የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሀገሪቱ “ጤናማ የፋይናንስ ስርዓት የመገንባት” እና “የተረጋጋ የዋጋና የውጭ ምንዛሪ ተመን የማስፈን” ኃላፊነት በአዋጅ የተጣለበት መንግስታዊ ተቋም ነው። የብሔራዊ ባንክ ገዢ ሆኖ የሚሾም ግለሰብ፤ የዚህን ተቋም አስተዳደር እና ስራ የመምራትና የመቆጣጠር ስልጣን አለው። የባንኩ ገዢ ሀገሪቱ በምታሳትማቸው የገንዘብ ኖቶች እና የዋስትና ሰነዶች እንዲሁም ሌሎች ሰነዶች ላይ “ብቻውን ወይም ከሹማምንት ጋር በአንድነት” የመፈረም ኃላፊነትም ተሰጥቶታል።
በዚህ ኃላፊነት ላይ የሚቀመጥ ግለሰብ ስልጣንን በተመለከተ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ፤ “የብሔራዊ ባንክ ገዢው ማለት ኪሳችን ውስጥ ያለውን ብር ገንዘብ ያደረገው ሰውዬ ማለት ነው” ሲሉ ይገልጹታል። “ሰዎች ኪሳቸው ውስጥ ባለው ወይም በወር በሚያገኙት ገንዘብ ቤተሰባቸውን ያስተዳድራሉ ወይም አያስተዳድሩም? እጥረት ይገጥማቸዋል ወይም አይገጥማቸውም? የሚለውን የሚወስነው ገዢው ነው። ገንዘባቸውን ባንክ ቢያስቀምጡት ይሄንን ያህል ወለድ ያገኛሉ የሚለውን የሚወስነውም ገዢው ነው” በማለት ያብራራሉ።
በዚህ እና ሌሎች ምክንያቶች፤ በአንድ ሀገር ውስጥ ወሳኝ ከሚባሉ ስልጣኖች አንዱ የማዕከላዊ ባንክን የመምራት ኃላፊነት መሆኑ ይጠቀሳል። ኢትዮጵያ ከአራት ዓመት ከመንፈቅ ቆይታ በኋላ አዲስ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ማግኘቷ “ምን አንደምታ አለው” ሲል የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” አማኑኤል ይልቃል ባለሙያዎችን በማነጋገር ተከታዩን ዳሰሳ አጠናቅሯል።
ከትላንት በስቲያ አርብ ከስልጣናቸው የተነሱት የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ፤ ከአንድ ወር በፊት ለፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርት ለማቅረብ በፓርላማ ተገኝተው ነበር። ሁለት ሰዓት ተኩል ገደማ በፈጀው በዚህ ስብሰባ ወቅት፤ ዶ/ር ይናገር በሌሎች የመንግስት ኃላፊዎች ከተለመዱ አካሄዶች “ወጣ ያለ አካሄድ” መከተላቸው እና ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች “ቀጥተኛ እና ሀቀኛ” ምላሾች ሲሰጡ መስተዋላቸው ትኩረት ስቦ ነበር።
ዶ/ር ይናገር የብሔራዊ ባንክን የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድ እና የሩብ ዓመት አፈጻጸም ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት፤ በሌሎች ስብሰባዎች እንደተለመደው በ“ፓወር ፖይንት” ታግዘው ሳይሆን የማስታወሻ ደብተራቸውን እያጣቀሱ ነበር። ሌሎች የመንግስት ተቋማት ኃላፊዎች እንደሚያደርጉት፤ አብረዋቸው በስብሰባው ላይ የተገኙ ባልደረቦቻቸው በቀጥታ የሚመለከታቸው ጉዳይ ሲኖር ማብራሪያ እንዲያቀርቡ ዕድል ሲሰጡም አልታዩም።
የብሔራዊ ባንክ ገዢው በሪፖርታቸውም ሆነ በማብራሪያቸው፤ “በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ጫና እያሳደሩ” ስላሉ ጉዳዮች አጽንኦት ሰጥተው ሲናገሩ ተደምጠዋል። ኢትዮጵያ እየከፈለች የምትገኘው የውጭ ዕዳ ስለመጨመሩ፣ የሀገሪቱ የንግድ ሚዛን (trade balance) በከፍተኛ ሁኔታ እየሰፋ ስለመምጣቱ፣ ከዚህ ቀደም በወጪ ንግድ ጥሩ አፈጻጸም ይታይባቸው የነበሩት እንደ ወርቅ አይነት ምርቶች በ“ከፍተኛ መጠን” ስለ መቀነሳቸው ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግስት የዋጋ ግሽበትን ወደ ነጠላ አሃዝ የማውረድ ዕቅድ ቢይዝም፤ እስከሚቀጥለው ሰኔ ድረስ ባለው ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ግን “ይህን ማድረግ ይቻላል” የሚል እምነት እንደሌላቸውም በወቅቱ አስታውቀዋል።
