የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ የምክክር ተሳታፊዎችን የመለየት ስራ ከሶስት ሳምንት በኋላ ሊጀምር ነው 

በሃሚድ አወል

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሶስት ሳምንት በኋላ የምክክር ተሳታፊዎች የመለየት ስራን በወረዳ ደረጃ እንደሚጀምር አስታወቀ። ኮሚሽኑ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከባለድርሻ አካላት ጋር ሲያደርጋቸው የነበሩ የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይቶችን ማጠናቀቁንም ገልጿል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ይህን የገለጸው ዛሬ ሰኞ ጥር 15 በአዲስ አበባው ኃይሌ ግራንድ ሆቴል እያካሄደ ባለው “የመጨረሻው የባለድርሻ አካላት ውይይት” ላይ ነው። ኮሚሽኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ እና ነገ በሚያደርገው ውይይት ላይ፤ የአዲስ አበባ ከተማ የወረዳ እና የክፍለ ከተማ አመራሮች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የኃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ተሳተፈዋል። 

በዛሬው የውይይቱ መክፈቻ ላይ የተገኙት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ፤ “የታሳታፊዎች ልየታ አጠር ባለ ጊዜ በተለያዩ ወረዳዎች ይጀምራል” ሲሉ ተናግረዋል። ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል ውጭ ባሉ የሀገሪቱ ክልሎች እስካሁን ባደረጋቸው ውይይቶች፤ ለኮሚሽኑ የአሰራር ስርዓት (methodology) ግብዓቶች ማሰባሰቡን ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። 

ይህ አሰራር ስርዓት መጪው ሀገራዊ ምክክር የሚመራበት “ፍኖተ ካርታ” እንደሚሆን ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በምክክር ኮሚሽኑ ምክር ቤት መጽደቅ የሚጠበቅበት ይህ የአሰራር ስርዓት፤ የሀገራዊ ምክክሩን ተሳታፊዎች ብዛት፣ የውክልና አይነት እና የአጀንዳ አቀራረጽ ሂደት የሚወስን ነው። 

በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ መሰረት “የህዝብ ምክክር የሚደረግባቸውን አጀንዳዎች በዝርዝር በመፈተሽ፤ ምክክር እንዲደረግባቸው የመወሰን” ስልጣን የተሰጠው ለኮሚሽኑ ምክር ቤት ነው። አስራ አንዱን የምክክር ኮሚሽኑን ኮሚሽነሮች በአባልነት የያዘው ይህን ምክር ቤት የሚመሩት ዋና ኮሚሽነሩ ፕ/ር መስፍን አርዓያ ናቸው። 

የኮሚሽኑ ምክር ቤት የአሰራር ስርዓቱን ካጸደቀ በኋላ ወደ ተሳታፊዎች ልየታ እና አጀንዳ ማሰባሰብ እንደሚገባ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ማብራሪያ የሰጡት ኮሚሽነር ተናግረዋል። የተሳታፊዎች ልየታ የሚከናወነው በወረዳ እና ልዩ ወረዳዎች ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሆን ከ11 የምክክር ኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች አንዷ የሆኑት ብሌን ገብረመድህን በዛሬው ውይይት ለታደሙ ተሳታፊዎች ባደረጉት ገለጻ ላይ ጠቁመዋል። 

ብሌን በዚሁ ገለጻቸው፤ ኮሚሽኑ ከምክክር ተሳታፊዎች ልየታ ጋር በተያያዘ አራት የትኩረት ቦታዎች እንደሚኖሩት ይፋ አድርገዋል። ኮሚሽኑ ተሳታፊዎችን የሚለየው ከክልሎች፣ ከአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮች፣ ከፌደራል እና በውጭ ሀገር ከሚገኙ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን መሆኑንም አስታውቀዋል። በክልሎች ደረጃ በሚደረገው የተሳታፊዎች ልየታ፤ “እያንዳንዱ የህብረተሰብ ክፍል የሚወክለውን ተሳታፊ ይመርጣል” ሲሉ ኮሚሽነር ብሌን ተናግረዋል። 

በክልሎች በሚገኙ ወረዳዎች ደረጃ ይደረጋል የተባለው የተሳታፊዎች የመለየት ስራ፤ “በአጠረ ጊዜ” ከሶስት ሳምንት ገደማ በኋላ እንደሚጀመር ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገልጸዋል። ኮሚሽነሯ አክለውም “በአጭር ጊዜ ያልቃል ለማለት ግን እቸገራለሁ። ምክንያቱም ስራው ሰፊ ነው” ሲሉ የተሳታፊዎች የመለየት ስራ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ጠቁመዋል። 

“ነገሮችን አፍጥኖ ወደ ምክክሩ ጉባኤዎች ብንገባ ነው የምንመርጠው” ያሉት ሂሩት፤ “ተለዋዋጭ ነገሮች” እና “ከፍተኛ የሎጂስቲክስ ተግዳሮት” ጊዜውን ሊያስረዝመው እንደሚችል አመልክተዋል። ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አክለውም “የተሳታፊዎች ልየታ ከተጀመረ በኋላ በሶስት፣ አራት ወር እንጨርሳለን ብለን እንገምታለን” ሲሉ የኮሚሽኑን ዕቅድ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ ለምክክር ተሳታፊነት ብቁ የሚያደርጉ ያላቸውን መስፈርቶች መለየቱ በዛሬው ስብሰባ ላይ ተነስቷል። ከእነዚህ መስፈርቶች መካከል “ተሳታፊው የሚወከልበት የህብረተሰብ ክፍል አባል መሆን፣ የህብረተሰቡን ድምጽ እና ሃሳብ ማሰማት የሚችል እንዲሁም ስለሚወክለው የህብረተሰብ ክፍል አውድና የሚነሱ ጉዳዮች በቂ ግንዛቤ መያዝ” የሚሉት ይገኙበታል።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ “በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተሳታፊዎችን ግልጽ በሆኑ መስፈርቶች እና የአሰራር ስርዓት መሰረት የመለየት” ኃላፊነት እንዳለበት በማቋቋሚያ አዋጁ ተደንግጓል። ኮሚሽኑ የተሳታፊዎችን ልየታ እና የምክክር ተሳትፎ በተመለከተ ዝርዝር መመሪያ እንደሚያወጣም በዚሁ አዋጅ ላይ አስፍሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)