በሃሚድ አወል
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በውጭ ሀገር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ለመወያያት የውጭ ሀገር ጉዞዎችን እንደሚያደርግ አስታወቀ። ኮሚሽኑ “በጥቂት ቀናት” ውስጥ ከዳያስፖራዎች ጋር በበይነ መረብ አማካኝነት ስብሰባዎችን እንደሚያደርግም ገልጿል።
ከአንድ ዓመት በፊት በአዋጅ የተቋቋመው የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ የምክክር ተሳታፊዎችን ለመለየት ትኩረት ከሚያደርግባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል አንደኛው ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን አስታውቆ ነበር። ኮሚሽኑ በፌደራል፣ በክልሎች፣ በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮች ከሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የምክክሩን ተሳታፊዎች የመለየት ስራ እንደሚያከናውንም ገልጿል።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለማወያየት አምስት ቦታዎችን በ“ክላስተር” መለየቱን ከኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች አንዷ የሆኑት ብሌን ገብረመድህን ከትላንት በስቲያ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል። ኮሚሽኑ ውይይቶችን ለማከናወን የለያቸው አምስት “ክላስተሮች” አውሮፓ፣ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ እስያ እና ኦሺኒያ እንዲሁም አሜሪካ እና ካናዳ ናቸው።
በእነዚህ “ክላስተሮች” የሚገኙ አካባቢዎች ተለይተው የተመረጡት “በርካታ ኢትዮጵያውያን ያሉባቸው እና ስትራቴጂካሊ ብዙ ተሳታፊ እንዲመጣ ተደራሽ ስለሆኑ ነው” ሲሉ ኮሚሽነር ብሌን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። ኮሚሽኑ በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር በ“ዙም” ስብሰባ የሚያደርገው ግብዓቶችን ለማሰባሰብ እንደሆነም ገልጸዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከሚገኙ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሲያደርጋቸው የነበሩ የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይቶችን ትላንት ማክሰኞ አጠናቅቋል። ኮሚሽኑ ከትላንት በስቲያ ሰኞ ጀምሮ ለሁለት ቀናት ባካሄው የመጨረሻ የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ የወረዳ እና የክፍለ ከተማ አመራሮች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
ኮሚሽኑ በውጭ ሀገር ከሚገኙ አትዮጵያውን ጋር ከሚያደርገው የ“ዙም” ስብሰባ በኋላ፤ በ“ክላስተር” በተለዩት አምስት ቦታዎች ውይይቶችን በአካል ለማካሄድ ከተሞችን ወደ መምረጥ ሂደት እንደሚገባ ኮሚሽነሯ በሰኞው ስብሰባ አመልክተው ነበር። የምክክር ኮሚሽኑ “በጥቂት ቀናት” ውስጥ ለሚያደርጋቸው የበይነ መረብ ስብሰባዎች እና በአካል ከሀገር ውጭ ለሚደረጉት ውይይቶች፤ የዳያስፖራ ኤጀንሲን ጨምሮ “ሌሎች ከዳያስፖራዎች ጋር የሚሰሩ” ተቋማትን እንደሚያማክር ብሌን ጠቁመዋል።
ከሀገር ውጭ የሚደረጉ ውይይቶችን በተመለከተ፤ በአካል መገኘት የሚችሉት በአካል እንዲገኙ፣ በስፍራው መገኘት የማይችሉት ደግሞ በበይነ መረብ እንዲታደሙ እንደሚደረግ ኮሚሽነሯ ገልጸዋል። ውይይቶቹን ለማካሄድ ኮሚሽነሮቹ ከሀገር ውጭ እንደሚጓዙ የጠቀሱት ብሌን፤ የእነዚህ ጉዞዎች ዓላማ በመጪዎቹ የምክክር ጊዜያት በርካታ ሰዎች እንዲሳተፉ ማድረግ መሆኑን አብራርተዋል። ጉዞው የሚደረግበት ጊዜ እና የትኞቹ ኮሚሽነሮች ወደ የትኞቹ አካባቢዎች እንደሚሄዱ ግን ገና አለመወሰኑን አክለዋል።
የምክክር ኮሚሽኑ በውጭ ሀገር ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጋር የሚየደርጋቸውን ውይይቶች በተመለከተ፤ የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ “ተመሳሳይ አውድ ስሌለው፤ በሀገር ውስጥ የተከተልነውን አይነት የአሰራር ስርዓት አንከተልም” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በሀገር ውስጥ የሚደረገው ተሳታፊዎች ልየታ ከወረዳ እና ልዩ ወረዳ ጀምሮ ከታች ወደላይ የሚደረግ መሆኑን የጠቆሙት ሌላኛዋ ኮሚሽነር ብሌን፤ በምክክሩ የሚሳተፉ ተሳታፊ ዳያስፖራዎች የሚለዩት በ“ክላስተር” ደረጃ ከዳያስፖራ ማህበረሰቦች (community) እንደሆነ ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)