የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኤርትራ ወታደሮች ከሰሜን ኢትዮጵያ እየወጡ መሆኑን ገለጹ 

የኤርትራ ወታደሮች ከሰሜን ኢትዮጵያ እየወጡ መሆኑ፤ በአካባቢው “ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ቁልፍ ጉዳይ” መሆኑን የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ተናገሩ። ይህን የሚከታተሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተቆጣጣሪዎች ወደ አካባቢዎቹ መድረስ የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻችም አሳስበዋል።   

ብሊንከን ይህን ያሉት የግጭት ማቆም ስምምነቱ አፈጻጸም በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ትላንት ቅዳሜ ጥር 13፤ 2015 በስልክ በተነጋገሩበት ወቅት መሆኑን የመስሪያ ቤታቸው ቃል አቃባይ ኔድ ፕራይስ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል የግጭት ማቆም ስምምነት ባለፈው ጥቅምት 23 ከተፈረመ ወዲህ፤ በአፈጻጸሙ ረገድ እስካሁን ድረስ “ጉልህ የሆነ መሻሻል” መታየቱን ብሊንከን በዚሁ የስልክ ውይይት ወቅት መናገራቸውን ቃል አቃባዩ ጠቅሰዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት ያለመውን እና በአፍሪካ ህብረት የሚመራውን ሂደት ለመደገፍ ያላትን ቁርጠኝነት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መግለጻቸውንም አክለዋል። ብሊንከን የኤርትራ ወታደሮች ሰሜን ኢትዮጵያን ለቅቀው እየወጡ መሆኑን በበጎነት ተቀብለውታል ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን፤ ባለፈው ታህሳስ ወር መጀመሪያ በዋሽንግተን ዲሲ በተደረገው የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በተገናኙበት ወቅት “የኤርትራ ወታደሮች በአፋጣኝ ከኢትዮጵያ የመውጣት አስፈላጊነት” ተነስቶ ነበር። ከዚሁ ጎን ለጎን የትግራይ ተዋጊዎች ትጥቅ የመፍታት ጉዳይም የወቅቱ አንድ የመወያያ ጉዳይ እንደነበር ከውይይቱ በኋላ በወጣው መግለጫ ላይ ሰፍሯል። በትላንቱ ውይይት ይህ ጉዳይ ስለመነሳቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያለው ነገር የለም።

በትላንቱ መግለጫ የተነሳው ሌላ ጉዳይ በኦሮሚያ ክልል ያለው ግጭት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና ብሊከን፤ በኦሮሚያ ክልል ያለውን አለመረጋጋት የማቆም አስፈላጊነት ላይ መወያየታቸውን ኔድ ፕራይስ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)