አዲሱ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፤ የፍርድ ቤቶች የአገልግሎት አሰጣጥ “በቂ እና አርኪ” አይደለም አሉ

አዲሱ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፤ ፍርድ ቤቶች ከተገልጋዮች ፍላጎት አንጻር የሚሰጡት ምላሽ “በቂ እና አርኪ የመሆኑ ጉዳይ ጥያቄ የሚነሳበት ነው” አሉ። በፍርድ ቤቶች ውስጥ ያለውን ችግር “ከግዝፈቱ እና ስፋቱ” አንጻር ተመልክቶ መፍትሄ ለመስጠት እና እርምጃ ለመውሰድ ይቻል ዘንድ፤ ህብረተሰቡ በትግስት እንዲጠብቃቸውም ጠይቀዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ይህን ያሉት፤ ከቀድሞዎቹ የፍርድ ቤቱ አመራሮች ጋር ዛሬ ሰኞ ጥር 15፤ 2015 የስራ ርክክብ ባደረጉበት ወቅት ባሰሙት ንግግር ነው። በፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በተካሄደው በዚሁ የርክክብ ስነ ስርዓት ላይ፤ ተሰናባቿ የፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፣ ምክትላቸው አቶ ሰለሞን አረዳ እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ተገኝተዋል። ስነ ስርዓቱን አዲሲቷ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ወ/ሮ አበባ እምቢአለም ታድመውታል። 

“የንቃተ ህግ መዳበር እና ለመብት ቀናኢ የመሆን ሁኔታ እየጨመረ” መምጣቱን በስነ ስርዓቱ ላይ የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፤ “በአንጻሩ ደግሞ የፍርድ ቤቶች ምላሽ በቂ እና አርኪ ስለመሆኑ የሚነሳው ጥያቄ በቀላሉ የምንመልሰው ሆኖ አይገኝም” ብለዋል። ፍርድ ቤቶች “የተጠራቀመ እና የተንከባለለ ችግር ሲሸከሙ የቆዩ ተቋማት” መሆናቸውንም አመልክተዋል።  

አዲሱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፤ “አዳዲስ አሰራሮችን እና ቴክኖሎጂዎችን ስራ ላይ በማዋል፤ የማህበረሰቡን ፍላጎት ለማርካት እንዲሁም ፍርድ ቤቱ በህዝብ እምነት የሚጣልበት ተቋም ለማድረግ” ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል። በፍርድ ቤቶች ውስጥ ያለውን ችግር ከ“ግዝፈቱ እና ስፋቱ” አንጻር ተመልክቶ መፍትሄ ለመስጠት የሚያስችሉ እቅዶችን ነድፈው ወደ ተግባር እንደሚገቡም ገልጸዋል። 

“ህብረተሰቡ የችግሩ ግዝፈት የሚጠይቀውን ጊዜ ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ ለሚሰጡት መፍትሄዎች፣ ለሚወሰዱት እርምጃዎች  በትግስት እንዲጠብቀን እንጠይቃለን” ሲሉም አቶ ቴዎድሮስ ጥሪ አቅርበዋል። “ልናመጣ የምንፈልገው ለውጥ ባለድርሻ አካላት የዳር ተመልካች ሆነው ሊሳካ [አይችልም]” ያሉት አዲሱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፤ የፍርድ ቤትን ነጻነት ለማረጋገጥ፣ ተጠያቂነትን ለማስፈን እና ግልጽ አሰራርን ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት “የሁሉም አዎንታዊ ድጋፍ” እንዳይለያቸው መልዕክት አስተላለፈዋል።

በዚህ ስነ ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት ወ/ሮ መአዛ፤ የመጀመሪያዋ ሴት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት በመሆናቸው ደስታ እንደሚሰማቸው ገልጸዋል። የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትነት ጊዜያቸውን “ውጤታማ እና አስቸጋሪ” ሲሉ የጠሩት ወ/ሮ መአዛ፤ በእርሳቸው የአስተዳደር ዘመን “የዳኝነት ነጻነት፣ ቅልጥፍና እና ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ አንጻር” ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል። 

በተሰናባቾቹ የጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራር ጊዜ የጸደቁ ህጎች ስኬት ማስገኘታቸውንም ጠቅሰዋል። ከፍርድ ቤት አመራሮች ባሻገር ሌሎች የፍትህ አካላት የተካተቱበት “አጠቃላይ የፍትህ ዘርፍ ማሻሻያ ፍኖተ ካርታ” ለማዘጋጀትም የዳሰሳ ጥናት እና “ሌሎች የቅደመ ስራዎች” እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።

ወ/ሮ መአዛ በዛሬው ንግግራቸው ከጠቀሷቸው የህግ ማሻሻያዎች ውስጥ የስነምግባር እና ዲሲፕሊን ደንብ ይገኝበታል። ይህን ደንብ  በመጠቀም “ለዳኝነት ተጠያቂነት መሰረት የሚጥሉ የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል” ብለዋል። “በዳኝነት አካሉ ውስጥ የሚስተዋሉትን የሙስና ተግባራትን ለመከላከል የሚያስችል የሙስና መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ በማጽደቅ ተግባራዊነቱን የሚከላከል ጽህፈት ቤት እና ኃላፊ እንዲመደብ ተደርጓል” ሲሉም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)