በአማኑኤል ይልቃል
ላለፈው አንድ ዓመት ገደማ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽንን ሲመሩ የቆዩት አቶ መሐመድ አብዱራህማን፤ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሆነው ተሾሙ። አዲሱ ተሿሚ በቀድሞው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ለስምንት ዓመታት በምክትል ዋና ዳይሬክተርነት የሰሩ ናቸው።
አቶ መሐመድ ከተመሰረተ 72 ዓመታት ያስቆጠረውን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መስሪያ ቤትን በዋና ዳይሬክተር እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተሾሙት ዛሬ ረቡዕ ጥር 17፤ 2015 እንደሆነ የተቋሙ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አዲሱ ዋና ዳይሬክተር ዕድሜ ጠገብ በሆነው መስሪያ ቤት ከፕሮጀክት መሀንዲስነት አንስቶ በተለያዩ ደረጃዎች ሰርተዋል።
አቶ መሐመድ ለ20 ዓመታት ካገለገሉበት መስሪያ ቤት የለቀቁት፤ የመንግስት የልማት ድርጅት ለሆነው የኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ በተሾሙበት ወቅት ነበር። በሲቪል ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ያገኙት አዲሱ ተሿሚ፤ ከእንግሊዙ ሬዲንግ ዩኒቨርስቲ በኮንስትራክሽን አስተዳደር ትምህርት በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቀዋል።
ተሰናባቹ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ተገኝ፤ ከተተኪያቸው ጋር ተቀራራቢ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ነበሩ። አቶ ሀብታሙ በሲቪል ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን ሁለተኛ ዲግሪያቸው ደግሞ በኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ አስተዳደር አግኝተዋል። አቶ ሀብታሙ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደርን የመሩት ለአራት ዓመት ከመንፈቅ ነበር።
በእርሳቸው የአስተዳደር ዘመን ተቋሙ ለረጅም ዓመታት ሲጠቀምበት የቆየውን “የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን” የተሰኘውን ስያሜ ቀይሯል። አቶ ሀብታሙ በተቋሙ በነበራቸው ቆይታ፤ “ለረጅም ጊዜ ከህዝብ ጥያቄ ይቀርብባቸው የነበሩ የመንገድ መሰረተ ልማቶች እንዲገነቡ በማድረግ” ረገድ ስማቸው በበጎ ይነሳል። ከዚህ በተጨማሪ በተቋሙ ያከናወኗቸው “የሪፎርም ስራዎች” የሚጠቀሱላቸው ናቸው።
በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣንን በዋና ዳይሬክተርነት፤ በኢትዮጵያ መንገዶች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽንን ደግሞ በዋና ስራ አስኪያጅነት የመሩት አቶ ሀብታሙ፤ ካለፈው አርብ ጥር 12፤ 2015 አንስቶ የማዕድን ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል። ከሌሎች ሁለት ሚኒስትሮች ጋር በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አማካኝነት ሹመት ያገኙት አቶ ሀብታሙ፤ ሹመታቸው በተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀው ትላንት ማክሰኞ ጥር 16 ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)