የገቢዎች ሚኒስቴር በግማሽ ዓመት ብቻ 4.1 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ሀሰተኛ ደረሰኞችን በምርመራ ማግኘቱን አስታወቀ   

በአማኑኤል ይልቃል

የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፈው ስድስት ወራት “በጥናት በተለዩ” ድርጅቶች ላይ ባደረገው የምርመራ ኦዲት 4.1 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ሀሰተኛ ደረሰኞችን እንዳገኘ አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ህገ ወጥ ደረሰኝ በግብር ስርዓቱ ላይ ችግር እንደፈጠረበት እና ይሄንን ለመከላከል የሚደረገው “ቅንጅታዊ አሰራር የተወሰነ ጉድለት” እንዳለበት ገልጿል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህንን ያስታወቀው የስድስት ወራት አፈጻጸሙን አስመልክቶ ዛሬ ረቡዕ ጥር 17፤ 2015 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። መግለጫውን የሰጡት ሚኒስትሯ ወ/ሮ አይናለም ንጉሴ፤ ግብር ለመሰወር ሲባል “ግብይት ሳይፈጸም እንደተፈጸመ ተደርጎ” የሚቀርቡ ሀሰተኛ ደረሰኞች በግማሽ ዓመቱ ውስጥ ከታዩ ችግሮች መካከል እንደሆነ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

“ህገወጥ ደረሰኝ አሁንም፣ ባለፉት ጊዜያትም ችግር ነበር። [ይህንን] በዝርዝር ገምግመናል” ያሉት ወ/ሮ አይናለም፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይሄንን ለመቅረፍ “በርካታ” ስራዎችን ቢያከናውንም “አሁንም ትኩረት የሚጠይቅ” እና “እንደ ችግር የሚቆጠር” መሆኑን ገልጸዋል። ተቋሙ ሀሰተኛ ደረሰኝ የሚያደርሰውን ጉዳት ለማስወገድ ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል አንዱ ግብር ከፋዮች እና አስመጪዎች “ያላቸውን የስጋት ደረጃ” መሰረት በማድረግ የሚከናወን የስጋት ትንተና (risk analysis) እንደሆነ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ከዚህም ባሻገር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በድርጅቶች የምርመራ ኦዲት (investigation audit) እንደሚያካሄድ ወ/ሮ አይናለም ጠቅሰዋል። ተቋሙ ባለፈው ስድስት ወራት ውስጥ ባካሄደው ጥናት ከለያቸው ድርጅቶች መካከል በ168 ያህሉ ላይ የምርመራ ኦዲት ማድረጉን አስታውቋል። በተካሄደው የምርመራ ኦዲትም 4.1 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 2,851 ሀሰተኛ ግብይት ደረሰኞችን ማግኘቱን ገልጿል።

የገቢዎች ሚኒስቴር የስድስት ወራት አፈጻጸሙን አስመልክቶ ያዘጋጀው ማብራሪያ፤ የምርመራ ኦዲት የተደረገባቸው ድርጅቶች ሀሰተኛ ደረሰኞቹን “ለታክስ ዓላማ” እንደተጠቀሙበት መረጋገጡን አመልክቷል። እነዚሁ ድርጅቶች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ደረሰኞች “በኦዲት ወቅት ውድቅ ተደርገው ታክስ እንዲወሰን” እንደተደረገ በማብራሪያው ላይ ሰፍሯል። ሀሰተኛ የታክስ ደረሰኞችን “ሲያሰራጩ ነበሩ” የተባሉ ሶስት ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታየ እንደሚገኝ ማብራሪያው ያስረዳል።

የሀሰተኛ ደረሰኝ ስርጭትን ለመቆጣጠር የገቢዎች ሚኒስቴር በመፍትሔነት ያስቀመጠው፤ የግብር አሰባሰብ ስርዓቱን “ሙሉ ለሙሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ” ማድረግ እንደሆነ ወ/ሮ አይናለም ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። “በተቋም ደረጃ ህገ ወጥነትን በማባረር ወይም በቁጥጥር ብቻ የምንፈታው አይደለም” ያሉት ሚኒስትሯ፤ መስሪያ ቤታቸው በቀጣይ የሚወስደው እርምጃ “ከኤሌክትሮኒክ የደረሰኝ ስርዓት ውጪ ያሉ አሰራሮችን ከግብር ስርዓቱ ማስወጣት” እንደሆነ ጠቁመዋል። 

የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ሀሰተኛ ደረሰኞችን ለማጣራት ካደረገው ምርመራ በተጨማሪ “ያልተከፈለ እና የተደበቀ ገቢን ለመለየት” የምርመራ ኦዲት ማከናወኑ በዛሬው መግለጫ ተጠቅሷል። በዚህ የምርመራ ኦዲት፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወለድ እና መቀጫን ጨምሮ 4.95 ቢሊዮን ብር ያልተከፈለ ታክስ ማግኘቱን አስታውቋል። መስሪያ ቤቱ “ህገ ወጥ የንግድ ማጭበርበር እና ኮንትሮባንድን” ለመቆጣጠር በወሰዳቸው እርምጃዎች፤ መንግስት ሊያጣ የነበረውን 40.7 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉም በመግለጫው ላይ ተነስቷል። 

የገቢዎች ሚኒስቴር ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 225.9 ቢሊዮን ብር የሰበሰበ ሲሆን በዚህም 99 በመቶ እቅዱን ማሳካቱን አስታውቋል። በግማሽ ዓመቱ ውስጥ የተሰበሰበው ገቢ  ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ አንጻር 31.9 በመቶ እድገት ማሳየቱን ሚኒስትሯ ወ/ሮ አይናለም በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)