በአማኑኤል ይልቃል
ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወዲህ በአማራ ክልል ስር እየተዳደረች የምትገኘው አላማጣ ከተማ፤ በቀበሌዎች አደረጃጀት ላይ ለውጥ አደረገች። የከተማዋ ጊዜያዊ አስተዳደር ያደረገው ይህ የመዋቅር ለውጥ፤ “ህጋዊ አካሄድ” የተከተለ መሆኑ ላይ ጥያቄ ተነስቶበታል።
በአዲሱ የመዋቅር ለውጥ መሰረት በአላማጣ ከተማ ከዚህ ቀደም የነበሯት አራት ቀበሌዎች ወደ ስምንት አድገዋል። የአላማጣ ከተማን እየመራ ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር የቀበሌዎችን ቁጥር በእጥፍ ያሳደገው፤ ነባሩ መዋቅር በተዘረጋበት ጊዜ የነበረው የህዝብ ቁጥር በመጨመሩ እና የከተማዋ ስፋት በማደጉ እንደሆነ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ሀይሉ አበራ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
አላማጣን በአራት ቀበሌዎች የሚከፍለው የቀድሞው መዋቅር በተዘረጋበት ጊዜ የከተማዋ ነዋሪዎች ቁጥር 20 ሺህ ገደማ እንደነበር የሚያነሱት ከንቲባው፤ በዚያን ወቅት የአንድ ቀበሌ ነዋሪዎች ብዛት ከአምስት ሺህ በላይ እንዳልነበረ ተናግረዋል። “አሁን የህዝብ ቁጥሩ ወደ 120 ሺህ ደርሷል። ከዚያም በላይ ነው” የሚሉት አቶ ሀይሉ፤ የህዝብ ብዛት መጨመሩ አገልግሎቶቹን ተደራሽ በማድረግ ረገድ እና በአስተዳደር ላይ ችግር መፍጠሩን አስረድተዋል።

በነባሩ መዋቅር 35 ሺህ ነዋሪዎችን የያዘ ቀበሌ እንደነበር የሚጠቅሱት ከንቲባው፤ “አንድ ቀበሌ የሚባለው፤ የአንድ ወረዳ ከተማ ስፋት እና የህዝብ ቁጥር ያለው ነው። ይህ ደግሞ ለማስተዳደር አልተመቸም” ሲሉ ችግሩን አስረድተዋል። ይህን የሚያህል የህዝብ ብዛት የአንድ ቀበሌ አመራሮች ሊያስተዳድሩ ከሚችሉት በላይ በመሆኑ፤ የአስተዳደር ምቹነትን በሚያመጣ መልኩ ቀበሌዎቹን እንደ አዲስ ማዋቀር “ተገቢ እና አስፈላጊ” ሆኖ መገኘቱንም አብራርተዋል።
በዚህም መሰረት “ህዝቡ የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኝ” በማሰብ፤ አዲስ የቀበሌ መዋቅር ተዘርግቶ አመራሮች እንደተሾሙ አቶ ሀይሉ ገልጸዋል። አዲሶቹ አመራሮች ካለፈው ሳምንት ሰኞ ጥር 8፤ 2015 ጀምሮ ወደ ስራ መግባታቸውን አክለዋል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ አዲሶቹን ቀበሌዎች አደራጅቶ ወደ ስራ ቢገባም፤ የመዋቅር ለውጥ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ህጋዊ ሂደቶች አለመሟላታቸውን “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው የክልሉ የስራ ኃላፊዎች ተናግረዋል።
በአንድ ክልል ውስጥ የሚገኙ የመዋቅር ለውጦች የሚጸድቁት በክልል አስተዳደር ምክር ቤት ቢሆንም፤ በአላማጣ ተግባራዊ የተደረገው የቀበሌዎች ቁጥር ለውጥ ግን እስካሁን በአማራ ክልልም ሆነ በትግራይ ክልል አልጸደቀም። በትግራይ ክልል ህገ መንግስት መሰረት የአላማጣ ከተማ በክልሉ ደቡባዊ ዞን ስር የምትገኝ ከተማ ነች። በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ግን ከተማይቱ እየተዳደረች የምትገኘው በአማራ ክልል ስር ነው።

የአላማጣ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሞገስ እያሱ፤ በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ለሚገኙት ሰራተኞች ደመወዝ እየከፈለ የሚገኘው የአማራ ክልል መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። የከተማይቱ ከንቲባ አቶ ሀይሉ በበኩላቸው፤ የአላማጣ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር ተጠሪነቱ ለአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን መሆኑን አስታውቀዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተስፋው ባታብል፤ የአላማጣ ከተማን የሚያስተዳድረው አካል “በነዋሪዎች ምርጫ” የተዋቀረ መሆኑን ተናግረዋል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተቋቋመው፤ ለከተማዋ ነዋሪዎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዲያቀርብ መሆኑንም አክለዋል። የከተማይቱ ጊዜያዊ አስተዳደር ስላካሄደው የመዋቅር ለውጥ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ተስፋው፤ “ቀበሌ አይከፈልም” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ “ስራው ህዝቡን ማረጋጋት ብቻ ነው። ውሃ ማቅረብ፣ ምግብ ማቅረብ፣ ጸጥታውን ማስከበር ነው” ሲሉም የተቋቋመበት ዓላማ በጊዜያዊነት እነዚህን ጉዳዮች እንዲያከናውን መሆኑን ጠቁመዋል። የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪው አክለውም አላማጣ “ገና ወደ አማራ ክልል ውስጥ አልተካለለም” ብለዋል። የአላማጣ ከንቲባ አቶ ሀይሉ በበኩላቸው “እኛ already ጥያቄያችን ተመልሷል ብለን ነው የምናምነው። ምክንያቱም [አላማጣ] በህግ ወደ ትግራይ የሄደበት አግባብ አልነበረም” ሲሉ ይሞግታሉ።

በአላማጣ ከተማ ተግባራዊ የሆነውን የመዋቅር ለውጥ ለማጽደቅ የታሰበው፤ ለአማራ ክልል አስተዳደር ምክር ቤት በማቅረብ መሆኑን ከንቲባው ይናገራሉ። ይሁንና አዲሱ መዋቅር ከመጽደቁ በፊት የአላማጣ ከተማ “ወደ አማራ ክልል የመጠቃለል ህጋዊ ሂደት መጠናቀቅ አለበት” በሚለው የክልሉ ኃላፊዎች አስተያየትም ይስማማሉ። “ነገ ማንነታችን ተመልሶ፤ በህጋዊ መንገድ ወደ አማራ ክልል ሲቀርብ፤ የክልሉ ምክር ቤት ያጸድቃል ብለን እንጠብቃለን” ሲሉም አቶ ሀይሉ ተስፋቸውን ይገልጻሉ።
የአላማጣ ከተማ የመዋቅር ለውጥ ጥያቄ እስካሁን ለአማራ ክልል መንግስት እንዳልቀረበ፤ የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንሙት በለጠ እና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ደሳለኝ አስራደ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የአማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ፤ አላማጣ ከተማን በተመለከተ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የደረሰ ጥያቄ መኖሩን አስታውሰዋል። ከአላማጣ ከተማ በተጨማሪ ከወሰን እና ማንነት ጋር በተያያዘ ጥያቄ የሚነሳባቸው ሌሎች ቦታዎች መኖራቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የገለጹት አቶ ግዛቸው፤ ጥያቄዎች መቅረብ ያለባቸው “በተናጠል የአንዲት ከተማ ጉዳይን በማንሳት አይደለም” ብለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)