ይህ በመንግስት ኃላፊዎች ዘንድ እምብዛም ያልተለመደው ዕቅድ እና ነባራዊ ሁኔታን በሀቀኝነት የማነጻጸር አካሄድ፤ በዶ/ር ይናገር ሌላ ገለጻ ወቅትም በጉልህ ተስተውሎ ነበር። የብሔራዊ ባንክ ገዢው “በሀገር ውስጥ እና በውጭ በተፈጠሩት አንዳንድ ሁኔታዎች፤ በእኛም በኩል፣ በገንዘብ ሚኒስቴር እና በእኛ፣ ጥብቅ የሆነ የfisical እና የmonetary ፖሊሲ መከተል አዳጋች ሆኖብናል። የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ያንን ማድረግ የሚያስችል ሆኖ አላገኘነውም። ስለዚህ ወደፊት ምን ማድረግ እንዳለብን ትኩረት ሰጥተን እየተነጋገርን ነው ያለነው” ሲሉ በወቅቱ ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ ተናግረዋል።
የተሰናባቹ ገዢ ፈተናዎች
ዶ/ር ይናገር ይህን ሪፖርት ለፓርላማ ባቀረቡ በአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀናት ጊዜ ውስጥ፤ ከብሔራዊ ባንክ ገዢነታቸው ተነስተው በምትካቸው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ማሞ ምህረቱ ተሹመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ይናገር በቦታው ላይ የቆዩት ለአራት ዓመት ከመንፈቅ ብቻ ነው። ከእርሳቸው አስቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ገዢ የነበሩት ተክለወልድ አጥናፉ በኃላፊነት ቦታው ላይ የቆዩት ለ13 ዓመታት ነበር።
ተሰናባቹ የብሔራዊ ባንክ ገዢ፤ ኃላፊነቱን ከተረከቡበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተለያዩ ጫናዎች ውስጥ አልፏል። ሪፎርም፣ ኮቪድ-19፣ ከፍተኛ የዋጋ ንረት እና ጦርነት ከጫናዎቹ መካከል በጉልህ የሚጠቀሱ ናቸው። ከውጭ ምንዛሬ፣ ከፋይናንስ ተቋማት እና ከገንዘብ አቅርቦት ጋር የተያያዙ ውሳኔዎች የማስተላለፍ ስልጣን የተሰጠውን ብሔራዊ ባንክን ሲመሩ የቆዩት ዶ/ር ይናገር፣ በባንኩ ገዢነታቸው ወቅት የብር የመግዛት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ተዳክሟል። እርሳቸው ወደ ብሔራዊ ባንክ ሲመጡ በይፋዊ የውጭ ምንዛሬ ተመን 27 ብር ገደማ የነበረው የአንድ ዶላር ዋጋ፤ አሁን 53 ብር ገደማ ሆኗል።
የማዕከላዊው ባንክ ገዢ ከመሆናቸው አስቀድሞ በብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነርነት ያገለገሉት ዶ/ር ይናገር፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ትምህርት የያዙት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው። ኔዘርላንድ ከሚገኘው ዓለም አቀፍ የማህበራዊ ጥናት ተቋም (International Institute of Social Studies) በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁት ዶ/ር ይናገር፤ ኦስትሪያ ቬይና ውስጥ ከሚገኘው University of National Resources and Life Sciences የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
