ለፓርላማ የቀረበው የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ማሻሻያ ምን ይዟል?

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ከሰዓት በሚያደርገው መደበኛ ስብሰባ፤ የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅን መርምሮ ጉዳዩ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለመምራት አጀንዳ ይዟል። ለፓርላማው የቀረበው ይህ የአዋጅ ረቂቅ፤ በመጋቢት 2012 ዓ.ም የወጣው እና አሁን በስራ ላይ ባለው አዋጅ የኤክሳይዝ ታክስ የተጣለባቸው ምርቶች እና የታክስ መጠን ላይ ለውጦችን ያደረገ ነው። በኤክሳይዝ ታክስ አዋጁ ላይ ለውጥ የተደረገባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች እንደሚከተለው ቀርበዋል:-

 • ከዚህ ቀደም ከኤክሳይዝ ታክስ ነጻ የነበሩት የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎቶች አሁን 5 በመቶ እንዲጣልባቸው ያደርጋል።
 • ቴሌቪዥን እና የቪድዮ ካሜራዎች ሙሉ ለሙሉ ከኤክሳይዝ ታክስ ነጻ እንዲሆኑ ማሻሻያው ላይ ቀርቧል። አሁን ባለው አሰራር ሁለቱ ምርቶች እያንዳንዳቸው 10 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይከፈልባቸዋል።
 • ከቀረጥ እና ታክስ ነጻ ሆነው እቃዎችን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ኢንቨስተሮች፣ አካል ጉዳቶኞች እና በጉምሩክ ታሪፍ ሁለተኛ መደብ የተዘረዘሩ ተቋማት የኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣልባቸው ያደርጋል።
 • 60 በመቶ የኤክሳይዝ ታክስ ተጥሎበት የነበረው የማይጠጣ ንጹህ አልኮል አሁን ወደ 10 በመቶ ዝቅ እንዲል በረቂቅ ህጉ ላይ ቀርቧል። በማይጠጣ ንጹህ አልኮል ላይ ተጥሎ የነበረው ታክስ፤ የኮቪድ ወረርሽኝ በተባባሰበት ወቅት ለ“ሳኒታይዘር” መስሪያ ግብዓት መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ሙሉ ለሙሉ ተነስቶ እንደነበር ይታወሳል።
 • ረቂቅ አዋጁ አሁን በስራ ላይ ካለው በተለየ፤ ተሽከርካሪዎችን በአራት የሚከፍልበት አዲስ አመዳደብ ይዟል። በአዲሱ ምድብ አብዛኛዎቹ አዲስ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው የኤክሳይዝ ታክስ ምጣኔ ቀንሷል።
 • በ2012 በወጣው አዋጅ ላይ ከ1300 ሲሲ በታች የሆኑ አዲስ ተሽከርካሪዎች በተለያዩ ምድቦች 5 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይጣልባቸዋል። አዲሱ የአዋጅ ረቂቅ በአንጻሩ “ከ1500 ሲሲ በታች” የሚካተቱ ተሽከርካሪዎችን አዲስ ምድብ ሰጥቷቸዋል። በዚህ ምድብ ስር ባሉ ተሽከርካሪዎች ላይ 10 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ የሚጥል ድንጋጌ በአዲሱ የአዋጅ ረቂቅ ላይ ሰፍሯል።
 • አሁን በስራ ላይ ባለው ምደባ ከ1500 ሲሲ በልጠው፣ ከ3000 ሲሲ ግን የማይበልጡ አዲስ ተሸከርካሪዎች፤ 60 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ተጥሎባቸዋል። የአዋጅ ረቂቁ “ከ1501 እስከ 2500 ሲሲ” የሚል አዲስ ምድብ ያካተተ ሲሆን፤ በዚህ ውስጥ የሚካተቱ ተሽከርካሪዎች ላይ 20 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ይጥላል።
 • በአዲሱ ምድብ ከ2501 እስከ 3000 ሲሲ የሆኑ ተሽከርካሪዎች፤ 30 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጣልባቸው በረቂቁ ላይ ቀርቧል። አሁን በስራ ላይ ያለው ምድብ ከ1800 ሲሲ በላይ የሆኑ አዲስ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጥለው የኤክሳይዝ ታክስ መቶ በመቶ (100%) ነው።
 • በስራ ላይ ያለው አዋጅ ከ3000 ሲሲ በላይ የሆኑት አዲስ ተሸከርካሪዎች መቶ በመቶ (100%) ኤክሳይዝ ታክስ እንዲጥልባቸው የሚያደርግ ሲሆን ረቂቅ አዋጁ ይህንን የታክስ ምጣኔ ወደ 60 በመቶ ቀንሶታል።
 • እንደ ከረሜላ ያሉ ስኳር የታከለባቸውን ምርቶች የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች፤ ለምርቶቻቸው የሚከፍሉት 20 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ ወደ 10 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጎ በአዋጅ ረቂቁ ላይ ቀርቧል።
 • የአዋጅ ረቂቁ እስካሁን ተግባራዊ ሳይደረግ የቆየው፤ ለምግብነት በተዘጋጀ ከ100 ግራም ውስጥ 40 ግራም ወይም የበለጠ “ሳቹሬትድ ስብ” የያዘ የአትክልት እና የእንስሳት ዘይት ላይ የተጣለው ታክስ “ለጊዜው” ቀሪ እንዲሆን አድርጓል። [በ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተጠናቀረ]