ላለፉት አራት ዓመታት በእስር ላይ የቆዩት አቶ በረከት ስምኦን “የአመክሮ ጊዜያቸውን ጨርሰው” ዛሬ ረቡዕ ጥር 17፤ 2015 ጠዋት ከባህር ዳር ማረሚያ ቤት መፈታታቸውን ጠበቃቸው ህይወት ሊላይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ከጥረት ኮርፖሬሽን የገንዝብ ብክነት ጋር በተያያዘ በቀረበባቸው ክስ የስድስት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው የነበሩት አቶ በረከት የተፈቱት የአመክሮ ጊዜያቸውን በማጠናቀቃቸው መሆኑን የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ውቤ ወንዴ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት “ተጽዕኖ ፈጣሪ እና ተደማጭ” ፖለቲከኛ የነበሩት አቶ በረከት በአዲስ አበባ ከሚገኘው የመኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት ከአራት ዓመታት በፊት ጥር 15፤ 2011 ነበር። የቀድሞው የብሔር አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ታደሰ ካሳም በተመሳሳይ ወንጀል ተጠርጥረው በዚያኑ ጊዜ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ሁለቱ ጉምቱ ሹማምንት የጥረት ኮርፖሬሽንን በኃላፊነት በመሩባቸው ዓመታት “ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ አባክነዋል” የሚል ክስ በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚያዝያ 2011 ዓ.ም ተመስርቶባቸዋል። ከቀድሞው የአማራ ክልል ገዢ ፓርቲ ብአዴን ጋር ግንኙነት የነበረው ጥረት ኮርፖሬሽን፤ ዳሸን ቢራ ፋብሪካ፣ አምባሰል የንግድ ሥራዎች የመሳሰሉ ተቋማትን እና በእርሻና የመጓጓዣው ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎችን የሚያስተዳድር ነው። የኮርፖሬሽኑ ተጠሪነት ከህዳር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለአማራ ክልል ምክር ቤት እንዲሆን ተደርጓል።
በባህር ዳር መቀመጫውን ያደረገው እና በሁለቱ የጥረት ኮርፖሬሽን የቀድሞ አመራሮች ላይ የቀረበውን ክስ ሲመለከት የቆየው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፤ አቶ በረከት ስምኦን በስድስት አመት እስራት እና በ10 ሺህ ብር እንዲቀጡ ሚያዝያ 30፤ 2012 ወስኗል። በሶስት የክስ መዝገቦች ጥፋተኛ የተባሉት አቶ ታደሰ ካሳ በአንጻሩ የስምንት አመታት እስር እና የ15 ሺህ ብር ቅጣት ተጥሎባቸዋል።
አቶ በረከት በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት ለሁለት አስርት ዓመታት ገደማ በተለያዩ የመንግስት ኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉ የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣን ነበሩ። በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የስልጣን ዘመን የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሚኒስትር የነበሩት አቶ በረከት፤ የዚህ መስሪያ ቤትን መፍረስ ተከትሎ የተቋቋመውን የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤትን በኃላፊነት መርተዋል።
በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መንግስት ውስጥ በሚኒስትር ማዕረግ የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል። ለአራት አመታትም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር አማካሪም ነበሩ። አቶ በረከት በአገሪቱ ፖለቲካ ሁነኛ ተሳታፊ በነበሩባቸው ዓመታት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በቦርድ ሊቀ መንበርነት የቀድሞውን የኢትዮጵያ ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት በቦርድ ሰብሳቢነት ይመሩ ነበር።
ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር የጠበቀ ግንኙነት የነበራቸው በረከት በ1997 የተካሔደውን ምርጫ ጨምሮ በተለያዩ ፖለቲካዊ ሙግቶች ኢህአዴግን እየወከሉ የሚከራከሩ ነበሩ። “የሁለት ምርጫዎች ወግ” እንዲሁም “ትንሳኤ ዘ-ኢትዮጵያ ከመንታ መንገድ” የሚል ርዕስ የተሰጣቸው ሁለት መጻህፍትንም ለንባብ አብቅተዋል።
በረከት ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፣ የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) እና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) ጋር በመሆን ኢህአዴግን የመሠረተው የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን) መስራች አባል ናቸው። ኢህዴን በስተኋላ ላይ ስያሜውን ወደ ብአዴን ቀይሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[የ”ኢትዮጵያ ኢንሳይደሩ” አማኑኤል ይልቃል ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል]