በአማኑኤል ይልቃል
የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ከወሰዱ ተፈታኞች ውስጥ ከ50 በላይ ውጤት ያመጡት፤ 3.3 በመቶ መሆናቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ፈተናውን በትክክል ከወሰዱት 896,520 ተማሪዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ ውጤት ያመጡት፤ 29,909 መሆናቸውን ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በትላንትናው ዕለት ይፋ የተደረገውን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤትን አስመልክቶ ዛሬ አርብ ጥር 19፤ 2015 በሰጡት መግለጫ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ በዩኒቨርስቲዎች የተሰጠው የ12ተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተካሄደው በሁለት ዙር ነበር፡፡ ከመስከረም 30 እስከ ጥቅምት 18፤ 2015 በተሰጠው በዚህ ሀገር አቀፍ ፈተና፤ የማህበራዊ ሳይንስ እና የተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ ተማሪዎች ፈተናውን የወሰዱት በተለያየ ጊዜ ነው።
ከሁለቱ የትምህርት ዘርፎች ውስጥ የተሻለ ውጤት የተመዘገበው በተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች መሆኑን ፕሮፌሰር ብርሃኑ በዛሬው መግለጫቸው ላይ ገልጸዋል። በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ፈተናውን ከወሰዱት 339,642 ተማሪዎች ውስጥ፤ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያመጡት 6.8 በመቶው ናቸው። በማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ደግሞ 556,878 ተማሪዎች ፈተናውን የወሰዱ ሲሆን፤ ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያመጡት 1.3 በመቶው ብቻ መሆናቸውን ፕሮፌሰር ብርሃኑ አስታውቀዋል።
ከ50 በመቶ በላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ የትምህርት ሚኒስቴር አዲስ አሰራር ለመከተል ማቀዱን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት ከግማሽ በላይ ያመጡት 30 ሺህ ገደማዎቹ ተማሪዎች በሚቀጥለው ዓመት በቀጥታ ወደ ዩኒቨርስቲ ገብተው የአንደኛ ዓመት ተማሪ ይሆናሉ። ቀሪዎቹ ደግሞ የዩኒቨርሲቲዎችን የመቀበል አቅም መሰረት በማድረግ፤ የተሻለ ያመጡት ተመርጠው ወደ ዩኒቨርስቲ እንዲገቡ እንደሚደረግ የትምህርት ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
ይሁንና እነዚህ ተማሪዎች በቀጥታ የዩኒቨርስቲ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች እንደማይሆኑ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ጠቁመዋል። ተማሪዎቹ “የደከሙባቸው ትምህርቶችን” ለአንድ ዓመት በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እየተማሩ ከቆዩ በኋላ፤ በዓመቱ መጨረሻ ፈተና ወስደው ካለፉ በዩኒቨርስቲዎች የአንደኛ ዓመት ተማሪ ሆነው እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)