በአጭር ጊዜ የተካሄደው የሚኒስትሮች ሹም ሽር በፓርላማ አባላት ጥያቄ ተነሳበት

በሃሚድ አወል

በመንግስት ውስጥ “በየጊዜው የሚካሄደው” የሚስትሮች ሹመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄ ተነሳበት። የምክር ቤት አባላቱ ጥያቄውን ያነሱት ዛሬ ማክሰኞ ጥር 16፤ 2015 የሶስት ሚኒስትሮችን ሹመት ባጸደቁበት ወቅት ነው። በፓርላማው የመንግስት ተጠሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው መንግስት “አመራር የማሸጋሸግ ስልጣን አለው” ሲሉ መልሰዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ቀዳሚ የነበረው አጀንዳ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙ ሚኒስትሮችን ሹመት ማጽደቅ ነበር። ዛሬ ሹመታቸው የጸደቀላቸው ሶስቱ አዳዲስ ሚኒስትሮች ዶ/ር አለሙ ስሜ፣ አቶ ሀብታሙ ተገኝ እና ዶ/ር ግርማ አመንቴ ናቸው። ዶ/ር አለሙ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር፤ አቶ ሀብታሙ ተገኝ የማዕድን ሚኒስትር እንዲሁም ዶ/ር ግርማ አመንቴ በግብርና ሚኒስትርነት የተሾሙት ባለፈው ሳምንት አርብ ጥር 12፤ 2015 ነበር።

በፓርላማ የመንግስት ተጠሪው አቶ ተስፋዬ በልጅጌ የሶስቱን ተሿሚ ሚኒስትሮች የትምህርት ዝግጅት እና የስራ ልምድ በንባብ ካሰሙ በኋላ ስድስት የምክር ቤት አባላት ጥያቄ እና አስተያየታቸውን አቅርበዋል። ከስድስቱ የፓርላማ አባላት መካከል የሁለቱ ጥያቄ እና አስተያየት ለየት ያለ ነበር።

ሁለቱ አባላት ፓርላማው የሚኒስትሮችን ሹመት ያጸደቀው ባለፈው ዓመት መሆኑን አስታውሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚኒስትሮች ሹም ሽር ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት ላይ ማብራሪያ ጠይቀዋል። የተቃዋሚው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን ተወካይ የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ፤ “ለምንድን ነው በየዓመቱ እንደ ዘመን መለወጫ ሚኒስትር የምንቀያይረው?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።

አቶ ክርስቲያን “በየጊዜው” የሚካሄደው ሹም ሽር የተረጋጋ አመራር እና ስርዓት እንዲሁም የተቋም ግንባታ ላይ የራሱ ተጽዕኖ ይኖረዋል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል። አቶ ክርስቲያን አክለውም፤ “በየጊዜው የሚካሄደው የአመራር መቀያየር ማቆሚያው እንዴት ነው?” ሲሉ በአጽንኦት ጠይቀዋል።

ዛሬ ሹመታቸው የጸደቀላቸውን ሚኒስትሮች በተመለከተም አስተያየት የሰጡት አቶ ክርስቲያን ለግብርና ሚኒስትርነት የተሾሙት “ከዶ/ር ግርማ ጋር ተያይዞ reservation አለኝ። ስለዚህ ድምጽ አሰጣጡ በተናጠል እንዲሆን” ሲሉ የአሰራር ጥያቄ አቅርበዋል።

ወ/ሮ አሌ በላቸው የተባሉ ሌላ አንዲት የምክር ቤት አባልም  እንዲሁ ከአቶ ክርስቲያን ጋር ተመሳሳይ አስተያየት ሰንዝረዋል።  ፓርላማው ባለፈው አመት የአስፈጻሚ አካላትን ሹመት ማጽቁን ያስታወሱት ወ/ሮ አሌ “ዛሬ አዲስ ሹመት የምናጸድቀው ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል። ወ/ሮ አሌ አክለውም ዛሬ የጸደቀውን ሹመት “ሴቶችን ያካተት አይደለም” ሲሉ ተችተውታል።

የመንግስት ተጠሪው አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ለጥያቄዎቹ በሰጡት ምላሽ “መንግስት እንደ አስፈላጊነቱ ስራዎችን እየገመገመ አመራሩን የማሸጋሸግ፣ የማጠናከር [እና] በተለያዩ ቦታዎች ላይ አዟዙሮ የመመደብ ስልጣን አለው፤ የተለመደም ነው” ብለዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ አክለውም፤ “ሌላ ጊዜም እንዲህ አይነት የአመራር ምደባ ለዚህ ምክር ቤት ቀርቦ አይጸድቅም ብሎ ቃል መግባት አይቻልም” ሲሉ ለተነሱ አስተያየቶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

“አንድ ጊዜ አመራር ከተመደበ እና ስራ ከተጀመረ በኋላ አይነካም፤ አይታሰብም የሚባል አሰራር የለም” ያሉት የመንግስት ተጠሪው፤ አመራሮችን “በተለያዩ ምክንያቶች” የማሸጋሸግ እና አዟዙሮ ማሰራት “የተለመደ አሰራር” መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከተቋማት ግንባት ጋር ተያያዞ ለተነሳውም ጥያቄ የሚኒስትሮች ሹም ሽር “ተቋም ግንባታውን ያናጋል የሚል ዕምንት የለንም” ብለዋል፡፡

ከመንግስት ተጠሪው ምላሽ በኋላ የፓርላማው አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ከአሰራር ጋር በተያያዘ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በተናጠል ድምጽ የሚሰጥበት ስርዓት መኖሩን ያነሱት አፈ ጉባኤው፤ ዶ/ር ግርማን በተመለከተ “ከይዘት አኳያ ብዥታ የሚፈጥር የቀረበ ነገር የለም” በማለት ለብቻ ድምጽ እንደማይሰጥ ገልጸዋል፡፡

አፈ ጉባኤው ይህን ካሉ በኋላ በዛሬው ስብሰባ የተገኙ የምክር ቤት አባላት የሚኒትሮችን ሹመት በተመለከተ በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ድምጽ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡ በዛሬው ስብሰባ ላይ ከተገኙት 321 የምክር ቤት አባላት መካከል አቶ ክርስቲያንን ጨምሮ አስር አባላት የሚኒስትሮቹን ሹመት ተቃውመዋል፡፡ ሁለት የፓርላማ አባላት ድምጽ ከመስጠት ሲታቀቡ አብላጫዎቹ ደግሞ የድጋፍ እጃቸውን አንስተዋል፡፡

ከማዕድን ሚኒስትር ተሿሚው ሀብታሙ ተገኝ በስተቀር የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ ዶ/ር አለሙ ስሜ እና የግብርና ሚኒስትሩ ዶ/ር ግርማ አመንቴ በፓርላማ ተገኝተው ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጥር 9፤ 2015 የተሾሙት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት፤ አዲሶቹን ሚኒስትሮች ቃለ መሃላ አስፈጽመዋል፡፡ (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)