚድ አወል
ለአምስት ዓመታት ያህል ጭማሪ ማሻሻያ ሳይደረግበት የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ የአውቶብስ ትራንስፖርት ታሪፍ ላይ በአማካይ 56 በመቶ ጭማሪ ተደረገ። በሚኒባስ ታክሲ የህዝብ ትራንስፖርት ታሪፍ ላይም፤ ከ50 ሳንቲም እስከ ሁለት ብር ድረስ ጭማሪ መደረጉ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ዛሬ አርብ ጥር 12፤ 2015 ይፋ ባደረገው ማሻሻያ መሰረት፤ አንድ ብር ከ50 ሳንቲም የነበረው ዝቅተኛ የከተማ አውቶብስ ታሪፍ ወደ ሶስት ብር ከፍ ብሏል። ሃያ ብር የነበረው ከፍተኛ የከተማ አውቶብስ ታሪፍ ደግሞ የአምስት ብር ጭማሪ ተደርጎበት 25 ብር ገብቷል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የከተማ አውቶብስ ታሪፍ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈለገው ታሪፉ ከተሻሻለ “ረጅም ጊዜ” ስላስቆጠረ እና “አስተዳደራዊ እና operational ወጪዎች በመጨመራቸው” ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል። የጥገና እና መለዋወጫ ወጪዎች “በጣም በሰፊ ሁኔታ እየጨመሩ” መምጣታቸውን ያነሱት አቶ ምትኩ፤ የከተማ አስተዳደሩ በሚያደርገው ድጎማ ብቻ የከተማ አውቶብሶች የሚሰጡትን አገልግሎት ማዘመን እንደማይቻል አውስተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አውቶብስ ታሪፍ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ ማሻሻያ የተደረገው በህዳር 2011 ዓ.ም ነው። በዛሬው ማሻሻያ መሰረት በአጫጭር ጉዞዎች ላይ 83 በመቶ እንዲሁም በረጅም ጉዞዎች ላይ ደግሞ 43 በመቶ ጭማሪ ተደርጓል።
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ማሻሻያ ያደረገበት ሌላኛው የትራንስፖርት አማራጭ፤ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ነው። በጭማሪው መሰረት አራት ብር የነበረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ታሪፍ ሰባት ብር ሆኗል።
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ለሁሉም ጉዞዎች ተመሳሳይ ታሪፍ እንደሚያስከፍል የጠቆሙት አቶ ምትኩ፤ የታሪፍ ማሻሻያ ቢደረግለትም ቀላል ባቡር የሚሠራው “በዜሮ ፐርሰንት የትርፍ ህዳግ” መሆኑን ተናግረዋል። በአዲሱ ታሪፍ ጭምር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቀላል ባቡር አገልግሎት የ73 በመቶ ድጎማ እንደሚያደርግም አክለዋል።
ከአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ጋር በተያያዘ በሁሉት ዋና ዋና ምክንያቶች በከተማይቱ ካሉት 41 ባቡሮች መካከል አገልግሎት እየሰጡ ያሉት 42 በመቶ ያህሉ መሆናቸውን አቶ ምትኩ በዛሬው መግለጫቸው ተናግረዋል። ለዚህም ምክንያቶቹ የኃይል መቆራረጥ እና “ከመለዋወጫ እና ጥገና አቅም ጋር የተያያዙ ችግሮች” መሆናቸውን አስረድተዋል።
ከሰባት ዓመት በፊት በ2008 ዓ.ም አገልግሎት መስጠት የጀመረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር፤ በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው በሁለት መስመሮች ነው። በትራንስፖርት ቢሮው መረጃ መሰረት፤ በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጡ ባሉት 18 ባቡሮች በቀን በአማካኝ 56 ሺህ ገደማ ተሳፋሪዎች ያጓጓዛሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)