የአዲሶቹ ሚኒስትሮች ሹመት ነገ በፓርላማ ሊጸድቅ ነው

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙ ሶስት ሚኒስትሮች፤ ሹመታቸው በነገው ዕለት በፓርላማ ሊጸድቅ ነው። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ ከሰዓት በኋላ በሚያደርገው መደበኛ ስብሰባ ከተያዙ አጀንዳዎች መካከል፤ ቀዳሚው የሚኒስትሮችን ሹመት ማጽደቅ መሆኑን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው ሶስት የፓርላማ አባላት አረጋግጠዋል።

በነገው የፓርላማ ስብሰባ ሹመታቸው ይጸድቅላቸዋል ተብለው የሚጠበቁት አዳዲስ ተሿሚ ሚኒስትሮች፤ ዶ/ር አለሙ ስሜ፣ አቶ ሀብታሙ ተገኝ እና ዶ/ር ግርማ አመንቴ ናቸው። የብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማህበራት ዘርፍን ሲመሩ የቆዩት ዶ/ር አለሙ፤ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርን እንዲመሩ የተሾሙት ባለፈው አርብ ጥር 12፤ 2015 ነበር። 

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ሀብታሙ ተገኝ በተመሳሳይ ቀን የማዕድን ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። በህገ መንግስቱ መሰረት ነገ የተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸውን እንዲያጸድቅላቸው ከሚጠበቁት ተሿሚዎች ውስጥ ሶስተኛው፤ የግብርና ሚኒስትርነትን ቦታ ያገኙት ዶ/ር ግርማ አመንቴ ናቸው። 

ዶ/ር ግርማ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከተሾሙበት ዕለት ድረስ በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመንግስት የልማት ተቋማት ክላስተር አስተባባሪ ሆነው በመስራት ላይ ነበሩ። አዲሱ የግብርና ሚኒስትር ወደ ኦሮሚያ ክልል ከመሄዳቸው በፊት ለአንድ ዓመት ያህል የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)