እነዚህን የትምህርት ዝግጅቶች ይዘው የብሔራዊ ባንክ ገዢነት ስልጣንን የተረከቡት ዶ/ር ይናገር፤ እንደ ገንዘብ ኖት መቀየር ያሉ አበይት ክስተቶችን ያስተናገደ የስልጣን ዘመን አሳልፈዋል። የፋይናንስ ዘርፉም በእርሳቸው የስልጣን ዘመን በተላለፉ አነጋጋሪ ውሳኔዎች ጉልህ ለውጦችን አስተናግዷል። ከእነዚህ ውሳኔዎች ውስጥ ተጠቃሽ የሚሆነው፤ ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸውን በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ አምስት ቢሊዮን ብር እንዲያሳድጉ መታዘዛቸው ነው።
የዶ/ር ይናገር የብሔራዊ ባንክ ገዢነትን ዘመን ከፈተኑ ጉዳዮች መካከል፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ “በከፍተኛ የዋጋ ንረት ጫና” ውስጥ መውደቁ በዋነኛነት የሚጠቀስ እንደሆነ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት መረጃ እንደሚያሳየው፤ ዶ/ር ይናገር ወደ ስልጣን በመጡበት 2010 ዓ.ም የነበረው አማካይ አመታዊ የዋጋ ግሽበት 14.4 በመቶ ነበር። ይህ የዋጋ ግሽበት ባለፈው ታህሳስ ወር 33.8 በመቶ ደርሷል።
“በአንድ ኢኮኖሚ ውስጥ የዋጋ ግሽበት ግፊቶችን (inflationary pressure) ለመግታት ዋነኛው ተቋም የሚባለው ብሔራዊ ባንክ ነው” የሚሉት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው፤ ባንኩ “ገንዘብ የመፍጠር እና የመሰብሰብ” አቅም ያለው ተቋም በመሆኑ ያንን ተጠቅሞ የዋጋ ንረቱን ማቆም ይችል እንደነበር ይከራከራሉ። በዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ የሚሰሩ የኢኮኖሚ ባለሙያ በበኩላቸው፤ ብሔራዊ ባንኩ ያወጣቸው የነበሩ መመሪያዎች “የማይገመቱ እና በደንብ ጥናት ያልተደረገባቸው” በመሆናቸው የዋጋ ንረቱን መግታት አልቻሉም ይላሉ።
በዶ/ር ይናገር የገዢነት ጊዜ በብሔራዊ ባንክ ውስጥ በአማካሪነት ሲሰሩ የነበሩ የኢኮኖሚ ባለሙያ ግን የተለየ አስተያየት አላቸው። እኚህ የኢኮኖሚ ባለሙያ፤ ብሔራዊ ባንኩም ሆነ ገዢው ነጻነት ኖሯቸው፤ በራሳቸው ውሳኔዎችን የሚያስተላልፉ አልነበሩም ባይ ናቸው። አብዛኞቹ ውሳኔዎች በብሔራዊ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው አማካኝነት የተላለፉ መሆናቸውን የኢኮኖሚ ባለሙያው በማሳያነት ይጠቅሳሉ። “በእኛ አገር ሁኔታ ብሔራዊ ባንኩ ነጻ አይደለም። እንደሌላው ተቋም ሁሉ ማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው በሚያወጣው እቅድ ላይ ተመስርቶ ነው የሚሰራው” ሲሉም በተቋሙ በነበሩበት ወቅት ያስተዋሉትን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ዶ/ር ይናገር ወደ ስልጣን የመጡት፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት የኢኮኖሚ ሪፎርም እያደረገ በነበረበት ጊዜ መሆኑ ከግምት ውስጥ መግባት ያለበት ጉዳይ መሆኑንም የቀድሞው አማካሪ ይገልጻሉ። “ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተብሎ የተቀረጸ ፕሮግራም ነበር። የብሔራዊ ባንክ ገዢው እሱን ነው ሲተገብሩ የነበረው” ሲሉም ይህንኑ ሀሳብ ያጠናክራሉ። ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን ጨምሮ ከሌሎች አበይት የኢኮኖሚ ውሳኔዎች ጀርባ እንዳለ በሚነገርለት በማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴ ውስጥ አባል ከሆኑት ውስጥ አንዱ አቶ ማሞ ምህረቱ ናቸው።
የአዲሱ ገዢ ሚና ምን ይሆናል?
የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት አምስት ዓመታት ባደረጋቸው የኢኮኖሚ ሪፎርሞች ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ የሚነገርላቸው አቶ ማሞ፤ በስራ ዘመናቸው መንግስት በቅርቡ የወሰናቸው እና በቀጣይ ይፋ ያደርጋቸዋል ተብሎ የሚጠበቁ ሌሎች ውሳኔዎችን ከማስፈጸም አንጻር ትልቅ ሚና እንደሚኖራቸው ይጠበቃል። ከእነዚህ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የብሔራዊ ባንክን የተቆጣጣሪነት አቅም ይገዳደራል ተብሎ የሚጠበቀው የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ መግባት ነው።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ዓመት መጨረሻ ነሐሴ 2014 የባንክ ዘርፍን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት የሚያደርግ ፖሊሲ ያጸደቀ ሲሆን፤ የባንክ ስራ አዋጁም ይሄንን ለማስፈጸም በሚያስችል መልኩ እየተሻሻለ ነው። በዚሁም መሰረት የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ መግባት እና ስራ መጀመር እንዲሁም የሀገር ውስጥ ባንኮች የመወዳደር አቅምን በማሳደግ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው፤ ይሄንን ዕቅድ የሚያስፈጽሙ ህጎች ከወጡ በኋላ ብሔራዊ ባንኩ የአሰራር ስርዓቶችን የመዘርጋት እና የውጭ ባንክ ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት ኃላፊነት እንዳለበት ይገልጻሉ። ዕቅዱን ከማስፈጸም አንጻር የብሔራዊ ባንኩ የሚወስዳቸው እርምጃዎች “ጥንቃቄ የሚፈልጉ” መሆናቸውን ባለሙያው ያስረዳሉ። “ኢኮኖሚው በዘላቂነት ለውጪ ጫናዎች ተጋላጭ ሊሆን የሚችልባቸው ነገሮችን ሊፈጥር የሚችል እርምጃ ስለሆነ፤ በጣም ጥንቃቄ የሚፈልግ ነገር ነው” ሲሉ ስጋት የተቀላቀለበት አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
መንግስት በቅርቡ ይፋ ያደርጋዋል ተብሎ የሚጠበቀው ሁለተኛው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕቅድም፤ ሌላኛው የብሔራዊ ባንኩን ሚና የሚሻ ጉዳይ ሆኖ ይጠቀሳል። ለሶስት ዓመታት በሚተገበረው በዚህ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከተጠቀሱ ዋነኛ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ፤ በገበያ ፍላጎት እና አቅርቦት የሚመራ የውጭ ምንዛሬ ተመን እንዲኖር የማድረግ ዕቅድ ነው። መደበኛውን እና ትይዩውን የውጭ ምንዛሬ ገበያ አንድ የማድረግ ዕቅድን የያዘውን ይህን ማሻሻያ በማስፈጸም ረገድ፤ የብሔራዊ ባንኩ ድርሻ የላቀ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት “ የኢትዮጵያ ብር የመግዛት አቅም አሁንም መዳከም አለበት” የሚል አቋም እንዳላቸው የሚገልጹት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው፤ “ከውጭ ምንዛሬ አንጻር ያሉት እና እየተሄደባቸው ያሉ አቅጣጫዎች በጣም ሰከን ያለ የፖሊሲ ማኔጅመንት የሚፈልጉ ናቸው” ይላሉ። መንግስት ይሄንን ሀሳብ ተቀብሎ የብርን የመግዛት አቅም የማዳከም እቅድ ቢይዝ እንኳ፤ ከዋጋ ንረት እና ሌሎች ችግሮች አንጻር አፈጻጸሙ “ቀላል እንደማይሆን” ባለሙያው ያስረዳሉ።
የውጭ ምንዛሬን የመተመንም ሆነ የማስተዳደርም ኃላፊነት የብሔራዊ ባንኩ ስለሆነ ይሄንን በመምራት ረገድ “የብሔራዊ ባንክ ገዢው ብዙ ሚና አለው” ሲሉም ያክላሉ። በ2000 ዓ.ም በወጣው የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ “የተረጋጋ የዋጋና የውጭ ምንዛሪ ተመን የማስፈን” እና “ጤናማ የፋይናንስ ስርዓት የመገንባት” ኃላፊነት የተጣለበት እንደሆነ ያትታል። በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ለበርካታ ዓመታት የሰሩት አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዢ፤ በውጭ ምንዛሬ ተመን ረገድ “በተቋማቱ የሚቀርቡ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ሊተገብሩ” ይችላሉ የሚል ስጋት በበርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ዘንድ ሲንጸባረቅ ተስተውሏል።
ማሞ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸው በፊት ለስምንት ዓመታት ገደማ በዓለም ባንክ ከፍተኛ የፕሮግራም ስራ አስኪያጅ ሆነው ሰርተዋል። ተቀማጭነታቸውን በኬንያ ናይሮቢ ከተማ አድርገው የነበሩት አዲሱ ገዢ፤ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ከባቢ ላይ ትኩረት ያደረገን የዓለም ባንክ ፕሮግራም ሲመሩ ነበር። በዚህ ፕሮግራም አማካኝነት ባንኩ ከንግድ ህጎች፣ ሎጂስቲክስ፣ ታክስ እና የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ያደርጋቸው የነበሩ “ግንኙነቶች እና ድጋፎችን” በኃላፊነት አስተዳድረዋል። እርሳቸው የሚመሩት ፕሮግራም ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች ውስጥ፤ ንግድን አስመልክቶ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ ያላቸው ግንኙነት ይገኝበታል።
የትምህርት እና ልምድ ጉዳይ
በአዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ተሿሚ ላይ የሚነሳው ሌላው ጥያቄ፤ አቶ ማሞ ከሚመሩት ዘርፍ ጋር የተያያዘ የትምህርት ዝግጅት እና “የቀደመ ልምድ” የሌላቸው መሆኑ ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የኢኮኖሚ ባለሙያዎች፤ አቶ ማሞ በፋይናንስ ዘርፉ “የመስራት ልምድ የሌላቸው” መሆኑን በስጋት ያነሳሉ። ለዚህም በማነጻጸሪያነት የሚያቀርቡት፤ ከዚህ ቀደም የብሔራዊ ባንክ ገዢ የነበሩ ግለሰቦች የተሻለ የትምህርት ዝግጅት እና የስራ ልምድ ነበራቸው የሚል ነው።
ማሞ ምህረቱ፤ በ1992 ዓ.ም በህግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ነው። በደቡብ አፍሪካ ከሚገኘው ፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ በንግድ እና ኢንቨስትመንት የህግ ሁለተኛ ዲግሪ የያዙት ማሞ፤ ከአምስተርዳም ዩኒቨርስቲ ደግሞ በዓለም አቀፍ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ዲፕሎማ አላቸው፡፡ ማሞ በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በህዝብ አስተዳደር እና አመራር ከአሜሪካው ሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ ሌላ ሁለተኛ ዲግሪም ተቀብለዋል።
ከሰኔ 1997 ጀምሮ ለሶስት ዓመታት ገደማ፤ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን በአባልነት ለመቀላቀል ስታደርግ በነበረቻቸው ድርድሮች ላይ የንግድ ሚኒስቴርን ሲያማክሩ ቆይተዋል። ማሞ በሌሎች የሁለትዮሽ የንግድ ስምምነቶች እና የንግድ ፖሊሲ ጉዳዮች የንግድ ሚኒስቴርን በተጨማሪነት ያማክሩ እንደነበርም መረጃዎች ያመለክታሉ።
አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዢ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ መንግስት ውስጥ የመጀመሪያውን ስልጣን ያገኙት በነሐሴ 2010 ዓ.ም ነው። በጊዜው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የፖሊሲ ሪፎርም አማካሪ እና የዓለም ንግድ ድርጅትና የአካባቢያዊ ውህደት ድርድሮች ዋና ተደራዳሪ ሆነው ከተሾሙ በኋላ በኃላፊነቱ ላይ ለሶስት ዓመት ከመንፈቅ ቆይተዋል። በዋና ተደራዳሪነት ኃላፊነታቸው ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅትን በአባልነት ለመቀላቀል የምታደርገውን ድርድር ከስምንት ዓመት መቋረጥ በኋላ በጥር 2012 ዓ.ም አስጀምረዋል።
ማሞ ምህረቱ የብሔራዊ ባንክ ገዢ እንዲሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እስከተሾሙበት ቀን ድረስ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ 27 የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በስሩ የያዘውን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በዋና ስራ አስፈጻሚነት በመምራት ላይ ነበሩ። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣ ደንብ በ100 ቢሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ነበር።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ሀብት ከማስተዳደር ባሻገር “አትራፊ ናቸው ብሎ በሚያምንባቸው ማንኛቸውም የንግድና ኢንቨስትመንት ስራዎች” ላይ መዋለ ንዋይ የማፍሰስ ስልጣን ያለው ተቋም ነው። ይህ መንግስታዊ ተቋም ብቻውን ወይም ከአገር ውስጥ እና ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በመሆን የተቋቋሙ ድርጅቶችን አክስዮን መግዛት እንደሚችልም በማቋቋሚያ ደንቡ ላይ ሰፍሯል።
