የ12ኛ ክፍል ፈተና ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 39.2 በመቶው ያህሉ “አንድም ተፈታኝ” ለዩኒቨርስቲ አለማሳለፋቸው ተገለጸ

በዘንድሮው ዓመት መደበኛ ተማሪዎቻቸውን የ12ኛ ክፍል ፈተና ካስፈተኑ በመላው አገሪቱ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ፤ በ39.2 በመቶው ያህሉ “አንድም ተፈታኝ” የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት እንዳላመጣ ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ። ከመደበኛ ውጪ ያሉ ተማሪዎችን ያስተፈኑ ትምህርት ቤቶች ስሌት ውስጥ ሲገቡ፤ ምንም ተማሪ ያላለፈባቸው ትምህርት ቤቶች ብዛት ወደ 56 በመቶ ከፍ እንደሚል ሚኒስቴሩ አስታውቋል። 

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ይህንን ያስታወቁት፤ በተያዘው ዓመት በሁለት ዙር የተሰጠውን የ12ተኛ ክፍል ፈተና ውጤት አስመልክተው ዛሬ አርብ ጥር 19፤ 2015 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። የክልል ትምህርት ቢሮ አመራሮች በተገኙበት በተሰጠው የዛሬው መግለጫ ላይ ሚኒስትሩ የፈተናውን ውጤት እና ተያያዥ መረጃዎችን ለጋዜጠኞች በዝርዝር ገልጸዋል። ፕሮፌሰር ብርሃኑ “የሚሳዝን” ብለው በጠሩት የዘንድሮው 12ኛ ክፍል ውጤት፤ ፈተናውን በትክክል ከወሰዱት 896,520 ተማሪዎች ውስጥ የዩኒቨርስቲ መግቢያ የሆነውን 50 በመቶ ውጤት ያመጡት፤ 3.3 በመቶው ብቻ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በመላው አገሪቱ ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ ማሳለፍ የቻሉት ሰባት ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸውንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። ከእነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ “ደሴ” እና “ኦዳ” ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም የወላይታ ሊቃ ትምህርት ቤት በትምህርት ሚኒስትሩ መግለጫ በምሳሌነት ተጠቅሰዋል። ከግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተማሪዎቹ ያለፉለት 41 ተማሪዎችን ያስተፈተነው ለባዊ አካዳሚ መሆኑንም አክለዋል። 

በሀገር አቀፍ ደረጃ በመደበኛ የትምህርት አሰጣጥ ስርዓት ያስተማሯቸውን የቀን ተማሪዎች ለፈተና ያስቀመጡ ትምህርት ቤቶች ብዛት 2,959 እንደሆኑ በዛሬው መግለጫ ተጠቅሷል። “ከእነዚህ ውስጥ 1,798ቱ ቢያንስ አንድ ተማሪ አሳልፈዋል” ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ 60.7 በመቶው ያህሉ ትምህርት ቤቶች ከግማሽ በላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች እንዳሏቸው አስረድተዋል። 

በቀሪዎቹ 39.2 በመቶ ያህል ትምርት ቤቶች ግን አንድም የ12ኛ ክፍል ተማሪ ከ50 በመቶ በላይ  ውጤት እንዳላመጣ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። ይህ ቁጥር በመደበኛ ትምህርት የወሰዱ ተማሪዎች የተፈተኑባቸው ትምህርት ቤቶችን ብቻ እንደሚያካትት ፕሮፌሰር ብርሃኑ አስታውሰዋል። “መደበኛ ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን ሌሎቹንም ጨምረን ካደረግን፤ የጠቅላላ የትምህርት ቤቶች ብዛት እኛ ዳታ ላይ 5,040 ነው የሚመጡት። ከዚህ ውስጥ 56 በመቶው ምንም ተማሪ አላሳለፉም” ሲሉ በሀገሪቱ ካሉት ትምህርት ቤቶች ከግማሽ በላይ በሚሆኑት አንድም ተማሪ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ውጤት እንዳላመጣ አብራርተዋል።  

በ12ኛ ክፍል ፈተና ላይ የታየው ይህ አነስተኛ ውጤት “እንደ ሀገር ትምህርት ቤቶች ምን እንደሚመስሉ የሚያሳይ ነው” ሲሉ ፕሮፌሰር ብርሃኑ በዛሬው መግለጫቸው ተናግረዋል። “ይህ ፈተና ማንነታችንን፣ የትምህርት ስርዓታችን ያለበትን ደረጃ፤ በግላጭ፣ ልንደብቀው በማንችለው መልኩ፣ በወሬና በአሉባልታ ሳይሆን በዳታ እንድናገኝ አድርጎናል” ሲሉም በአጽንኦት ተናግረዋል።

“[ለዚህ ውጤት] እውነተኛ ተጠያቂው የወደቁት ተማሪዎቻችን ብቻ አይደሉም። የወደቅነው እንደ ሀገር ነው። ኃላፊነቱም የጋራ እና የሁላችን ነው” ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ መምህራን፣ ርዕሰ መምህራን፣ መንግስት፣ ወላጅ እና ባለሀብቶች ተጠያቂነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። “ተማሪዎች በሚገባቸው ዲሲፕሊን፣ ትምህርትን ከቁም ነገር ወስደው ትምህርታቸውን መከታተል አለመቻላቸው በተወሰነ ደረጃ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ መምህራን እና ርዕሰ መምህራንም በአደራ የተቀበሏቸው ተማሪዎች ይህንን ውጤት በማስመዘገባቸው ተጠያቂ መሆናቸውን አንስተዋል። 

“መንግስት እንደ መንግስት ያለበትን ኃላፊነት በምንም አይነት ተወጥቷል ማለት አይቻልም” ሲሉም “የትኛውንም መንግስት ሳይለይ” ሁሉም አገዛዝ ለተማሪዎች ውጤት ተጠያቂነት እንዳለበት አመልክተዋል። “ትምህርት ከካድሬ፣ ከፖለቲካ ጋር ተያይዞ እዚህ ደረጃ እስከሚደርስ መጠበቁ፤ በመንግስት ደረጃ ሁላችንም መንግስት ላይ ያለን ሰዎች ኃላፊነት የምንወስድበት ነው” ሲሉ ለውጤት ማሽቆለቆሉ የመንግስት ባለስልጣናት ጭምር ተጠያቂ እንደሆኑ ተናግረዋል። ከፌደራል እስከ ክልል ያሉ የትምህርት ዘርፍ አመራሮች ተጠያቂነቱን እንደሚጋሩም አስረድተዋል። 

ልጆችን ስነ ምግባር በማስተማር ረገድም ወላጆች፣ እንዲሁም ትምህርት ቤቶች ኃላፊነታቸውን እንዳልተወጡም ፕሮፌሰር ብርሃኑ በመግለጫው ላይ አንስተዋል። “የግል ትምህርት ቤቶች እውነተኛ ትምህርት፣ ትክክለኛ ዲሲፕሊን ያለው ትምህርት ለልጆቻችን ይሰጣሉ ወይ? የመንግስት ትምህርት ቤቶችስ ይህንን ይሰጣሉ ወይ? ሁሉም ጋር ነው ውድቀት ያለው” በማለትም ወቀሳቸውን አሰምተዋል። “ሀብት በአቋራጭ የሚገኝበት ሀገር ሲሆን፤ [ተማሪ] ለምንድነው ትምህርት በትክክል የሚማረው?” የሚል ትችት አዘል ጥያቄም ሰንዝረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)