ማሞ ተቋሙን በመመስረት ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ አብረዋቸው የሰሩ ባልደረቦቻቸው ይናገራሉ። “ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመሆን ሀሳቡን ከማመንጨት ጀምሮ፣ ነገሩን አብስሎ ተግባራዊ በማድረግ እና ፕሮፌሽናሎችን አሰባስቦ በማሰራት” ረገድ አቶ ማሞ ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸው ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የተቋሙ ሰራተኛ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሌላ ባልደረባ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ይህ ተቋም ሲቋቋም፤ ማሞ የምስረታ ሂደቱ “የተለሳለሰ” እንዲሆን አድርገዋል ይላሉ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተቋቋመው በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እና የኢንቨስትመንት ፍሰቱ በተቀዛዘበት ሁኔታ ውስጥ መሆኑን የሚጠቅሱት ባልደረባው፤ “እንደዚያም ሆኖ ግን በአንድ ዓመት ውስጥ ሁለት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ማስገኘት ችለናል” ብለዋል። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንደኛው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚህ ሳምንት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በተገኙበት ወቅት ስምምነት የተፈጸመበት የጸሀይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ልማት ነው።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና የአቡዳቢው “ማስዳር” የተሰኘ ታዳሽ ኃይል ላይ የሚሰራ ተቋም በጋራ የሚያለሟቸው ሁለት የጸሀይ ኃይል ማመንጪያ ጣቢያዎች፤ 500 ሜጋ ዋት ማመንጨት እንደሚያስችሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በቲውተር ገጹ ላይ ባሰፈረው መረጃ፤ ይህ የማመንጨት አቅም በሂደት ሁለት ጊጋ ዋት ሊደርስ እንደሚችል ገልጿል።
መንግስታዊው ተቋም በሁለተኝነት አሳክቶታል ተብሎ የተጠቀሰው የግዮን ሪዲቨሎፕመንት ፕሮጀክት (Ghion redevelopment project) ነው። ይህ ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በስሩ ከያዛቸው ሶስት ሆቴሎች ውስጥ አንዱ የሆነው የግዮን ሆቴልን በዘመናዊ ሁኔታ መልሶ ለመገንባት ያቀደ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከሁለት ወራት በፊት ህዳር 2015 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት “በመንግስት እና በግል ትብብር” በሚካሄድ ፕሮጀክት ግዮንን ባለ ስድስት ኮከብ ሆቴል አድርጎ ለመገንባት መታቀዱን ተናግረው ነበር። ፕሮጀክቱ ግዮን ሆቴል ቪላዎች እና የገበያ ሞል እንዲኖረው የሚያደርግ መሆኑንም ጠቅሰው ነበር።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልንዲንግስ ከእነዚህ በተጨማሪ ከውጭ ባለሀብቶች እና ኩባንያዎች ጋር በመሆን ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር “በርካታ” ድርድሮችን እያደረገ መሆኑን የተቋሙ ሰራተኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። አቶ ማሞ ይመሩት በነበረው ተቋም በአጭር ጊዜ ውጤታማ ስራዎችን መስራታቸውን ባልደረቦቻቸው ቢመሰክሩላቸውም፤ በአዲሱ መስሪያ ቤታቸው ተመሳሳዩን ማሳካታቸው ላይ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ጥርጣሬ አላቸው።
መጪው ጊዜ ለአዲሱ የባንክ ገዢ እንዴት ያለ ነው?
ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ሀሳባቸውን ያጋሩት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ፤ አቶ ማሞ የተሾሙት ኢትዮጵያ “አንገብጋቢ ችግሮችን” በምትጋፈጥበት ወቅት መሆኑን በአጽንኦት ያነሳሉ። “እንደ ሀገር እጅግ በጣም ብዙ ስራዎች ነው የሚጠበቁብን። በጥንቃቄ ነገሮችን ማስተዳደር ያለብን ሰዓት ነው። ብዙ ተወዳዳሪ ፍላጎቶች ናቸው ያሉት። ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማቱ የራሳቸውን ፍላጎት መጫን ይፈልጋሉ። [እነዚህን ጉዳዮች] በጥንቃቄ መምራት የሚችል ሰው መጥቷል ብዬ አላስብም” ሲሉ የግል አስተያየታቸውን ያጋራሉ።
ከዚህ ቀደም በብሔራዊ ባንክ ውስጥ የሰሩት የኢኮኖሚ ባለሙያ በበኩላቸው፤ ውሳኔዎች የሚተላለፉት በማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው መሆኑን በማውሳት በዘርፉ ላይ እምብዛም ለውጥ ይመጣል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል። ውሳኔዎችን በቅጡ ለመተግበርም ቢሆን ግን ሁነኛ ሰው እንደሚያስፈልግ ይቀበላሉ። “የግለሰቦች መለዋወጥ ለውጥ የሚያመጣው፤ በእቅድ የወጣው ስራ ማስፈጸም ሂደት ላይ የሚኖረው ኃላፊነት እና ሚናን በተመለከተ ነው። የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው ብሔራዊ ባንክ ይሄንን ይተግብር ሲል ለማስፈጸምም ብቃት ይጠይቃል” ሲሉ የመከራከሪያ ሃሳባቸውን ያብራራሉ።
የኢኮኖሚ ባለሙያዎቹ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ውሳኔዎች በሀገሪቱ የማክሮ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚኖራቸውን ሚና እውቅና የሚሰጡ ቢሆንም፤ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲውን የመምራት እና የማክሮ ኢኮኖሚውን ችግሮች ለመፍታት ያለውን ሚና መጫወት የሚችለው “ነጻነት ሲኖረው” መሆኑን በአጽንኦት ይናገራሉ። በ2000 ዓ.ም. የወጣው የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅ፤ ተቋሙ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑን ደንግጓል።
ይሄንን አሰራር የሚቃወሙት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ፤ የባንኩ ተጠሪነት የበጀት ፖሊሲውን ለሚመሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆኑን በመጥቀስ “በእኛ ሀገር የገንዘብ ፖሊሲው፤ ለበጀት ፖሊሲ ባርያ ነው” ሲሉ ይተቻሉ። ብሔራዊ ባንኩ በራሱ ውሳኔ ገንዘብ ማተም፣ የገንዘብን ስርጭትን የመቆጣጠር፣ የፋይናንስ ስርዓቱን የማስተዳደር እንዲሁም የፋይናንስ ስርዓቱ ውስጥ ያሉ የፖሊሲ መሳሪያዎች ተጠቅሞ ኢኮኖሚውን ማንቀሳቀስ አማራጭ ሊኖረው እንደሚገባም ያመለክታሉ።
“የብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጁ በራሱ ማሻሻያ ተደርጎበት የባንኩን ገዢ ነጻ ሊያወጣው ይገባል። ያለበለዚያ የሾመው አካል ‘ይሄንን ያህል ገንዘብ እፈልጋለሁ ገንዘብ አትምልኝ’ ሲለው ‘እሺ አትምልሃለሁ’ የሚል ሰውዬ ነው የሚመጣው” ሲሉም የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ይሟገታሉ። ይሄንን ሀሳብ የሚጋሩት እና በዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ የሚሰሩ የኢኮኖሚ ባለሞያ በበኩላቸው፤ “ባንኩ በድጋሚ ተዋቅሮ የማክሮ ኢኮኖሚ ተቋም መሆን አለበት። አሁን የ[ገንዘብ] ማተሚያ ተቋም ነው” ሲሉ መከራከሪያውን ያጠናክራሉ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)